የፊታችን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበትን
50ኛ ዓመት በዓል በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ለማክበር ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በ1960ዎቹ የጋናውያን ፕሬዚደንት
የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ከአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካውያን ወንድማማችነት
ለማረጋገጥ “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ” (USA) በሚል መጠሪያ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ያልተሳካ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡
የኋላ ኋላ ንክሩማህ የዘራው ዘር በመሰሎቹ የነጻ አፍሪካ የወቅቱ መሪዎችና ምሁራን ጆሞ ኬንያታ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ሌኦፖልድ ሴንጎር፣
ዊልሞት ብሊደንና አብዱላዬ ዋዴ ትጋት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጽያዊው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ግንቦት 25 ቀን 1963ዓ.ም ስፖንሰር
ባደረጉትና በአዲስ አበባ በተካሄደው የፓን አፍሪካን ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) ለመውለድ በቅቷል፡፡ ውሎ
አድሮም ይኸው ድርጅት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) በሚል ተሰይሟል፡፡
ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት መነሻቸው የፓን አፍሪካን
ፍልስፍና መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ፓን አፍሪካ ፍልስፍና ምንድነው? መቼ ተጀመረ? ለምን? ዛሬ ፍልስፍናው ምን
ደረጃ ላይ ይገኛል? ለነገይቱ አፍሪካስ ምን ተስፋ ይኖረዋል? የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይሆናል፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ህዝቦችን የሚጋሯቸውና የሚያስተሳስሯቸው የጋራ
ጉዳዮችና ዓላማዎች አሏቸው፣ እነዚህንም ለማሳካት አፍሪካውያን በአንድነትና በኅብረት መስራት ይኖርባቸዋል የሚል እምነት ላይ የተመሰረተ
የአፍሪካውያን ፍልስፍና ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና በመላው
የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች፣ ከአፍሪካ ውጪ የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚኖሩ ነጭም ሆነ ጥቁር ህዝቦች
ያራመዷቸውን ሃሳቦችና ለተፈጻሚነቱ የከፈሉለትን መስዋዕትነትና በአሁኑ ወቅት የሚራመደውን መሰል ፍልስፍና አጠቃሎ የሚይዝ ሃሳብ
ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም
አፍሪካ በራሷ ነባር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና መመመራት አለባት የሚል እምነትን የሚያራምድ ሲሆን ሁለት
መገለጫዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አህጉራዊ ፓንአፍሪካኒዝም
(continental pan-Africanism) የሚባለው ሲሆን ይህም
በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ሀገሮችና ህዝቦች በፖለቲካና በዓለምአቀፋዊ ትብብር አቅጣጫ በአንድነት መስራት እንደሚገባቸው
የሚያስረግጥ ነው፡፡ ሁለተኛው መገለጫ ዲያስፖራ ፓንአፍሪካኒዝም (Diaspora Pan-Africanism) ይባላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ
በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በባርነትና በስደት ወደሌሎች አህጉራት ተወስደው የሚኖሩ ጥቁር
አፍሪካውያንና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ አፍሪካውያን ዘንድ ወንድማማችነትና ትብብር ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም በወቅቱ በአውሮፓውያን ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድና
የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ለመዋጋትና ከስሩ ገርስሶ ለመጣል ቁርጠኛ ሆነው በተነሱ አፍሪካውያንና ከአህጉሪቱ ተሰደው በጭካኔ፣ በግፍ፣
በአድልዎ አገዛዝ ስር ወድቀው- በአውሮፓና በአሜሪካ አህጉራት ተበታትነው ይኖሩ በነበሩ ትውልደ አፍሪካውያን እልህ የተቀጣጠለ የአፍሪካውያን
ፍልስፍና ፍልስፍናውን ተከትሎ የፈነዳ ንቅናቄ ነው፡፡
ምንም እንኳን የንቅናቄው መስራቾች በዓለም ላይ ተበታትነው የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያንና
በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ምሁራን በመሆናቸው ፍልስፍናውን እውን ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነ ቢረዱትም አፍሪካውያንና ትውልደ አፍሪካውያን
ህብረት መፍጠርና በአንድነት ለመስራት ጥረት ማደረግ ከቻሉ ከግብ አንደሚያደርሱት ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፓን
አፍሪካ ንቅናቄ አራማጅና የምዕራብ አፍሪካ ባህል አስተዋዋቂው ላይቤርያዊው ዊልሞት ብሊደን (Edward Wilmot Blyden)
በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በአስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ፓን አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) የሚለውን መጠሪያ ቃል ለፍልስፍናው
የሰየመውም ብሊደን መሆኑን ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በዘመናዊ መልኩ የቅኝ አገዛዝን በመቃወም የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ በ20ኛው
ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በተደራጀ መልኩ እንደጀመረ የሚነገርለት በካረቢያን ደሴት ውስጥ የህግ ባለሙያ የነበረው ሄንሪ ሲልቬስተር
ዊልያምስ (Henery Sylvester Williams) ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲወያዩ
ለማስቻል በር የከፈተውን የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካ ጉባዔ በለንደን ከተማ ውስጥ ለማዘጋጀት ችሏል፡፡ በዊልያምስ የተጀመረው የፓን
አፍሪካን ጉባኤ በቀጣይም በጥቁር አሜሪካዊው የታሪክና የሥነ-ማህበረሰብ ሊቅ ዱ ቦይስ (W.E.B. Du Bois) አዘጋጅነት በተከታታይ
ተካሂዷል፡፡
በእነ ዱ ቦይስ ጥረት በአሜሪካን ሀገር በተመሰረተው የባለቀለም ህዝቦች
ማጎልበቻ ማህበር (NAACP) እንቅስቃሴና የፓን አፍረካኒዝም ተከታታይ ጉባዔያት ያላሰለሰ ጥረት ሳቢያ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹና
ሰላሳዎቹ አካባቢ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በአሜሪካ በሚኖሩ ጥቁር ህዝቦችና ትውልደ አፍሪካውን ዘንድ ከፍተኛ የባህል መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ በኒዮርክ ከተማ ሀርለም በተባለ
አካባቢ የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን ሀርለም ሬናይሰንስ በሚል የራሳቸውን ነባር ማንነት (Negritiude) የሚያንጸባርቁ እንደ ሙዚቃ ያሉ ኪነጥበባዊ ስራዎችን
በመጠቀም በጥቁርነታቸው የሚሰማቸውን ኩራትና ለመግለጽና በዘርና በቀለም የሚፈጸመውን አድልዎ ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡
በሃገር ቤትም ማልኮም ኤክስን (Malcom X) የመሳሰሉ ዲያስፖራ አፍሪካ ምሁራን በተደጋጋሚ ጉዞ በማድረግ ጥቁር አፍሪካውያን
ለራሳቸው ማንነት ዋጋ እንዲሰጡና በአንድነት መስራት እንዲችሉ ብርቱ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሃገሮች ከቅኝ አገዛዝ
ነጻነት በተጎናጸፉ ማግስትም አንዳንድ የአፍሪካ ምሁራን መሪዎች አፍሪካ ነባር ወደሆነው የራሷን ማንነት መመለስና ከሌሎች የአፍሪካ
ሃገሮች ጋር አንድነት መፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ የታንዛንያው ፕሬዚደንት ጁሊየስ
ኔሬሬ በ1974 ዓ.ም ዳሬ ሰላም ላይ የተካሄደውን ስድስተኛው የፓን አፍሪካን ኮንግረስ ከማዘጋጀቱም ባሻገር በርሱ ዘመን ታንዛንያ የስዋሂሊ ቋንቋን የታንዛንያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል፤ ኡጃማ
(Ujamma) በተባለው የአፍሪካውያን ልዩ የሆነ የሀገር ቤት ሶሻሊዝም ሀገሩን ለማስተዳደር ችሏል፤ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችም በየራሳቸው
ነባር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና እንዲመሩ አስተምሯል፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አዘጋጅነት የዛሬ ሃምሳ ዓመት በወርሃ
ግንቦት 1963ዓ.ም አፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ በተደረገው የፓን አፍሪካ ኮንግረስ ላይ በአፍሪካን ዳያስፖራና በአፍሪካ ምሁራን
መሪዎች ጥረት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) በመውለድ ምናባዊው የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አፍሪካን
አንድ የማድረግን ዓላማ እውን ለማድረግ የመጀመሪው የመወጣጫ ድንጋይ
ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እንደታሰበው አፍሪካን አንድ ለማድረግ አልተሳካለትም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም
የአፍሪካ መሪዎች በሃሳብ መጋጨት የጀመሩት ገና የምስረታ ጉባዔው “ሀ” ተብሎ ሲጀመር “ድርጅቱ ምን ዓይነት መልክ ይኑረው?” በሚለው ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ መሪዎቹ በሁለት ጎራ
ተከፍለዋል፡፡ በእነ ክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የነበሩት ጥቂት የሀገራት መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አፍሪካን አንድ የሚያደርግ
በአንድ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚመራ (United States of Africa) ይሁን የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው ጎራየተሰለፉት ግን
ገና ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ ብዙም ያልቆዩ ሀገራት በመሆናቸውና ውሳኔውን በመቃወማቸው ድርጅቱ በራሱ አነስተኛ ስልጣን ያለው የሃገራቱን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትብብር የሚያጠናክር
ተቋም እንዲሆን በሚል ለመመስረት በቅቷል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
በታንዛንያዊው ሳሊም አህመድ ሳሊም የአመራር ዘመን ድርጅቱ የተመሰረተበትን የአህጉሪቱን የፖለቲካና ኢኮኖሚዊ ግብ ይበልጥ እንዲገልጸውና አህጉሪቱ የሉላዊነትን ተጽዕኖ እንድትወጣ በሚል
ምክንያት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) የሚል አዲስ ስያሜ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ይኸውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
የሚለው መጠሪያ ከቀድሞ የፓን አፍሪካ መስራቾች አፍሪካን አንድ የማድረግ ርዕይ የመነጨ ስለሆነና ድርጅቱ በተግባር እየተከተለ ያለው
ግን አንድ ማድረግ ላይ ሳይሆን መተባበር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ
ስያሜው መቀየር አለበት የሚል ነው፤ የስያሜው መቀየር ያስፈልጋል የሚለው ውሳኔ የፓን አፍሪካን ነባር ፍልስፍና መቀየርና በአዲስ
ፍልስፍና መተካት ያስፈልጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአባል ሃገራቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣
ልማትና ሰላም ላይ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን ከሃምሳ ዓመት በፊት ከተመሰረተበት የፓን አፍሪካን ፍልስፍናና ርዕይ አንጻር ሲመዘን
ግን የሚተችባቸውም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ አፍሪካን እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (USA) በዶላር ወይም እንደ አውሮፓ ህብረት (EU) በዩሮ የሚገበያይ አንድ ጠንካራ፣ ሰላማዊ
የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አልቻለም፡፡ ይልቁንም አባል ሃገራቱ ከዘመን ወደ ዘመን በእርስ በርስ ግጭት ወደ ከመበታተንና
በመነጣጠልና ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? የሰለጠነው የምዕራቡ አህጉር ከዕለት ወደ ዕለት አንድ ወደሚሆንበት ፍልስፍና
ወደፊት ሲፈተለክ አፍሪካውያን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃማኖት፣ በቀለምና በቋንቋ ተከፋፍለን በጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን የኋሊት መፈርጠጣችን
ለምን ይሆን? የፓን አፍሪካ ፍልስፍናስ ለአፍሪካ እድገት አስፈላጊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ትጥቆችን የያዘ ተግባራዊ ፍልስፍና ወይስ
ሊተገበር የማይችል የቀደምት አፍሪካ መሪዎች ህልመኛ (ideal) ፍልስፍና?
በርግጥ አንዳንዶች በተለይም ምዕራባውያን የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና
በተግባር ሊተረጎም የማይችል እንደ ግሪክ ፈላስፋው ፕሌቶ ሃሳባዊ ሪፐብሊክ (Plato’s Ideal Republic) በፍልስፍና ደረጃ
የሚቀር እንጂ በውን የማይተገበር (Utopian Philosophy) ህልመኛ ፍልስፍና ነው በሚል ዝቅተኛ ግምት ሲቸሩትና ከአፍሪካ
ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምህዳር ለማውጣት ብርቱ ጥረት ሲደርጉ ኖረዋል፡፡ ለዚህም አስተሳሰብ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በመጀመሪያ
ፍልስፍናው በቅኝ ገዢዎችና በባርነት አስፋፊዎችን በመቃወም ላይ የተመሰረተ
በመሆኑ ምዕራባውያን ይህን በአወንታ የሚቀበሉት አልነበረም፡፡ ከዚህም ባሻገር በባርነት ስርዓትም ሆነ በቅኝ አገዛዝ ታሪካቸው፣
እንዲሁም ከድህረ ቅኝ ግዛት በኋላ የአፍሪካ ህዝቦች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓታቸው ሰፊ ልዩነት ስነበራቸው ዩናይትድ ስቴትስ
ኦፍ አፍሪካን ለመፍጠር የሚሞከር አልነበረም፡፡ በመጨረሻም አፍሪካውያን በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በፖለቲካዊ
ስርዓት ሰፊ ልዩነት ስላላቸው ይህንን ልዩነት አስታርቆ በአንድነት ለመስራት
እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል የሚል ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አህጉሪቱን
ወደ ዓለምአቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ የሚቀርብበት ሰረገላ ሆኖ አህጉራዊ ፓን አፍሪካኒዝም ባለንበት ዘመን በልዩ ልዩ መልኩ
የአፍሪካን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት በተዋቀሩ እንደ ECOWAS, SADC, EAC በመሳሰሉ ክልላዊ ድርጅቶች
አማካይነት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በእኔ እምነት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና ከዚህም አልፎ አፍሪካውያን
ለራሳቸው ነባር ባህላዊ እሴቶችና ማንነት ቦታ ሰጥተው በነክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደተሰነዘረው ዩናይትድ ስቴትስ
ኦፍ አፍሪካ የአንድነት ደረጃ ላይ እስክትደርስ ድረስ መጓዝ ያለበት
ፍልስፍና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የፍልስፍና ምሁራን፣ የፖለቲካዊ ሳይንስ ሊቃውንትና የአፍሪካ መሪዎች እጅ
ለእጅ ተያይዘው የያኔዎቹ አፍሪካውያን መሪዎችና ምሁራን የያኔዎቹን ቅኝ ገዢዎች ለመዋጋት ክንዶቻቸውን መስተሃልያቸውን
(mind) እንዳስተባበሩ ሁሉ፣ የዛሪዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቻችንን ለመዋጋትና የዛሬ ሃምሳ ዓመት የታሰበውን የፓን አፍሪካ
ርዕይ እውን ለማድረግ ክንዶቻቸውንና መስተሃልያቸውን ማስተባበር አለባቸው እላለሁ፡፡ ያን ጊዜ የድርጅቱ መጠሪያም “ከአፍሪካ ህብረት” ወደ “አፍሪካ አንድነት”
(US Africa) ይመለስ ይሆናል…ማን ያውቃል?!
በጣም ጥሩ አርቲክል ነው። ሆኖም ግን አፍሪካውያን መሪዎች የተባባሩት አፍሪካን ወይም አፍሪካን በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ማስቀመጥ ስልጣን የሚያሳጣቸው መስሎ ስለሚታያቸው የዶክተር ኩዋሜ ንኩሩማን የተባበሩት አፍሪካን የመፍጠር ሃሳብ ይቀበላሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።
ReplyDeleteለዚህ ሃሳብ አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችለው የፖን አፍሪካኒዝም የፍልስፍና አንዱ አካል የሆነው የተባበሩት አፍሪካን የመፍጠር ሃሳብ ትክክለኛውን ግዜ ባላስታውሰውም እዚሁ ሃገራችን ላይ በተደረገ አንድ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የቀድሞ የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ጋዳፊ ከረጅም ዓመታት በኋላ ይህንን ሃሳብ ቢያነሱትም ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም ነው። እንደውም እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ ስልጣናቸውን ከሃገራዊ ወደ አህጉራዊ ሊያሸጋግሩት ፈልገዋል ነው ይህን የሚሉት በሚል አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ማውገዛቸውን አስታውሳለሁ።
ሆኖም ግን በወቅቱ መታየት የነበረበት የጋዳፊ የስልጣን ጥመኝነት ሳይሆን ሃሳቡ አፍሪካን ያሻግራታል ወይ የሚለው ጉዳይ መሆን ነበረበት።
ነገር ግን በዚህ መንገድ ሊረዳው የሚችል የአፍሪካ መሪ ባለመገኘቱ የፓን አፍሪካኒዝም የፍልስፍና አካል የሆነው የጋዳፊ ጥያቄ አየር ላይ ተንሳፎ ቀርቷል።
እርግጥ ነው አንዳንዶቹ ይህ ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን ፍልስፍነው የተናጥል ስልጣን ያሳጣናል ከሚል ስጋት የመነጨ ነው።
ለምሳሌ አፍሪካ 54 ሃገራትን ይዛለች። ይህ ማለት ደግሞ 54 የሃገር መሪዎች አሉ ማለት ነው። በእነዚህ ሃገራት ፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ ስር ደግሞ ምን ያህል የፖለቲካ ጥቅመኞች እንዳሉ እናስብ።
ይህን በድምር ሂሳባዊ ስሌት አስልተን ካስቀመጥን አሁን አፍሪካ በምትከተለው መዋቅር እጅግ በርካቶች የዚህ መዋቅር ተጠቃሚ መሆናቸውን እንገነዘባለን።
ስለሆነም የእነ ዶክተር ኩዋሜ ንኩሩማ የተባበሩት አፍሪካን የመፍጠር ፍልስፍና በአንድ ማዕከላዊ መንግስት መመራትን የሚያስከትል በመሆኑ ቢያንስ ቢያንስ ይህ ፍልስፍና 53 መሪዎችንና በስራቸው ያሉ በርካታ ተከታዮቻቸውን የፖለቲካ ጥቅም የሚያስቀር ነው።
ግን ደግሞ ይህ የፖን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና ለአፍሪካ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጎልበት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው።
ለዚህ ነው መሪዎቻችን ስለ ተባበሩት አፍሪካ ምስረታ መስማት የማይፈልጉት....
በመጨረሻ.....ማስተካከያ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ዶክተር ሳሊም አህመድ ሳሊም ታንዛኒያዊ ሳይሆኑ ቱኒዚያዊ ናቸው። እርግጥ ነው ይህን የመሰለ ድንቅ አርቲክል የፃፈ ባለሞያ ዶክተር ሳሊም አህመድ ሳሊም ቱኒዚያዊ መሆናቸው እንደማይጠፋው እረዳለሁ።
ሆኖም ግን የአፍ ወለምታ እንደሚባለው የእጅ ወለምታ ሳይከሰት አልቀረምና ቢስተካከል ለማለት ነው።
በተረፈ ግን በጣም አመሰግናለሁ። እኔ የስፖርት ጋዜጠኛ ብሆንም እንዲህ አይነት ፅሁፎችን መከታተል በጣም ያስደስተኛል። ምክንያቱም እያንዳንዱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ስፖርቱንም ይነካካሉና......ZERAY EYASUU BEGEJIE