Tuesday, November 19, 2013

ፍልስፍና፡ የሳይንስ አልፋና ዖሜጋ!



ዛሬ ሳይንስ ብለን የምንጠራው ማንኛውም የዕውቀት ዘርፍ መገኛው የዓለም ፍልስፍና፤ አስገኚዎቹና  ጀማሪዎቹ መሀንዲሶች ደግሞ የዓለም ፈላስፎች ናቸው፡፡ ለዚህም የአሪስጣጣሊስን ሁለገብ ስራዎች፣ የፍራንሲስ ቤከንን ኢንደክቲቪዝምና የፓይታጎረስ ቴረምን በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ከዚህም ባሻገር ከአባታቸው ከፍልስፍና በመገንጠል ራሳቸውን ችለው የተፈጥሮና የማህበረሰብ ሳይንስ በሚል መጠሪያ ኑሮን የጀመሩት ልጆቹንና፤ ሂሳብ፣ አስትሮኖሚ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ህግ፣ ሶሲዎሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ፖለቲካል ሳይንስና ወዘተ በመባል የሚታወቁት የልጅ ልጆቹን በአመክንዮ ባህል ከስር ከስር ኮትኩቶ በማሳደግና መስመር ሲስቱ በመገሰጽ የሚጠበቅበትን ድርሻ ያለማቋረጥ በመወጣት ላይ ይገኛል፤ ፍልስፍና፡፡
ይሁንና በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች ላይ ከአባቶቻቸውና ከአያቶቻቸው ርቀው በስደት የሚኖሩና ስለቀደመ ታሪካቸውና አሴቶቻቸው እምብዛም የማያውቁ ሳይንሶችና የእነርሱ ሞግዚት ሳይንቲስቶቻቸው  ከአባታቸው ፍልስፍና በዘመንና በባህርይ በመራራቃቸው አባታቸው እንደ ሞተና እንደ ተረሳ በመቁጠር ከእርሱ መውረስ የሚገባቸውን ስልታዊ መጠራጠርን (Methodical skepticism) ፣ በጥልቀት የመጠየቅና (critical inquiry) የማሄስ (critique) ባህልን ወደ ጎን በመተው  ሳይንሳዊ ሃይማኖትን (Scientific dogmatism) ገንዘብ በማድረጋቸው በማንነት ጥያቄ ውዥንብር ውስጥ ገብተው የተወለዱበትን ዓላማ ማሳካት አቅቷቸው ሲደነባበሩ መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የአባታቸውንና ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ ሳይንሶችና ሞግዚቶቻቸው ሳይንቲስቶች ባሉባቸው ክፍላተ ዓለማት ውስጥ የሳይንስና ፍልስፍና ዘለዓለማዊ ቁርኝትና መግቦት እስከዛሬ ህያው ሆኖ እናገኛለን፡፡ ለዚህም ነው የጽሁፌን ርዕስ ፍልስፍና የሳይንስ አልፋና ኦሜጋ በማለት የሰየምኩት፡፡ አልፋና ዖሜጋ በግሪክ የመጀመሪያና የመጨረሻ ማለት፡፡ ከሳይንሶች ሁሉ በፊት የነበረ በመሆኑና እነርሱም ከእርሱ በመገኘታቸው የመጀመሪያ ስለው የመጨረሻ ያልኩበት  ምክንያትም ዛሬም ድረስ ፍልስፍና ለሳይንስ መሻሻል የላቀ አስተዎጽኦ በማበርከት ላይ በመሆኑ ነው፡፡
በፍልስፍናና በሳይንስ መካከል እጅግ ጠንካራ ትስስር እናገኛለን፡፡ ከሳይንስ ከተለየ ፍልስፍና ግምታዊ ዕውቀት (Speculative Knowledge) እንደሚሆን ሁሉ፤ ከፍልስፍና የተለየ ሳይንስም እንዲሁ አዳዲስ ፈጠራዎች የማይገኙበትና በእምነት ላይ የተመሰረተ የዘልማድ ዕውቀት (Common sense Knowledge) መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በማንኛውም የሳይንስ ዘርፍ  ለከፍተኛው የትምህርት፣ የምርምርና የግኝት ደረጃ የሚሰጠው ዲግሪ የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ (Doctor of Philosophy) ወይም በምህጻረ ቃል ፒ.ኤች.ዲ (Ph.D) ተብሎ መሰየሙ ፍልስፍና የሳይንስ ኦሜጋ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ስለ ዕውቀት ምንነት፣ ስለእውነትና እውነተኛ እውቀት ምንነትና ስለ ሰው ልጆች የእውቀት ምንጭ፣ ስለ ሳይንስ፣ ሳይንሳዊ ስነ-ዘዴና ሌሎች ሳይንሳዊ ያልሆኑ የእውቀት መንገዶች የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና ንዑስ ዘርፍ ስነ-ዕውቀት (epistemology) ይባላል፡፡
ይህ የፍልስፍና ዘርፍ ባለንበት ዘመን  “የሳይንስ ፍልስፍና” (Philosophy of Science) በሚል ሳይንሳዊ እውቀት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ የሳይንስን ፍልስፍናዊ መሰረት ጠንቅቀው በሚያውቁ ምሁራን በሚመሩ በርካታ ዓለማችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት በተለይ ለሳይንስ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንደ አንድ ወሳኝ (Compulsory) ኮርስ ይሰጣል፡፡
የሳይንስ ፍልስፍና ትምህርት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፤ በተለይም ፒ.ኤች.ዲ ተመራማሪዎች ዋነኛ ግብ አዲስ እውቀትን ማግኘት (Innovation & Discovery) እንደመሆኑ መጠን ለማንኛውም የሳይንስ ጥናት መስኮች የሚዘጋጁ ምሁራን ስለ እውቀት ምንነት፣ ምንጮችና መስፈርቶች ወዘተ ማወቃቸው የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በዘልማድ ከሚያውቁት ወይም በአንደኛ፣ በሁለተኛ ደረጃና በቅድመ ምረቃ ትምህርት ሂደት ላይ ካወቁትና ካወቁበት መንገድ በተለየ ሁኔታ እንዲጠይቁ፣ አንዲመራመሩና በተሰማሩበት የምርምር ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ነባር ንድፈ ሃሳቦችን በእምነት እንዲቀበሉ ሳይሆን በጥልቀት እንዲፈትሹና እንዲያሻሽሉ፣ ማህበራዊ ችግሮችን እንዲለዩና እንዲፈቱ፣ አዳዲስ ንድፈ ሃሳቦችን (New Theory) እንዲያፈልቁ፣ እንዲሁም እንደ ሳይንስ አብዮተኛው ኮፐርኒከስ (Copernicus Revolutions) አዲስ የአስተሳሰብ አድማስ (New Paradigm) ወይም ርዕዮተ ዓለም (World View) እንዲያመጡ፤ በአጠቃላይ የነገዎቹን ሳንቲስቶችና ቴክኖሎጂስቶችን ለማፍራት “የሳይንስ ፍልስፍናን” ማስተማር የጥናትና ምርምርን ሀ-ሁ እንደማስቆጠር ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን በሀገሪቱ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አብዮት ለማምጣት ሰባ በመቶ ትኩረት ሰጥተው በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ መርሃግብሮች በትጋት እየሰሩ መሆናቸው በሚነገርላቸው የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ምንም ዓይነት “የሳይንስ ፍልስፍና” ትምህርት አለመካተቱ ነው፡፡ አንዳንድ ተቋማት ይባስ ብለው ከአንዳንድ የቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንደ Introduction to Logic የመሳሰሉ ወሳኝ የፍልስፍና ትምህርት ዓይነቶች እንደ አላስፈላጊ በመቁጠር ከቀድሞው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ለቅመው አስወግደዋቸዋል፡፡
ለሀገር ልማት ሳይንስ፤ ለሳይንስ እድገት ደግሞ የፍልስፍና ህልውና ይህን ያህል አስፈላጊ ሆኖ ሳለ በሀገራችን ለፍልስፍናና ለፍልስፍና ኮርሶች ይህን ያህል ትኩረት መነፈጉ ለምን ይሆን? የፍልስፍናን በሰው ልጆች ሁለንተናዊ ልማት (Genuine Development) ላይ ያለውን ሚና ከማንም በላይ የሚውቁትና የተጠቀሙበት ምዕራባውያንና በምዕራባውያን ተጽዕኖ ስር የሚገኙት እንደ IMF እና World Bank ዓይነት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትስ ፍልስፍናን እንዴት ለአፍሪካውያን ሳያስቡት ቀሩ?

Sunday, May 19, 2013

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ (USA)!


የፊታችን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ለማክበር ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በ1960ዎቹ የጋናውያን ፕሬዚደንት የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ከአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካውያን ወንድማማችነት ለማረጋገጥ “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ” (USA) በሚል መጠሪያ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ያልተሳካ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ንክሩማህ የዘራው ዘር በመሰሎቹ የነጻ አፍሪካ የወቅቱ መሪዎችና ምሁራን ጆሞ ኬንያታ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ሌኦፖልድ ሴንጎር፣ ዊልሞት ብሊደንና አብዱላዬ ዋዴ ትጋት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጽያዊው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ግንቦት 25 ቀን 1963ዓ.ም ስፖንሰር ባደረጉትና በአዲስ አበባ በተካሄደው የፓን አፍሪካን ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) ለመውለድ በቅቷል፡፡ ውሎ አድሮም ይኸው ድርጅት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) በሚል ተሰይሟል፡፡
ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት መነሻቸው የፓን አፍሪካን ፍልስፍና መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ፓን አፍሪካ ፍልስፍና ምንድነው? መቼ ተጀመረ? ለምን? ዛሬ ፍልስፍናው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለነገይቱ አፍሪካስ ምን ተስፋ ይኖረዋል? የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይሆናል፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ህዝቦችን የሚጋሯቸውና የሚያስተሳስሯቸው የጋራ ጉዳዮችና ዓላማዎች አሏቸው፣ እነዚህንም ለማሳካት አፍሪካውያን በአንድነትና በኅብረት መስራት ይኖርባቸዋል የሚል እምነት ላይ የተመሰረተ የአፍሪካውያን ፍልስፍና ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም  ፍልስፍና በመላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች፣ ከአፍሪካ ውጪ የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚኖሩ ነጭም ሆነ ጥቁር ህዝቦች ያራመዷቸውን ሃሳቦችና ለተፈጻሚነቱ የከፈሉለትን መስዋዕትነትና በአሁኑ ወቅት የሚራመደውን መሰል ፍልስፍና አጠቃሎ የሚይዝ ሃሳብ ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም  አፍሪካ በራሷ ነባር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና መመመራት አለባት የሚል እምነትን የሚያራምድ ሲሆን ሁለት መገለጫዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አህጉራዊ  ፓንአፍሪካኒዝም (continental pan-Africanism) የሚባለው ሲሆን ይህም  በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ሀገሮችና ህዝቦች በፖለቲካና በዓለምአቀፋዊ ትብብር አቅጣጫ በአንድነት መስራት እንደሚገባቸው የሚያስረግጥ ነው፡፡ ሁለተኛው መገለጫ ዲያስፖራ ፓንአፍሪካኒዝም (Diaspora Pan-Africanism) ይባላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በባርነትና በስደት ወደሌሎች አህጉራት ተወስደው የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካውያንና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ አፍሪካውያን ዘንድ ወንድማማችነትና ትብብር ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም በወቅቱ በአውሮፓውያን ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድና የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ለመዋጋትና ከስሩ ገርስሶ ለመጣል ቁርጠኛ ሆነው በተነሱ አፍሪካውያንና ከአህጉሪቱ ተሰደው በጭካኔ፣ በግፍ፣ በአድልዎ አገዛዝ ስር ወድቀው- በአውሮፓና በአሜሪካ አህጉራት ተበታትነው ይኖሩ በነበሩ ትውልደ አፍሪካውያን እልህ የተቀጣጠለ የአፍሪካውያን ፍልስፍና ፍልስፍናውን ተከትሎ የፈነዳ ንቅናቄ ነው፡፡
 ምንም እንኳን  የንቅናቄው መስራቾች በዓለም ላይ ተበታትነው የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያንና በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ምሁራን በመሆናቸው ፍልስፍናውን እውን ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነ ቢረዱትም አፍሪካውያንና ትውልደ አፍሪካውያን ህብረት መፍጠርና በአንድነት ለመስራት ጥረት ማደረግ ከቻሉ ከግብ አንደሚያደርሱት ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አራማጅና የምዕራብ አፍሪካ ባህል አስተዋዋቂው ላይቤርያዊው ዊልሞት ብሊደን (Edward Wilmot Blyden) በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በአስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ፓን አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) የሚለውን መጠሪያ ቃል ለፍልስፍናው የሰየመውም ብሊደን መሆኑን ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በዘመናዊ መልኩ የቅኝ አገዛዝን በመቃወም የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በተደራጀ መልኩ እንደጀመረ የሚነገርለት በካረቢያን ደሴት ውስጥ የህግ ባለሙያ የነበረው ሄንሪ ሲልቬስተር ዊልያምስ (Henery Sylvester Williams) ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲወያዩ ለማስቻል በር የከፈተውን የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካ ጉባዔ በለንደን ከተማ ውስጥ ለማዘጋጀት ችሏል፡፡ በዊልያምስ የተጀመረው የፓን አፍሪካን ጉባኤ በቀጣይም በጥቁር አሜሪካዊው የታሪክና የሥነ-ማህበረሰብ ሊቅ ዱ ቦይስ (W.E.B. Du Bois) አዘጋጅነት በተከታታይ ተካሂዷል፡፡
በእነ ዱ ቦይስ ጥረት በአሜሪካን ሀገር በተመሰረተው የባለቀለም ህዝቦች ማጎልበቻ ማህበር (NAACP) እንቅስቃሴና የፓን አፍረካኒዝም ተከታታይ ጉባዔያት ያላሰለሰ ጥረት ሳቢያ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹና ሰላሳዎቹ አካባቢ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በአሜሪካ በሚኖሩ ጥቁር ህዝቦችና ትውልደ አፍሪካውን ዘንድ  ከፍተኛ የባህል መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ በኒዮርክ ከተማ ሀርለም በተባለ አካባቢ የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን ሀርለም ሬናይሰንስ በሚል የራሳቸውን ነባር  ማንነት (Negritiude) የሚያንጸባርቁ እንደ ሙዚቃ ያሉ ኪነጥበባዊ ስራዎችን በመጠቀም በጥቁርነታቸው የሚሰማቸውን ኩራትና ለመግለጽና በዘርና በቀለም የሚፈጸመውን አድልዎ ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡ በሃገር ቤትም ማልኮም ኤክስን (Malcom X) የመሳሰሉ ዲያስፖራ አፍሪካ ምሁራን በተደጋጋሚ ጉዞ በማድረግ ጥቁር አፍሪካውያን ለራሳቸው ማንነት ዋጋ እንዲሰጡና በአንድነት መስራት እንዲችሉ ብርቱ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሃገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነጻነት በተጎናጸፉ ማግስትም አንዳንድ የአፍሪካ ምሁራን መሪዎች አፍሪካ ነባር ወደሆነው የራሷን ማንነት መመለስና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ጋር አንድነት መፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ የታንዛንያው ፕሬዚደንት ጁሊየስ ኔሬሬ በ1974 ዓ.ም ዳሬ ሰላም ላይ የተካሄደውን ስድስተኛው የፓን አፍሪካን ኮንግረስ ከማዘጋጀቱም ባሻገር በርሱ ዘመን ታንዛንያ  የስዋሂሊ ቋንቋን የታንዛንያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል፤ ኡጃማ (Ujamma) በተባለው የአፍሪካውያን ልዩ የሆነ የሀገር ቤት ሶሻሊዝም ሀገሩን ለማስተዳደር ችሏል፤ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችም በየራሳቸው ነባር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና እንዲመሩ አስተምሯል፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አዘጋጅነት የዛሬ ሃምሳ ዓመት በወርሃ ግንቦት 1963ዓ.ም አፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ በተደረገው የፓን አፍሪካ ኮንግረስ ላይ በአፍሪካን ዳያስፖራና በአፍሪካ ምሁራን መሪዎች ጥረት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) በመውለድ ምናባዊው የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አፍሪካን አንድ የማድረግን ዓላማ  እውን ለማድረግ የመጀመሪው የመወጣጫ ድንጋይ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እንደታሰበው አፍሪካን አንድ ለማድረግ አልተሳካለትም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ መሪዎች በሃሳብ መጋጨት የጀመሩት ገና የምስረታ ጉባዔው “ሀ” ተብሎ ሲጀመር “ድርጅቱ ምን ዓይነት መልክ ይኑረው?”  በሚለው ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ መሪዎቹ በሁለት ጎራ ተከፍለዋል፡፡ በእነ ክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የነበሩት ጥቂት የሀገራት መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አፍሪካን አንድ የሚያደርግ በአንድ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚመራ (United States of Africa) ይሁን የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው ጎራየተሰለፉት ግን ገና ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ ብዙም ያልቆዩ ሀገራት በመሆናቸውና ውሳኔውን በመቃወማቸው ድርጅቱ  በራሱ አነስተኛ ስልጣን ያለው የሃገራቱን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትብብር የሚያጠናክር ተቋም እንዲሆን በሚል ለመመስረት በቅቷል፡፡  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በታንዛንያዊው ሳሊም አህመድ ሳሊም የአመራር ዘመን ድርጅቱ የተመሰረተበትን የአህጉሪቱን የፖለቲካና ኢኮኖሚዊ  ግብ ይበልጥ እንዲገልጸውና አህጉሪቱ የሉላዊነትን ተጽዕኖ እንድትወጣ በሚል ምክንያት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) የሚል አዲስ ስያሜ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ይኸውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚለው መጠሪያ ከቀድሞ የፓን አፍሪካ መስራቾች አፍሪካን አንድ የማድረግ ርዕይ የመነጨ ስለሆነና ድርጅቱ በተግባር እየተከተለ ያለው ግን አንድ ማድረግ ላይ ሳይሆን  መተባበር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ስያሜው መቀየር አለበት የሚል ነው፤ የስያሜው መቀየር ያስፈልጋል የሚለው ውሳኔ የፓን አፍሪካን ነባር ፍልስፍና መቀየርና በአዲስ ፍልስፍና መተካት ያስፈልጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአባል ሃገራቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ልማትና ሰላም ላይ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን ከሃምሳ ዓመት በፊት ከተመሰረተበት የፓን አፍሪካን ፍልስፍናና ርዕይ አንጻር ሲመዘን ግን የሚተችባቸውም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ አፍሪካን እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (USA) በዶላር  ወይም እንደ አውሮፓ ህብረት (EU) በዩሮ የሚገበያይ አንድ ጠንካራ፣ ሰላማዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አልቻለም፡፡ ይልቁንም አባል ሃገራቱ ከዘመን ወደ ዘመን በእርስ በርስ ግጭት ወደ ከመበታተንና በመነጣጠልና ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? የሰለጠነው የምዕራቡ አህጉር ከዕለት ወደ ዕለት አንድ ወደሚሆንበት ፍልስፍና ወደፊት ሲፈተለክ አፍሪካውያን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃማኖት፣ በቀለምና በቋንቋ ተከፋፍለን በጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን የኋሊት መፈርጠጣችን ለምን ይሆን? የፓን አፍሪካ ፍልስፍናስ ለአፍሪካ እድገት አስፈላጊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ትጥቆችን የያዘ ተግባራዊ ፍልስፍና ወይስ ሊተገበር የማይችል የቀደምት አፍሪካ መሪዎች ህልመኛ (ideal) ፍልስፍና?
በርግጥ አንዳንዶች በተለይም ምዕራባውያን የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና በተግባር ሊተረጎም የማይችል እንደ ግሪክ ፈላስፋው ፕሌቶ ሃሳባዊ ሪፐብሊክ (Plato’s Ideal Republic) በፍልስፍና ደረጃ የሚቀር እንጂ በውን የማይተገበር (Utopian Philosophy) ህልመኛ ፍልስፍና ነው በሚል ዝቅተኛ ግምት ሲቸሩትና ከአፍሪካ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምህዳር ለማውጣት ብርቱ ጥረት ሲደርጉ ኖረዋል፡፡ ለዚህም አስተሳሰብ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በመጀመሪያ ፍልስፍናው በቅኝ ገዢዎችና በባርነት አስፋፊዎችን  በመቃወም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ምዕራባውያን ይህን በአወንታ የሚቀበሉት አልነበረም፡፡ ከዚህም ባሻገር በባርነት ስርዓትም ሆነ በቅኝ አገዛዝ ታሪካቸው፣ እንዲሁም ከድህረ ቅኝ ግዛት በኋላ የአፍሪካ ህዝቦች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓታቸው ሰፊ ልዩነት ስነበራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካን ለመፍጠር የሚሞከር አልነበረም፡፡ በመጨረሻም አፍሪካውያን በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በፖለቲካዊ ስርዓት ሰፊ ልዩነት ስላላቸው ይህንን ልዩነት አስታርቆ በአንድነት ለመስራት  እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል የሚል ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አህጉሪቱን ወደ ዓለምአቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ የሚቀርብበት ሰረገላ ሆኖ አህጉራዊ ፓን አፍሪካኒዝም ባለንበት ዘመን በልዩ ልዩ መልኩ የአፍሪካን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት በተዋቀሩ እንደ ECOWAS, SADC, EAC በመሳሰሉ ክልላዊ ድርጅቶች አማካይነት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በእኔ እምነት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና ከዚህም አልፎ አፍሪካውያን ለራሳቸው ነባር ባህላዊ እሴቶችና ማንነት ቦታ ሰጥተው በነክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደተሰነዘረው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ  የአንድነት ደረጃ ላይ እስክትደርስ ድረስ መጓዝ ያለበት ፍልስፍና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የፍልስፍና ምሁራን፣ የፖለቲካዊ ሳይንስ ሊቃውንትና የአፍሪካ መሪዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የያኔዎቹ አፍሪካውያን መሪዎችና ምሁራን የያኔዎቹን ቅኝ ገዢዎች ለመዋጋት ክንዶቻቸውን መስተሃልያቸውን (mind) እንዳስተባበሩ ሁሉ፣ የዛሪዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቻችንን ለመዋጋትና የዛሬ ሃምሳ ዓመት የታሰበውን የፓን አፍሪካ ርዕይ እውን ለማድረግ ክንዶቻቸውንና መስተሃልያቸውን ማስተባበር አለባቸው እላለሁ፡፡  ያን ጊዜ የድርጅቱ መጠሪያም “ከአፍሪካ ህብረት” ወደ “አፍሪካ አንድነት”  (US Africa) ይመለስ ይሆናል…ማን ያውቃል?!

Saturday, April 27, 2013

ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!

የሚጥም መልክ፣ የሚጥም ሙዚቃ፣ የሚጮኽ ቀለም ፣ የተረጋጋ ስዕል የሚሉ የውበት አገላለለጾችን ሰምተው ይሆናል፡፡ እነዚህን አገላለጾች በድጋሚ ለአፍታ በአጽንኦት ቢመረምሯቸው ሙዚቃን በምላስ እንደመቅመስ፣ ቀለምን በጆሮ እንደመስማት፣ እንዲሁም ስዕልን በሰው ፀባይ እንደመግለጽ ነው፡፡ ስለ ውበት ስናነሳ በተለምዶ ከምንጠቀምባቸው ቆንጆ እና አስቀያሚ፤ ወይም የሚያምርና የሚያስጠላ ከሚሉት ቃላት ባሻገር ከላይ የጠቀስናቸውን ዓይነት ሌሎች ጽንሰ ሃሳቦችን ጥቅም ላይ መዋላቸው ስለ ውበት ያለን ግንዛቤ፣ ምልከታና ግምገማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጠቱን ያመለክታል፡፡
ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የሰው ልጅ እርካታን ከሚጎናጸፍባቸው መንገዶች አንዱ ውበት ነው፡፡ በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ውበትን ያደንቃሉ፤ ቆንጆ ሆነው መታየትን ይፈልጋሉ፤ ያማረ ነገርን ማየትንና መስማትን ይወዳሉ፡፡ ዓለማችን ስለውበት ብዙ ብላለች፤ በየዕለቱ ቀላል የማይባል ገንዘብ ውበትን ለመጠበቂያ ታወጣለች፡፡ በየወቅቱ ቄነጃጅቱን እያወዳደረች ትሸልማለች…ሌላም ሌላም፡፡ ለመሆኑ ውበት ምንድን ነው?  ውበት በምን መስፈርት ይለካል? በምን ቋንቋ ይገለጻል? ውበት ከሥነ-ምግባር ምን ዝምድና፤ ከሃብት ጋርስ ምን ግኑኝነት አለው?
ሥነ-ውበት (Aesthetics) የውበትን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት፣ እሴቶች፣ አተያዮች እንዲሁም የመገምገሚያ መስፈርቶችን የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሲሆን የዛሬው ጸሁፌ ዋና ዓላማም ስለ ውበት አጭር ሐተታ ማቅረብ ይሆናል፡፡ የሥነ-ውበት ፈላስፎች ውበት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአጠቃላይ የሰው ልጅን፣ ኪነ-ህንጻን፣ ስዕልን፣ ሙዚቃን፣ ቅርጻ-ቅርጽን፣ ቲያትርን፣ ስነጽሁፍን፣ ፊልምንና የመሳሰሉትን የሰው ልጆች የጥበብ ስራዎች፤ እንዲሁም የተፈጥሮን መስህቦችን አካቶ የሚያጠና ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡  ውበት ማለት የአንድ ነገር የሚስብ፤ የሚያረካ ወይም የሚያስደስት ገጽታ ወይም ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ውበት ውጫዊ ቅርጽን፣ ቀለምን፣ መጠንን፣ መልክን ወይም ደምግባትን (pure aesthetics) የሚያመለከት አልያም ውስጣዊ ማንነትንና ሥነ-ምግባርን (moral) የሚመለከት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡  ነገር ግን አስቸጋሪው ጥያቄ  ማንን የሚስብ፣ ማንን የሚያሰደስት ወይም የሚያረካ? የውበቱን ባለቤት? ማህበረሰቡን? የሚስብ ወይም የሚስደስትስ ምን ዓይነት ነገር ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለሱ ላይ ነው፡፡
የዓለማችን ሊቃውንት እነዚህን መሰረታዊ የሥነ-ውበት ጥቄዎች ለመመለስ በሁለት ታላላቅ ጎራ ተሰልፈው ለበርካታ ዘመናት ተሟግተዋል፤ መጻህፍትን ጽፈዋል፤ የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ አድማስም አስፍተዋል፡፡ በመጀመሪያ የምናገኘው የሁሉን አቀፎች (universalists) ወይም የፍጹማውያኑን ርዕዮተ ዓለም ሲሆን ይህም ውበት መለካት ያለበት ነገሮቹ በራሳቸው ባላቸው ማንነት እንጂ ከእነርሱ ውጪ በሚገኝ ማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በማህበረሰቡ ወግ፣ አመለካከት ወይም እምነት ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም የሚል አቋምን የሚያራምድ ነው፡፡ በፍጹማውያኑ ፍልስፍና ውበት በቦታና በጊዜ የማይለዋወጥ በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኝና አንድ ወጥ መስፈርት የሚተገበርበት (objective) ነው፡፡ እንደነዚህ ፈላስፎች እምነት አንዲት ሴት በአንድ ሃገር በሆነ ወቅት ቆንጆ ከተባለች በየትኛውም ዘመን፣ በማንኛውም ቦታና ባህል ቆንጆ ናት ማለት ነው፤ ይህን ለማለት ካልደፈርን ግን ስለሴቲቱ ቁንጅና በርግጠኝነት መናገር አልቻልንም ማለት ነው፤ ወይም ቆንጆ አይደለችም እንደማለት ነው፤  ወይም ቁንጅና የሚባል ሃሳብ የለም ማለት ነው፡፡፡ በሌላ በኩል አንድ የሥነ-ጥበብ ወይም የኪነ-ህንጻ ሥራ ያማረ ነው ካልን  በማንኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ዘመንና ባህል ቢመዘን እኩል ውብ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው፡፡
ሁሉን አቀፍ ፈላስፎች ውበት በአጠቃላይ የራሱ የሆነ አለምአቀፋዊ መለኪያ መስፈርት ያለው ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ይቀበላሉ እንጂ ስለመስፈርቱ ምንነት ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የሁሉን አቀፍ እምነት አራማጆች ማሳመኛ የማንኛውንም ነገር ውበት መለኪያ አመክኗዊ መስፈርቶች ሥርዓት (harmony)፣ ጆሜትሪያዊነትና (geometricness)፣ ወደረኝነት (proportionality) ናቸው፡፡ ለምሳሌ የህንጻ ግንባታ ተጠናቆ እንደተረከብክ የዋናውን መኝታ ክፍል ውበት ገምግመህ አስተያየት እንድትሰጥ ብትጠየቅ በጂኦሜትያዊነትና በወደረኝነት ቀመር የክፍሉ የወለል ስፋት ከጣራው ቁመት ጋር ወደረኛ ከሆነ፣ የክፍሉ ግድግዳዎች እንዲሁም በሮቹና መስኮቶቹ አንድ የታወቀ ጆኦሜትሪያዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ተደርጎ ከሆነ፣ እንዲሁም በሥርኣት መርህ ክፍሉ የተቀባው ቀለም ከተገነባበት ዓላማና የብርሃን ጽምረት እንጻር በተገቢው መንገድ ተመርጦ ከሆነ የሚያምር ክፍል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ግለሰብ የግንባሩ፣ የዓይኑ፣ የአፍንጫው ወይም የከንፈሩ መጠን ከጠቅላላው የፊቱ ስፋት ጋር፤ እንዲሁም ቁመቱ ከክብደቱ ጋር ወደረኛ ከሆነ፤ የአካል ክፍሎቹ አቀማመጥ ጂኦሜትሪካል ከሆኑና በአጠቃላይ የሰውነት ክፍሎቹ በተለመደው ተፈጥሯዊ ሥርኣት ከተደረደሩ ቆንጆ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከነዚህ ባሻገር በተለይ እንደ ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ፊልም፣ ቲያትር፣ ሙዚቃ የመሳሰሉት የጥበብ ስራዎችን ለመገምገም መጠቀም ስለሚገባን መስፈርት ከጥበብ ስራዎቹ በአፍአ የሚገኝን ተመልካቾችና አድማጮች ስሜትና አመክኗዊ ግብረ መልስ መሆን እንዳለበት ይሞግታሉ፤ሌሎች የዘርፉ ምሁራን፡፡ የጥበብ ስራው ከሚሰጠው ተዝናኖታዊ ወይም አስተምህሮታዊ ፋይዳ፣ ከስራው ወጥነት (originality)፣ የራስን ማንነትን ከማንጸባረቅ ወይም አዳዲስ ስልት ከማስተዋወቅ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ድምጻዊ ጥላሁን የተጫወተውን ዜማ ድምጻዊት ዘሪቱ አስመስላ በድጋሚ ብትጫወተው የዘፈኑን ውበት መለካት የሚገባን በአዘፋፈናቸው ብቃት፤ ወይስ ከስራው ቅጂነትና ወጥነት አንጻር ነው የሚለውም ሌላው የሁሉን አቀፎች ርዕዮተ ኣለም መገለጫ ነው፡፡             
ሃሳባውያን (idealist) ፈላስፎች በሁሉን አቀፎች አስተሳሰብ ከሚመሩ ሊቃውንት ይመደባሉ፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋና የሂሳብ ሊቅ ፓይታጎረስ በዓለማችን ላይ ሥርዓትንና (harmony ወደረኛነትን (proportionality) ለመሳሰሉ ሃሳቦች መሰረታቸው ቁጥሮች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በዚህም ሙዚቃዊ ውበት በቁጥር ፍልስፍና ውስጥ እንደሚገለጽ በተለያየ መንገድ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ለምሳሌ አንጥረኛው የጋለውን ብረት በመዶሻ ሲደበድበው የሚሰማው ድምጽ በቁጥሮች ቀመር ከተደረደረ ከመዶሻው ክብደት ጋር ተዋህዶ የሚወጣው ድምጽ ጣዕም ያለው ሙዚቃዊ ቃና ሊኖረው እንደሚችል ማለት ነው፡፡
ሌላው የፓይታጎረስ ተከታይ ፕሌቶ በዚህ ዓለም የሚገኙና በስሜት ህዋሳቶቻችን በምናገኘው መረጃ የምንገነዘባቸው ነገሮች በሙሉ በአወቃቀራቸው ግዙፋን፣ ህጸጽ ያለባቸው፣ የሚለዋወጡ፣ የሚከፋፈሉና የተለያዩ ስለሆኑ የውበትን እውነተኛ ምንነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም ይላል፡፡ በሌላ በኩል በሃሳባዊው ዓለም የሚገኙ ነገሮች (Form) ረቂቃን፣ የማይለዋወጡ፣ የማይከፋፈሉ፣ ምንም ህጸጽ የሌለባቸውና ፍጹማን ስለሆኑ የሚታዩና የሚጨበጡ ግዙፋን ነገሮች እውነተኛ ውበት የሚታወቀው በረቂቁ ሃሳባዊ ዓለም (ideal world) ካላቸው ምስል ጋር በማነጻጸር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው የሥጋና የነፍስ ውሁድ ስለሆነ የአንድ ሰው የሥጋ ውበት የሚታወቀው የግለሰቡ ነፍስ ባህርይን ከሥጋው ማንነት ጋር በማነጻጸር በሚገኝ መስተጋብር ነው፡፡ አንድ የክብ (circle) ስዕል ቆንጆ ክበብ ነው የምንለው ስዕሉ በሃሳባችን ውስጥ ከሚገኘው ፍጹም እውነተኛ ክብ ስዕል ጋር ከሚኖረው ቅርበት አንጻር ነው፡፡
የአስራ ሰባተኛው ክፍለዘመን ጀርመናዊ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት ውበትን ከሥነ-ምግባር ጋር ያያይዘዋል “Beauty is a symbol of morality” ይላል:: ካንት በሥነ-ምግባር ፍልስፍናው ውስጥ በሚመራበት የcategorical imperative መርህ እንደ ስነ-ምግባር ጽንጸሃሳቦች ሁሉ ውበት መለካት ያለበት በአንድ ማህበረሰብ ውስት በሚያስከትለው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሳይሆን በራሱ ብቻ (as an end) ነው ይላል፡፡ ይህም ማለት ውበት  የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት የሚያግባባ የጋራ ቋንቋ እንጂ እንደማህበረሰቡ ስሜት የሚፈስ ጅረት አይደለም ማለት ነው፡፡ በፀሀይ ግባት ወቅት አድማስ ላይ የሚፈጠረው ውበት (sunset) በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ዘንድ በጋራ ሊደነቅ የሚችል የተፈጥሮ ውበት ሲሆን ከዚህም የሚገኘው ደስታ በራሱ የመጨረሻ የእርካታ ምንጭ (end) ነው እንጂ ይሄ ውበት ከማህበረሰብ ሊገኝ ወደሚችል ሌላ ደስታ የሚመራ መንገድ (means) አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ተረከዙ በጣም ረጅም የሆነ (heel) “ቆንጆ”፣ ነገር ግን የማይመች፣ ጫማ መጫማቷ ቆንጆ ጫማ አድርጋለች አያስብላትም፡፡ እንደ ካንት እምነት ምክንያቱም በጫማው ልታገኝ ያሰበችውን ደስታ የምታገኘው በቀጥታ ከጫማው ሳይሆን የጫማውን ዋጋ ወይም ማህበራዊ ፋይዳ ከሚገነዘቡ አካላት አድናቆትንና አክብሮትን ለማትረፍ እንደ መንገድ የተጠቀመችነት በመሆኑ ነው፡፡  
ሁለተኛው የሥነ-ውበት ፈላስፎች ጎራ የአንጻራውያን (relativists) ጎራ ይባላል፡፡ ከሁሉን አቀፎች በተቃራኒ አንጻራውያን ውበት የሚለካበት አንድ ወጥ መስፈርት መኖሩን አይቀበሉም፡፡ ይልቁንም “ውበት እንደተመልካቹ ነው” እንደሚባለው ለአንድ ግለሰብ ውብ የሆነው ነገር ለሌላው አስቀያሚ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ ናቸው፡፡ አንጻራውያን ማንም ሰው ቆንጆ ወይም መልከ ጥፉ ሆኖ አይወለድም፡፡ በተፈጥሮ የሚያምር ወይም የሚያስጠላ ፍጡርም ሆነ  የሰው የጥበብ ስራ የለም፡፡ ውበት የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ ነው፡፡ ለምሳሌ የሴት ልጅ ውፍረት በአንዱ ባህል እንደ ውበት ሲቆጠር በሌላው ደግሞ እንደ ውርደት ሲቆጠር አስተውለን ይሆናል፡፡ “ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!” የሚለው የጽሁፌን ርዕስም በአንጻራውያን እይታ ለአንዲት ሴት የጸጉር መርዘም፣ የአፍንጫ መሰልከክ ወይም የወገብ መቅጠን የውበት ምልክት እንደሆነ የነገራት ያደገችበት ማህበረሰብ እንጂ ከማህበረሰቡ ተጽእኖ ውጪ እነዚህ መስፈርቶች ምንም ናቸው የሚለውን ሃሳብ ለማጉላት የመረጥኩት ነው፡፡ በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በፊት ስለውበቱ በሰፊው የተነገረለትና በርካታ ሰዎች የገዙት አንድ ፋሽን ልብስ ወይም ጫማ ዛሬ አስቀያሚና ለመልበስም አሳፋሪ ሆኖ መገኘቱ፤ እንዲሁም  የአንድ ሙዚቃ አልበም ወይም የስነጽሁፍ ሥራ ውበት በተሸጠው ወይም በተሰራጨው የኮፒ ብዛት (best selling) አንጻር መወሰኑ ባለንበት ዘመን ውበት ምን ያህል በማህበረሰቡ  አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር እንደወደቀ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም ውበት ላይ ተመስርተን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት ስለውበት የጠራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል እላለሁ፡፡

Monday, April 22, 2013

ፍልስፍና አፈንጋጭነትና እብደት!


መቼም ፍልስፍና እንደሚባለው ቃል በበጎም ሆነ በክፉ በተደጋጋሚ የሚነሳ የጥበብ ዘርፍ አይኖርም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፍልስፍናን አንዳንዶች  ከእብደት ጋር፣ ሌሎች ደግሞ ከአፈንጋጭነት ጋር በቀጥታ ያያይዙታል፡፡ በርግጥ ፍልስፍናዊ አፈንጋጭነት ከማህበረሰብ ፍልስፍና ተለይቶ በግለሰባዊ ፍልስፍና የመመራት ውጤትና መገለጫ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ “በብዙ እብዶች መካከል የሚገኝ እንድ ጤነኛ እንደ እብድ ይቆጠራል!” እንዲሉ፤ ብዙዎች የአንድን ጉዳይ ትክክለኝነት በአመክንዮ ሳያረጋግጡ በስሜት፣ በሃማኖታዊ አስተሳሰብና በማህበረሰብ ፍልስፍና ብቻ ተነድተው እውነት ነው ብለው የተቀበሉትን ጉዳይ በግለሰባዊ አመክኗዊ ፍልስፍና የሚመራው ፈላስፋ ሀሰት መሆኑን ገልጾ በመቃወም ራሱ የሚያምንበትን ፍልስፍና ማራመዱን የሙጥኝ ካለ እንደ እብድ መቆጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ በርግጥም በፍልስፍና ታሪክ የምናውቃቸው ታላላቅ የዓለማችን ፈላስፎች በራሳቸው መስተሃልይ በመመራት በኖሩበት ዘመን በነበረው ማኅበረሰብ ያልታሰበውን ቀድመው በማሰባቸውና በጭፍን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ቱባ ማህበረሰባዊ እሴት መሰረት በማናጋታቸው አፈንጋጭና እብድ ተብለዋል፤ ከማህበረሰቡ ተገልለዋል፣ ከቀዬያቸው ተሰደዋል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፤ በመርዝም እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ፍልስፍና አፈንጋጭነትና እብደት ከፍልስፍና ጋር የሚገናኙበት መንገድ ቢኖርም ፍልስፍናን፣ አፈንጋጭነትንና እብደትን አንድና ተመሳሳይ አድርጎ መውሰድ ጉልህ ስህተትን መፈጸም ይሆናል፡፡ ብዙዎች ይህን ስህተት የሚፈጽሙት ደግሞ ስለፍልስፍና ምንነት ያላቸው ግንዛቤ በመዛባቱ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው በዛሬው ጽሁፌ ስለፍልስፍና ትክክለኛውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የወሰንኩት፡፡  
ፍልስፍና ያለምንም ውጪያዊ ግፊት በግለሰቡ ውስጣዊ ተነሳሽነት (Curiosity) ብቻ ገንፍሎ የሚወጣ ተፈጥሮአዊ የእውቀት ጥማት ወይም ጉጉት ነው፡፡ ይህም ስለ ራስ ማንነትና ምንነት፣ ስለ ዓለም አፈጣጠር፣ ስለ ውበት፣ ስለእውቀት፣ በአጠቃላይ የሰው መስተሃልይ (mind) ስለሚያመላልሳቸው የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ህልውና፣ አመጣጥ፣ ምንነት፣ አሰራርና ፍጻሜ የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚደረግ ውስጣዊ ትግል ነው፡፡
ይህ ውስጣዊ ትግል የቀለም፣ የዘር ወይም የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበው አእምሮ በተሰጣቸው የሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንም ዑደት ከህጻናት ባህርይ መረዳት  ይቻላል፡፡ የማህበረሰቡን ወግና ባህል ጠንቅቀው የማያውቁ ህጻናት አእምሮአቸው ውስጥ የሚመላለሰውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ካላቸው የተነሳ ብቻ ያለምንም ፍርሃትና ይሉኝታ አውጥተው እንደሚጠይቁ ሁሉ ፍልስፍናን የህይወታቸው መንገድ ያደረጉ ግለሰቦችም ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ፣ የባህል ወይም የሃይማኖት አስተሳሰብ ሳይገድባቸው ነጻ ሆነው አእምሮአቸው ላቀረበላቸውን ጥያቄ የመጨረሻውን እውነተኛ መልስ ለማግኘት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ይከፍላሉ፡፡ በሌላ  በኩል የሚነሳባቸውን መሰረታዊ ጥያቄ ዋጋ ቢስ  አድርጎ በማሰብ ወይም ለጥያቄው አንድ የመጨረሻ እውነተኛ መልስ አይኖረውም ብሎ በማመን፣ ወይም ለጥያቄው በተለምዶ የሚሰጠውን ምላሽ እንደ እውነተኛ መልስ በመቁጠር  የተነሳውን ውስጣዊ ጥያቄ ችላ የሚሉ ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙትን የፍልስፍና ዝንባሌ ስለሚያደበዝዙት ወደ ፍልስፍና መንገድ ለመግባት ወይም የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚኖራቸው ጉጉት በእጅጉ አነስተኛ ይሆናል፤ ሲከፋም እንደሰው እስካለማሰብ ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በተፈጥሮ የተገኘን የፍልስፍና ዝንባሌን በፍልስፍና ትምህርት ወይም በልምምድ በማዳበር ላቅ ወዳለ የፍልስፍና ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል፡፡
ፍልስፍና ከሚመልሳቸው መልሶች ይልቅ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ይበልጥኑ  ዋጋ ይኖራቸዋል፡፡ በፍልስፍና ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ በየትኛውም የጥልቀት ደረጃ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ጥያቄዎች ያነሳው ፈላስፋ ጥያቄዎቹን ሙሉ በሙሉ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲመልስ አይገደድም፤ ይልቁን እያንዳንዱ ፈላስፋ ካመላለሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን ሙሉ በሙሉ ሌሎቹን ደግሞ በከፊል በራሱ አተያይ ሊመልስ ወይም ደግሞ አንዱ ፈላስፋ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሌሎች ፈላስፎች ሊመልሷቸው ይችላሉ፡፡
ይሁን እንጂ በፍልስፍና ለሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ ፈላስፋ የተሰጡ መልሶችን የመጨረሻና ብቸኛ እውነት ብለን በእርግጠኝነት ልንቀበል አይገባም፤ የተሰጠውን መልስ እውነትነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥቄዎችን ልናከታትል እንጂ! በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ፍልስፍና በማያቋርጥ የጥያቄዎች ሰንሰለት የተመሰለውና መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች በየዘመናቱ እንደ አዲስ እንዲነሱ ምክንያት የሆነው፡፡
ፍልስፍና ለመሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር (Logic) ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህ ደግሞ አመክንዮ (reason) ነው፡፡ በምክንያታዊነት የሚመራ ሰው የአስተሳሰብ ህጸጽን (Fallacy) ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድና ውሳኔዎቹን ሁሉ በሰላ አስተሳሰብ (critically) መዝኖ ለማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ አቅም ነው ፈላስፎችን ከእውነተኛ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ሃሳብን ወይም ድርጊትን በጭራሽ እንዳይታገሱና በቀጥታም እንዲተቹ የሚያስገድዳቸው፡፡
ልስፍና አንድን እውነት በራሱ ፈትሾ ካልደረሰበት በቀር ፈጽሞ አይቀበልም፡፡ ፍልስፍና ሰዎች ለአንድ ውሳኔ ምክንያት ነው ብለው ያቀረቡትን ሁሉ እንደ ተገቢ ምክንያት ላይወስደው  ይችላል፤  ምክንያቱም ግለሰቦቹ የእውነተኛ አስተሳሰብ ቀመርን የማይከተሉ ከሆነ ድምዳሜያቸው ከስሜታዊነትና ከጋርዮሽ ፍልስፍና ወይም ከይሉኝታ፣ ከባህላዊና ሃይማኖታዊ እስተሳሰቦች ተጽዕኖ ነጻ ላይሆን ስለሚችል ነው፡፡
ፍልስፍና የአንድ ርዕዮተ ዓለም አገልጋይ ሳይሆን ሁሉም ሃሳቦች የሚገለጹበት የጋራ መሳሪያ ነው፡፡ፍልስፍና የራሱ የሆነ አንድ አቋም (position) የለውም:: በዚህም ምክንያት ፍልስፍና የራሱን ሳይሆን የተጠቃሚውን ግለሰብ የእምነት ፈለግ ተከትሎ በምክንያታዊነት ብርሃን እየተመራ የሚጓዝ ብርቱ የሃሳብ ባቡር ነው፡፡ ለምሳሌ ስለዓለማትና በውስጣቸው ስለያዟቸው ነገሮች ምንነትና የትመጣነት ዙሪያ የሚነሱ ዲበአካላዊ (metaphysical) ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ የተለያየ ዓይነት እምነት ያላቸው ፈላስፎች ሁሉም ፍልስፍናን የሃሳባቸው ማስኬጃ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ እንደ  ቶማስ አኳይናስና፣ቅዱስ ኦገስቲንና አንሰልምና ፓሊ የመሳሰሉ የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች በፈጣሪ ህልውና የሚያምኑ (Theist) ፈላስፎች ሲሆኑ ለዝች ዓለም ፈጣሪ፣ አስገኚ፣ መጋቢ አላት የሚለውን እምነታቸውን ትክክለናነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን ተገልግለውበታል፤ የነርሱ ተከታዮችም እንዲሁ፡፡ በተቃራኒው በፈጣሪ መኖር የማያምኑ (Atheist) አቋም ያላቸው ፈላስፎችም ሆኑ የፈጣሪ መኖርም ሆነ አለመኖር ሊታወቅ ወይም ሊረጋገጥ አይችልም የሚል እምነት ያላቸው ግኖስቲክ (Agnostic)  ፈላስፎች የዚሁ እምነታቸውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን በተመሳሳይ ሁኔታ ይገለገሉበታል፡፡
ፍልስፍና ለሚያጠነጥንበት ርዕሰ ጉዳይ ወሰን ወይም ድንበር (boundry) የለውም፡፡ ፍልስፍና በሁሉም የጥበብና የዕውቀት ዘርፎች ውስጥ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡ ከልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎች ቀዳሚ እንደመሆኑ መጠን ፍልስፍና ለሌሎች ዘርፎች መነሻ ወይም አባት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍልስፍና መነሻ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የእውቀትና የጥበብ ዘርፎች እንዲዳብሩ፣ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚኮተኩት፤ ለሁሉም በሚሰጠው የሰላ ትችት ዘርፎቹ ድክመቶቻተውን እንዲመለከቱና ለተሻለ እውነት እንዲተጉ የሚቀሰቅስ ንቁ አሰልጣኝ ነው፡፡ በተጨማሪም ፍልስፍና ባሉት መሰረታዊና ተግባራዊ ቅርንጫፎች ማለትም በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስ፣ በኪነጥበብ፣ በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በባህል፣ በስነምግባር፣ በስነውበት፣ በለውጥ (በልማት) እንዲሁም  በሞትና ህይወት ወዘተ ላይ ለየት ያሉና እጅግ ጠቃሚ ጥታቄዎችን የሚያነሳና አዲስ ዓይነት ምልከታ እንዲኖራቸው የሚቆሰቁስ ነው፡፡
ምንም እንኳ ፍልስፍና ግላዊ አስተሳሰብ ነው የሚለው ሃሳብ በፍልስፍና ባለቤትነት ላይ የበላይነት የሚኖረው ቢሆንም ፍልስፍና ሁልጊዜ ግላዊ ነው የሚል መደምደሚ ላይ መድረስ ግን ስህተት ይሆናል፡፡ የአንድ ሰው የግል ፍልስፍና በጊዜ ሂደት ተቋማዊ ወይም ማህበረሰባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ዲሞክራሲ ካፒታሊዝምና ሲሻሊዝም ያሉ በርካታ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናዎች መነሻ ምንጮቻቸው ግላዊ ፍልስፍና (individualistic Philosophy) ሲሆን ባለንበት ወቅት ግን ሀገራዊ ወይም ማህበረሰባዊ ፍልስፍናዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ወርቃማው ህግን የሚመስሉ የስነ-ምግባር ፍልስፍናዎች መነሻቸው ሃይማኖት ወይም ባህል (Communal Philosophy) ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ፍልስፍና አስተሳሰብ ነው በሚል የፍልስፍናን ትርጉም አስፍተው በመመልከት የማንኛውም ግለሰብ፣ ተቋም ወይም ማህበረሰብ አስተሳሰብ፣ እምነት (belief)፣ እሴት (value) ሁሉ ፍልስፍና ነው ሲሉ ይደመጠሉ፡፡ ይሁንና በበርካታ ግለሰቦች፣ ተቋምና በማህበረሰብ ውስጥ ያለው ፍልስፍና በቡድን እምነት (dogma) ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ በመሆኑ በሰላ አስተሳሰብና በምክንያታዊነት  ሚዛን ያልተቃኘ እንዲሁም ለትችት ዝግ የሆነ ነው፡፡ ለትችት ወይም ለለውጥ ክፍት ያልሆነ አስተሳሰብ ደግሞ የፍልስፍና ዋነኛ መገለጫዎች ስለማይታዩበት መደቡ ከፍልስፍና ወገን አይደለም ማለት ነው፡፡
ፍልስፍና ፍልስፍናን በትምህርት ቤት ገብተው በተማሩ ባለሙያዎች (professional philosophers) ወይም በተፈጥሮ ብርቱ የፍልስፍና ዝንባሌ ባላቸው ግለሰቦች ሊካሄድ ይችላል፡፡
በመጨረሻም አንድን የጥበብ ስራ ፍልስፍና ነው ለማለት ከሚያበቁን መስፈርቶች አንዱ ፍልስፍናው በጹሁፍ መቅረቡ ነው የሚል የሙግት ነጥብ ይዘው የሚቀርቡ ሰወች አይጠፉም፡፡ ይሁንና ፍልስፍና በጽሁፍ ወይም በቃል ሊቀርብ እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡
እንደ ኢትዮጽያ ባሉ  ባህላቸው ሃማኖታዊ እሴቱ የሚያመዝንባቸው ወይም የስነ-ጽሁፍ ባህላቸው ያልዳበረ ሃገሮች የግለሰቦችን ፍልስፍና በጽሁፍ የማስቀረት ባህላቸው በእጅጉ ደካማ በመሆኑ በርካታ ፍልስፍናቸው በቃላዊ በቅኔ፣ በተረት፣ በዘይቤ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በወጎች እና በመሳሰሉት የሥነ-ቃል ዘርፎች አማካኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላል ኖሯል፤ ይተላላፋልም፡፡ በዚህም የተነሳ ነው በእንደዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ በርካታ ፍልስፍናዎች የጋርዮሽ (communal) መስለው የሚታዩት ወይም መጀመሪያ ፍልስፍናውን ያመነጨው ግለሰብ ማንነት የማይታወቀው፡፡
ግለሰባዊ የስነ-ጸሁፍ ባህላቸው በእጅጉ ከዳበረ ማህበረሰብ ውስጥ የወጡ ፈላስፎች ሃሳባቸውን በቀጥታ በጽሁፍ ሊያሰፍሩ ካልሆነም ተማሪዎቻቸውና ተከታዮቻቸው ፍልስፍናቸውን በፈላስፎቹ ስም ጽፈው እንዲተላለፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡