Saturday, March 21, 2015

…ቅጠል በጣሾች

“ስር ማሽ ቅጠል በጣሽ” የሚለው የአማርኛ አነጋገር ባህላዊ የመድኃኒት ቀማሚዎችን በአሉታ ለመግለጽ ያገለግል የነገረ ሐረግ ሲሆን በርካታ የሙያው ባለቤቶችን አንገት ያስደፋ ሐረግ ነው፡፡ በዚህ ዓምድ “…ቅጠል በጣሾች”  በሚል ርዕስ በተከታታይ የሚቀርበው ጽሁፍ በዘመናዊነት ሰበብ የናቅናቸው፤ የጣልናቸው፣ ያቃጠልናቸው፣ ወይም በየዋህነት ለባዕድ አሳልፈን የሰጠናቸው መንፈሳዊ ጥበባችንና ቁሳዊ የህክምና መጻህፍቶቻችንን ምንነትና የሚዳስስ፤ ስለ ባህላዊ የመድኃኒት ቀማሚዎች ማንነት እንድናውቅ፤ እንዲሁም ጥበቡን በማጥናት እንዴት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ማዋሃድ እንደሚቻል፣  ከእጽዋቱ መድሃኒቶችን በመቀመም ማህበራዊና ምጣኔ-ሀብታዊ ዕድገታችንን እንዴት ማፋጠን እንደሚቻልና ባህላዊ የህክምና ጥበቡን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ጥቆማ የሚሰጥ ነው፡፡
ባህላዊ የህክምና ጥበብ በበርካታ የዓለማችን ሃገሮች፤ በተለይም የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት በሆኑ እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ግብጽ፣  ኢትዮጵያና መካከለኛው ምስራቅና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ካላት ልዩ ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና  የአየር ንብረት ሳቢያ በዓለም ከሚገኙ የዕጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች (flora & fauna) አብዛኞቹን በመያዝ ትታወቃለች፡፡ ይህም ለጥንታዊ የባህል ህክምና መሰረት የሆኑ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎችንና የመድሃኒት ዕጽዋት ዝርያዎች (trees & herbs) ባለቤት ለመሆን አብቅቷታል፡፡ ቀደምት ኢትጵያውያንም በእነዚህ የዕጽዋት ዝርያዎች፣ በእንስሳትና በልዩ ልዩ ማዕድናት ላይ እንደ ዘመናቸው የሥልጣኔ ደረጃ ምርምር በማድረግ ለዛሬው ትውልድ የደረሱና ለሚቀትለው ትውልድ ለተላለፉ የሚገቡ በርካታ መድኃኒቶችን ቀምመዋል፤ በዘመናቸው የነበሩ ዜጎችን ከልዩ ልዩ በሽታዎችንም ሲፈውሱና ለህሙማን እፎይታን ሲሰጡ ኖረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባህላዊ የህክምና ጥበብ በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ ከመግባቱ አንጻር ታሪክ ብቻ ሳይሆን ነባራዊ እውነታም ነው፡፡ ዘመናዊ የህክምና ሳይንስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበትና ባህላዊ ህክምናችንም ተፎካካሪ ከመጣበት ከ1890ዎቹ ጀምሮ ምንም እንኳ ዘመናዊ ሳይንስ የባህላዊ ጥበብ ተቃራኒ ተደርጎ የመገለል፣ የመናቅ፣ የመረሳት ፈተና ቢያጋጥመውም ጫናውን ተቋቁሞ እስከ ዛሬ ድረስ  በድርጊት ለመቆየት በቅቷል፡፡ በርግጥ ጥንታዊ የህክምና ጥበቡ መናቁ መዋረዱና የዘመናዊ ሳይንስ ተቃራኒ ተደርጎ መወሰዱ በሁለት ምክንያቶች ነበር፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የጥንት ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ (transcendental) የህክምና ፍልስፍና ከዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ኢ-መንፈሳዊ (pragmatic) ፍልስፍና የተለየ በመሆኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ በጥንት ኢትዮጵያውያን የህክምና ፍልስፍና መሰረት መድኃኒት የሚለው ቃል ሥጋን፣ ነፍስንና መንፈስን ማዳንን የሚመለከት ቃል ነው፡፡ ይህም ከልዩ ልዩ የሥጋ ደዌያት የሚፈውስ፣ ከመንፈስ ጭንቀት የሚያላቅቅና ከነፍስ በሽታ ከኃጢአት የሚያድን በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በዚህ ፍልስፍና መሰረት መገለጫቸው ቫይረስም ይሁን ባክቴሪያ የበሽታዎች ሁሉ ምክንያት አጋንንት ተደርገው መወሰዳቸውና፤  ለዚህም መፍትሄው የተለያዩ ጸሎቶች (የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና የህቡዕ ስሞች (አስማቶች)) መሆናቸውን ማስተማሩ የዘመናዊ ሳይንስ ተጻራሪ ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል፡
ይሁንና ከጸሎቱና ከድግምቱ (incantations) በተጨማሪ ማንኛውንም በሽታ ለመፈወስ “ዕፅ ይቀትል ወዕፅ የሃዩ” “ዕፅ ይገድላል ዕፅ ያድናል” በሚለው የአበው ብሂል መሰረት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ከሚገኙ ዕፅዋት (trees & herbs) ክፍሎት (ቅጠል፣ አበባ፣ ግንድ፣ ቅርፊት ወይም ስር) አወጣጥቶ በመቀመም ለበርካታ በሽታዎች መድኃኒት ማዘጋጀት ከመቻላቸው ባሻገር ይህንኑ ጥበብ ዕፀ ደብዳቤ በተባሉት ጽሁፎቻቸው ከትበው በማቆየት ለዛሬው ሳይንስ መሰረት እንደጣሉልን ልንዘነጋው አይገባም፡፡
ይልቁንም የጥንት ኢትዮጵያውያን የህክምና ጥበብ በጥልቀት ሲመረመር የዘመናዊ ሳይንስ ተቃራኒ ሳይሆን ሳይንስንና ሃይማኖትን ያዋሃደ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም በአንድ በኩል የበሽታዎቹም ሆነ የመድኃኒቶቹ ባለቤትነት ለአንድ ላዕላ ተፈጥሮ ላለው አካል መሰጠቱ ሃማኖታዊነቱን ሲያሳይ በሌላ በኩል ደግሞ መድኃኒቶቹ የሚቀመሙት በተፈጥሮ ከሚገኙ ዕፅዋት፣ እንስሳትና ማዕድናት መሆናቸው ሳይንሳዊነቱን ያመላክታል፡፡ 
ይህን የዕፅዋት መድኃኒት ዝርዝር የያዙ ጥንታዊ ጽሁፍ ዕፀ ደብዳቤ treatise of therapeutics በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህም በዘመናዊው የሳይንስ Ethno-pharmacopeia ወይም pharmacopeia በሚል የሚጠራው ነው፡፡ ጥንታዊውያን የዕፀ ደብዳቤ ጽሁፎች ለዘመናዊው የህክምና ሳይንስ የዕፅዋት የመድሃኒት ዐቢይ ንጥረ ነገር (active ingridient) ቅመማ ጥናት ፋርማኮግኖሲ (Pharmacognosy) መሰረት ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ስለእነዚህ ጥንታዊ ጽሁፎች ይዘት፣ አሰራርና እምቅ አቅምና ማብራራትና ለዛሬው ዘመን የሚጠቅሙንን እሴቶችና ጥበቦች እንድንለይ በጥናት የተደገፈ መረጃ መስጠት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በባለመድኃኒትነት የሚታወቁ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢኖሩም ለሳይንስ መሰረት የሆኑ መጽሐፈ መድኃኒቶቹን የፃፏቸው ግን ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው በርካታ ጽሁፎችን ለዛሬው ትውልድ የማቆየት ጥበብን የተላበሱት ጸሐፍት አባቶች ሲሆኑ በተለይ በዚህ ረገድ ደብተራዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ጽሁፌም በእነዚሁ መጻህፍትና ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ህክምና ከመስፋፋቱ በፊት የህክምና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩና በመስጠት ላይ የሚገኙ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በህክምና ዕውቀታቸው ስፋት፣ የመፈወስ ኃይሉን ከሚያገኙበት ምንጭና ከሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ዓይነት አንጻር በአምስት ይከፈላሉ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በመኖሪያ ቤት ወይም በስራ ቦታ አካባቢ የሚገኙ በቅርበት የሚገኝ ማናቸውም የሃይማኖት ሰው (Any Clergy) ማለትም ቄስ፣ አጥማቂ፣ ዲያቆን ሼህ ወይም ሃይማኖቱን በሚገባ የሚውቅ ምዕመን በመጀመሪ ደረጃ የህክምና ዕርዳታ ሰጪነት ይታወቃል፡፡ ይህም ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይህ ሰው በሽታውን አመጣ ተብሎ የሚታመነውን ስውር ሓይል በማስወገድ ታማሚውን ለመፈወስ ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን ጸሎት በማድረግ ግለሰቡን ለመርዳት ይሞክራል፡፡ ይህ ደረጃ በባህላዊ ህክምና የተራቀቁ ደብተራዎችን ወይም ሼሆችን አይጨምርም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ  የምናገኘው ባለመድኃኒት ባለዛር፣ ባለውቃቢ ወይም ጠንቅዋይ በመባል ታወቃል፡፡ ባለዛር የመፈወስ ኃይሉን የሚያገኘው ከቤተሰብ ወይም ከጎሳ መሪዎች በሚወረስ የዛር (የዛር ውላጅ) መንፈስ ሲሆን የዚህ ፈውስ ተቋዳሾችም በዚሁ መንፈስ የሚያምኑና ለመንፈሱም የሚገባውን መስዋዕት የሚያቀርቡ ወይም ቆሌዋን የሚለማመኑ ተከታዮችና ቤተሰቦች ብቻ ናቸው፡፡
ሶስተኛው የኢትዮጵያ ባለመድኃኒት የህብረተሰብ ክፍሎች ምድብ ወጌሻዎችን፣ የልምድ አዋላጆችን፣ ባህላዊ የጥርስ ሃኪሞችን፣ ገራዦችንና ዋግምት ሰሪዎችን የሚያካትተው ሲሆን (Secular Non-herbal Healers) እነዚህም የህክምና ሙያውን ያገኙት ከቀደምት ባለሙያዎች ከማየትና አብሮ በመስራት እንጂ ከዛር መንፈስ ጋርም ሆነ ከጸሎት ጋር በተገናኘ መንገድ አይደለም፡፡ ባለሙያዎቹ በስራዎቻቸው ላይ በአነስተኛ ደረጃ የቅጠላቅጠል መድኃኒትን ይጠቀሙ እንጂ በዋነኝነት ባህላዊ የቅጠላቅጠል መድኃኒት ቅመማ ስራ የተካኑ አይደሉም፡፡
አራተኞቹ የመድኃኒት አዋቂዎች በገጠር የሚኖሩና በሙያቸውም ገበሬዎች (Rural Herbalist) ናቸው፡፡ እነዚህ ባለመድኃኒቶች ከሁለት እስከ ሶስት ዓይነት መድሃኒቶችን በህይወታቸው  ልምድ አጋጣሚ በማካበት ያገኙ ሲሆን እነርሱም በጎረቤትና በቀዬአቸው ዘንድ ለተጠቀሱት በሽታዎች መድሓኒት አዋቂነታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡
የመጨረሻዎቹ ደብተራዎችና ሼሆች የሚገኙበት ምድብ ሲሆን እስካሁን ከተዘረዘሩት ሁሉ በመድኃኒት አዋቂነታቸው የላቀውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በጥንታዊ የህክምና መጻህፍቶቻችን በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋ ተጽፈው የሚገኙ ቢሆንም በዚህ ጽሁፌ የምዳስሰው  በግዕዝና በአማርኛ ተጽፈው የሚገኙትን ብቻ ይሆናል፡፡ ደብተራ የሚለው ቃል በብዙዎች ዘንድ አሉታዊ ስሜትን ያዘለና በዘይቤ ረቀቅ ያለ ሃይማኖታዊ ምስጢር ያለው ቢሆንም ተግባራዊ ብያኔው ግን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የቅኔ፣ የዜማና የዝማሜ ሊቅነትን፣ የአብነት መምህርነትን፣ የቁም ጽህፈት ባለሙያነትን አልፎ አልፎም ባህላዊ የቅጠላ ቅጠል መድኃኒት ቀማሚነትን  የሚያመላክት ሙያዊ መጠሪያ ነው፡፡ እንደ ተመራማሪው ያንግ (Young, A) ጥናት ደብተራዎች የመድኃኒት ዕውቀታቸውን ከሚያገኙበት ምንጭ አንጻር ትንሽ ደብተራና ጋኔን-ሳቢ ደብተራ በሚል በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ትንሽ ደብተራዎች የቅጠላ-ቅጠል መድኃኒት እውቀታቸውን በተግባር ከወላጅ አባታቸው ወይም ከመምህራቸው አንድ ለአንድ በሆነ ኢ-መደበኛ የሰርዓተ-ትምህርት በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የተማሩት ሲሆን ጋኔን-ሳቢ ደብተራ በመባል የሚታወቁት ደግሞ ከተለዩ አጋንንት ጋር በሚያደርጉት ቁርኝትና ቃል-ኪዳን አማካኝነት ከአጋንንት በሚያገኙት ኃይል ፈውስንና ድንቃ-ድንቅ ተዓምራትን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት በቅጠላ-ቅጠል መድኃኒት ቅመማ የተሰማሩ ትንሽም ሆነ ጋኔን-ሳቢ ደብተራዎች ከቤተክርስቲያን አገልግሎት የተለዩ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጥበቡን አውቃለሁ ወይም የህክምና መጻህፍቱ አሉኝ የሚሉ ሰወችን በአደባባይ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ጥበቡ ላይ ጥናትና ምርምር አድርጎ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚፈልጉ ምሁራን የአንዳንድ ባለመድኃኒቶችን እጅ ማየት ወይም በሀገር ውስጥና በውጪ ሃገር የሚገኙ ሙዚየሞችንና ቤተ-መዛግብቶችን የሙጥኝ ማለት ግድ ሆናባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment