Sunday, May 19, 2013

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ (USA)!


የፊታችን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ለማክበር ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በ1960ዎቹ የጋናውያን ፕሬዚደንት የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ከአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካውያን ወንድማማችነት ለማረጋገጥ “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ” (USA) በሚል መጠሪያ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ያልተሳካ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ንክሩማህ የዘራው ዘር በመሰሎቹ የነጻ አፍሪካ የወቅቱ መሪዎችና ምሁራን ጆሞ ኬንያታ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ሌኦፖልድ ሴንጎር፣ ዊልሞት ብሊደንና አብዱላዬ ዋዴ ትጋት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጽያዊው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ግንቦት 25 ቀን 1963ዓ.ም ስፖንሰር ባደረጉትና በአዲስ አበባ በተካሄደው የፓን አፍሪካን ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) ለመውለድ በቅቷል፡፡ ውሎ አድሮም ይኸው ድርጅት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) በሚል ተሰይሟል፡፡
ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት መነሻቸው የፓን አፍሪካን ፍልስፍና መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ፓን አፍሪካ ፍልስፍና ምንድነው? መቼ ተጀመረ? ለምን? ዛሬ ፍልስፍናው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለነገይቱ አፍሪካስ ምን ተስፋ ይኖረዋል? የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይሆናል፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ህዝቦችን የሚጋሯቸውና የሚያስተሳስሯቸው የጋራ ጉዳዮችና ዓላማዎች አሏቸው፣ እነዚህንም ለማሳካት አፍሪካውያን በአንድነትና በኅብረት መስራት ይኖርባቸዋል የሚል እምነት ላይ የተመሰረተ የአፍሪካውያን ፍልስፍና ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም  ፍልስፍና በመላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች፣ ከአፍሪካ ውጪ የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚኖሩ ነጭም ሆነ ጥቁር ህዝቦች ያራመዷቸውን ሃሳቦችና ለተፈጻሚነቱ የከፈሉለትን መስዋዕትነትና በአሁኑ ወቅት የሚራመደውን መሰል ፍልስፍና አጠቃሎ የሚይዝ ሃሳብ ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም  አፍሪካ በራሷ ነባር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና መመመራት አለባት የሚል እምነትን የሚያራምድ ሲሆን ሁለት መገለጫዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አህጉራዊ  ፓንአፍሪካኒዝም (continental pan-Africanism) የሚባለው ሲሆን ይህም  በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ሀገሮችና ህዝቦች በፖለቲካና በዓለምአቀፋዊ ትብብር አቅጣጫ በአንድነት መስራት እንደሚገባቸው የሚያስረግጥ ነው፡፡ ሁለተኛው መገለጫ ዲያስፖራ ፓንአፍሪካኒዝም (Diaspora Pan-Africanism) ይባላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በባርነትና በስደት ወደሌሎች አህጉራት ተወስደው የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካውያንና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ አፍሪካውያን ዘንድ ወንድማማችነትና ትብብር ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም በወቅቱ በአውሮፓውያን ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድና የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ለመዋጋትና ከስሩ ገርስሶ ለመጣል ቁርጠኛ ሆነው በተነሱ አፍሪካውያንና ከአህጉሪቱ ተሰደው በጭካኔ፣ በግፍ፣ በአድልዎ አገዛዝ ስር ወድቀው- በአውሮፓና በአሜሪካ አህጉራት ተበታትነው ይኖሩ በነበሩ ትውልደ አፍሪካውያን እልህ የተቀጣጠለ የአፍሪካውያን ፍልስፍና ፍልስፍናውን ተከትሎ የፈነዳ ንቅናቄ ነው፡፡
 ምንም እንኳን  የንቅናቄው መስራቾች በዓለም ላይ ተበታትነው የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካውያንና በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ምሁራን በመሆናቸው ፍልስፍናውን እውን ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነ ቢረዱትም አፍሪካውያንና ትውልደ አፍሪካውያን ህብረት መፍጠርና በአንድነት ለመስራት ጥረት ማደረግ ከቻሉ ከግብ አንደሚያደርሱት ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አራማጅና የምዕራብ አፍሪካ ባህል አስተዋዋቂው ላይቤርያዊው ዊልሞት ብሊደን (Edward Wilmot Blyden) በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በአስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ፓን አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) የሚለውን መጠሪያ ቃል ለፍልስፍናው የሰየመውም ብሊደን መሆኑን ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በዘመናዊ መልኩ የቅኝ አገዛዝን በመቃወም የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በተደራጀ መልኩ እንደጀመረ የሚነገርለት በካረቢያን ደሴት ውስጥ የህግ ባለሙያ የነበረው ሄንሪ ሲልቬስተር ዊልያምስ (Henery Sylvester Williams) ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲወያዩ ለማስቻል በር የከፈተውን የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካ ጉባዔ በለንደን ከተማ ውስጥ ለማዘጋጀት ችሏል፡፡ በዊልያምስ የተጀመረው የፓን አፍሪካን ጉባኤ በቀጣይም በጥቁር አሜሪካዊው የታሪክና የሥነ-ማህበረሰብ ሊቅ ዱ ቦይስ (W.E.B. Du Bois) አዘጋጅነት በተከታታይ ተካሂዷል፡፡
በእነ ዱ ቦይስ ጥረት በአሜሪካን ሀገር በተመሰረተው የባለቀለም ህዝቦች ማጎልበቻ ማህበር (NAACP) እንቅስቃሴና የፓን አፍረካኒዝም ተከታታይ ጉባዔያት ያላሰለሰ ጥረት ሳቢያ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹና ሰላሳዎቹ አካባቢ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በአሜሪካ በሚኖሩ ጥቁር ህዝቦችና ትውልደ አፍሪካውን ዘንድ  ከፍተኛ የባህል መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ በኒዮርክ ከተማ ሀርለም በተባለ አካባቢ የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን ሀርለም ሬናይሰንስ በሚል የራሳቸውን ነባር  ማንነት (Negritiude) የሚያንጸባርቁ እንደ ሙዚቃ ያሉ ኪነጥበባዊ ስራዎችን በመጠቀም በጥቁርነታቸው የሚሰማቸውን ኩራትና ለመግለጽና በዘርና በቀለም የሚፈጸመውን አድልዎ ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡ በሃገር ቤትም ማልኮም ኤክስን (Malcom X) የመሳሰሉ ዲያስፖራ አፍሪካ ምሁራን በተደጋጋሚ ጉዞ በማድረግ ጥቁር አፍሪካውያን ለራሳቸው ማንነት ዋጋ እንዲሰጡና በአንድነት መስራት እንዲችሉ ብርቱ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሃገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነጻነት በተጎናጸፉ ማግስትም አንዳንድ የአፍሪካ ምሁራን መሪዎች አፍሪካ ነባር ወደሆነው የራሷን ማንነት መመለስና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ጋር አንድነት መፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ የታንዛንያው ፕሬዚደንት ጁሊየስ ኔሬሬ በ1974 ዓ.ም ዳሬ ሰላም ላይ የተካሄደውን ስድስተኛው የፓን አፍሪካን ኮንግረስ ከማዘጋጀቱም ባሻገር በርሱ ዘመን ታንዛንያ  የስዋሂሊ ቋንቋን የታንዛንያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል፤ ኡጃማ (Ujamma) በተባለው የአፍሪካውያን ልዩ የሆነ የሀገር ቤት ሶሻሊዝም ሀገሩን ለማስተዳደር ችሏል፤ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችም በየራሳቸው ነባር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና እንዲመሩ አስተምሯል፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አዘጋጅነት የዛሬ ሃምሳ ዓመት በወርሃ ግንቦት 1963ዓ.ም አፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ በተደረገው የፓን አፍሪካ ኮንግረስ ላይ በአፍሪካን ዳያስፖራና በአፍሪካ ምሁራን መሪዎች ጥረት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) በመውለድ ምናባዊው የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አፍሪካን አንድ የማድረግን ዓላማ  እውን ለማድረግ የመጀመሪው የመወጣጫ ድንጋይ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እንደታሰበው አፍሪካን አንድ ለማድረግ አልተሳካለትም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ መሪዎች በሃሳብ መጋጨት የጀመሩት ገና የምስረታ ጉባዔው “ሀ” ተብሎ ሲጀመር “ድርጅቱ ምን ዓይነት መልክ ይኑረው?”  በሚለው ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ መሪዎቹ በሁለት ጎራ ተከፍለዋል፡፡ በእነ ክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የነበሩት ጥቂት የሀገራት መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አፍሪካን አንድ የሚያደርግ በአንድ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚመራ (United States of Africa) ይሁን የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው ጎራየተሰለፉት ግን ገና ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ ብዙም ያልቆዩ ሀገራት በመሆናቸውና ውሳኔውን በመቃወማቸው ድርጅቱ  በራሱ አነስተኛ ስልጣን ያለው የሃገራቱን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትብብር የሚያጠናክር ተቋም እንዲሆን በሚል ለመመስረት በቅቷል፡፡  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በታንዛንያዊው ሳሊም አህመድ ሳሊም የአመራር ዘመን ድርጅቱ የተመሰረተበትን የአህጉሪቱን የፖለቲካና ኢኮኖሚዊ  ግብ ይበልጥ እንዲገልጸውና አህጉሪቱ የሉላዊነትን ተጽዕኖ እንድትወጣ በሚል ምክንያት በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት (AU) የሚል አዲስ ስያሜ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ይኸውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚለው መጠሪያ ከቀድሞ የፓን አፍሪካ መስራቾች አፍሪካን አንድ የማድረግ ርዕይ የመነጨ ስለሆነና ድርጅቱ በተግባር እየተከተለ ያለው ግን አንድ ማድረግ ላይ ሳይሆን  መተባበር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ስያሜው መቀየር አለበት የሚል ነው፤ የስያሜው መቀየር ያስፈልጋል የሚለው ውሳኔ የፓን አፍሪካን ነባር ፍልስፍና መቀየርና በአዲስ ፍልስፍና መተካት ያስፈልጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአባል ሃገራቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ልማትና ሰላም ላይ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን ከሃምሳ ዓመት በፊት ከተመሰረተበት የፓን አፍሪካን ፍልስፍናና ርዕይ አንጻር ሲመዘን ግን የሚተችባቸውም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ አፍሪካን እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (USA) በዶላር  ወይም እንደ አውሮፓ ህብረት (EU) በዩሮ የሚገበያይ አንድ ጠንካራ፣ ሰላማዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አልቻለም፡፡ ይልቁንም አባል ሃገራቱ ከዘመን ወደ ዘመን በእርስ በርስ ግጭት ወደ ከመበታተንና በመነጣጠልና ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? የሰለጠነው የምዕራቡ አህጉር ከዕለት ወደ ዕለት አንድ ወደሚሆንበት ፍልስፍና ወደፊት ሲፈተለክ አፍሪካውያን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃማኖት፣ በቀለምና በቋንቋ ተከፋፍለን በጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን የኋሊት መፈርጠጣችን ለምን ይሆን? የፓን አፍሪካ ፍልስፍናስ ለአፍሪካ እድገት አስፈላጊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ትጥቆችን የያዘ ተግባራዊ ፍልስፍና ወይስ ሊተገበር የማይችል የቀደምት አፍሪካ መሪዎች ህልመኛ (ideal) ፍልስፍና?
በርግጥ አንዳንዶች በተለይም ምዕራባውያን የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና በተግባር ሊተረጎም የማይችል እንደ ግሪክ ፈላስፋው ፕሌቶ ሃሳባዊ ሪፐብሊክ (Plato’s Ideal Republic) በፍልስፍና ደረጃ የሚቀር እንጂ በውን የማይተገበር (Utopian Philosophy) ህልመኛ ፍልስፍና ነው በሚል ዝቅተኛ ግምት ሲቸሩትና ከአፍሪካ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምህዳር ለማውጣት ብርቱ ጥረት ሲደርጉ ኖረዋል፡፡ ለዚህም አስተሳሰብ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በመጀመሪያ ፍልስፍናው በቅኝ ገዢዎችና በባርነት አስፋፊዎችን  በመቃወም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ምዕራባውያን ይህን በአወንታ የሚቀበሉት አልነበረም፡፡ ከዚህም ባሻገር በባርነት ስርዓትም ሆነ በቅኝ አገዛዝ ታሪካቸው፣ እንዲሁም ከድህረ ቅኝ ግዛት በኋላ የአፍሪካ ህዝቦች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓታቸው ሰፊ ልዩነት ስነበራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካን ለመፍጠር የሚሞከር አልነበረም፡፡ በመጨረሻም አፍሪካውያን በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በፖለቲካዊ ስርዓት ሰፊ ልዩነት ስላላቸው ይህንን ልዩነት አስታርቆ በአንድነት ለመስራት  እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል የሚል ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና አህጉሪቱን ወደ ዓለምአቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ የሚቀርብበት ሰረገላ ሆኖ አህጉራዊ ፓን አፍሪካኒዝም ባለንበት ዘመን በልዩ ልዩ መልኩ የአፍሪካን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት በተዋቀሩ እንደ ECOWAS, SADC, EAC በመሳሰሉ ክልላዊ ድርጅቶች አማካይነት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በእኔ እምነት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና ከዚህም አልፎ አፍሪካውያን ለራሳቸው ነባር ባህላዊ እሴቶችና ማንነት ቦታ ሰጥተው በነክዋሜ ንክሩማህ ጎራ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደተሰነዘረው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ  የአንድነት ደረጃ ላይ እስክትደርስ ድረስ መጓዝ ያለበት ፍልስፍና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የፍልስፍና ምሁራን፣ የፖለቲካዊ ሳይንስ ሊቃውንትና የአፍሪካ መሪዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የያኔዎቹ አፍሪካውያን መሪዎችና ምሁራን የያኔዎቹን ቅኝ ገዢዎች ለመዋጋት ክንዶቻቸውን መስተሃልያቸውን (mind) እንዳስተባበሩ ሁሉ፣ የዛሪዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቻችንን ለመዋጋትና የዛሬ ሃምሳ ዓመት የታሰበውን የፓን አፍሪካ ርዕይ እውን ለማድረግ ክንዶቻቸውንና መስተሃልያቸውን ማስተባበር አለባቸው እላለሁ፡፡  ያን ጊዜ የድርጅቱ መጠሪያም “ከአፍሪካ ህብረት” ወደ “አፍሪካ አንድነት”  (US Africa) ይመለስ ይሆናል…ማን ያውቃል?!

Saturday, April 27, 2013

ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!

የሚጥም መልክ፣ የሚጥም ሙዚቃ፣ የሚጮኽ ቀለም ፣ የተረጋጋ ስዕል የሚሉ የውበት አገላለለጾችን ሰምተው ይሆናል፡፡ እነዚህን አገላለጾች በድጋሚ ለአፍታ በአጽንኦት ቢመረምሯቸው ሙዚቃን በምላስ እንደመቅመስ፣ ቀለምን በጆሮ እንደመስማት፣ እንዲሁም ስዕልን በሰው ፀባይ እንደመግለጽ ነው፡፡ ስለ ውበት ስናነሳ በተለምዶ ከምንጠቀምባቸው ቆንጆ እና አስቀያሚ፤ ወይም የሚያምርና የሚያስጠላ ከሚሉት ቃላት ባሻገር ከላይ የጠቀስናቸውን ዓይነት ሌሎች ጽንሰ ሃሳቦችን ጥቅም ላይ መዋላቸው ስለ ውበት ያለን ግንዛቤ፣ ምልከታና ግምገማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጠቱን ያመለክታል፡፡
ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የሰው ልጅ እርካታን ከሚጎናጸፍባቸው መንገዶች አንዱ ውበት ነው፡፡ በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ውበትን ያደንቃሉ፤ ቆንጆ ሆነው መታየትን ይፈልጋሉ፤ ያማረ ነገርን ማየትንና መስማትን ይወዳሉ፡፡ ዓለማችን ስለውበት ብዙ ብላለች፤ በየዕለቱ ቀላል የማይባል ገንዘብ ውበትን ለመጠበቂያ ታወጣለች፡፡ በየወቅቱ ቄነጃጅቱን እያወዳደረች ትሸልማለች…ሌላም ሌላም፡፡ ለመሆኑ ውበት ምንድን ነው?  ውበት በምን መስፈርት ይለካል? በምን ቋንቋ ይገለጻል? ውበት ከሥነ-ምግባር ምን ዝምድና፤ ከሃብት ጋርስ ምን ግኑኝነት አለው?
ሥነ-ውበት (Aesthetics) የውበትን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት፣ እሴቶች፣ አተያዮች እንዲሁም የመገምገሚያ መስፈርቶችን የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሲሆን የዛሬው ጸሁፌ ዋና ዓላማም ስለ ውበት አጭር ሐተታ ማቅረብ ይሆናል፡፡ የሥነ-ውበት ፈላስፎች ውበት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአጠቃላይ የሰው ልጅን፣ ኪነ-ህንጻን፣ ስዕልን፣ ሙዚቃን፣ ቅርጻ-ቅርጽን፣ ቲያትርን፣ ስነጽሁፍን፣ ፊልምንና የመሳሰሉትን የሰው ልጆች የጥበብ ስራዎች፤ እንዲሁም የተፈጥሮን መስህቦችን አካቶ የሚያጠና ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡  ውበት ማለት የአንድ ነገር የሚስብ፤ የሚያረካ ወይም የሚያስደስት ገጽታ ወይም ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ውበት ውጫዊ ቅርጽን፣ ቀለምን፣ መጠንን፣ መልክን ወይም ደምግባትን (pure aesthetics) የሚያመለከት አልያም ውስጣዊ ማንነትንና ሥነ-ምግባርን (moral) የሚመለከት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡  ነገር ግን አስቸጋሪው ጥያቄ  ማንን የሚስብ፣ ማንን የሚያሰደስት ወይም የሚያረካ? የውበቱን ባለቤት? ማህበረሰቡን? የሚስብ ወይም የሚስደስትስ ምን ዓይነት ነገር ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለሱ ላይ ነው፡፡
የዓለማችን ሊቃውንት እነዚህን መሰረታዊ የሥነ-ውበት ጥቄዎች ለመመለስ በሁለት ታላላቅ ጎራ ተሰልፈው ለበርካታ ዘመናት ተሟግተዋል፤ መጻህፍትን ጽፈዋል፤ የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ አድማስም አስፍተዋል፡፡ በመጀመሪያ የምናገኘው የሁሉን አቀፎች (universalists) ወይም የፍጹማውያኑን ርዕዮተ ዓለም ሲሆን ይህም ውበት መለካት ያለበት ነገሮቹ በራሳቸው ባላቸው ማንነት እንጂ ከእነርሱ ውጪ በሚገኝ ማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በማህበረሰቡ ወግ፣ አመለካከት ወይም እምነት ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም የሚል አቋምን የሚያራምድ ነው፡፡ በፍጹማውያኑ ፍልስፍና ውበት በቦታና በጊዜ የማይለዋወጥ በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኝና አንድ ወጥ መስፈርት የሚተገበርበት (objective) ነው፡፡ እንደነዚህ ፈላስፎች እምነት አንዲት ሴት በአንድ ሃገር በሆነ ወቅት ቆንጆ ከተባለች በየትኛውም ዘመን፣ በማንኛውም ቦታና ባህል ቆንጆ ናት ማለት ነው፤ ይህን ለማለት ካልደፈርን ግን ስለሴቲቱ ቁንጅና በርግጠኝነት መናገር አልቻልንም ማለት ነው፤ ወይም ቆንጆ አይደለችም እንደማለት ነው፤  ወይም ቁንጅና የሚባል ሃሳብ የለም ማለት ነው፡፡፡ በሌላ በኩል አንድ የሥነ-ጥበብ ወይም የኪነ-ህንጻ ሥራ ያማረ ነው ካልን  በማንኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ዘመንና ባህል ቢመዘን እኩል ውብ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው፡፡
ሁሉን አቀፍ ፈላስፎች ውበት በአጠቃላይ የራሱ የሆነ አለምአቀፋዊ መለኪያ መስፈርት ያለው ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ይቀበላሉ እንጂ ስለመስፈርቱ ምንነት ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የሁሉን አቀፍ እምነት አራማጆች ማሳመኛ የማንኛውንም ነገር ውበት መለኪያ አመክኗዊ መስፈርቶች ሥርዓት (harmony)፣ ጆሜትሪያዊነትና (geometricness)፣ ወደረኝነት (proportionality) ናቸው፡፡ ለምሳሌ የህንጻ ግንባታ ተጠናቆ እንደተረከብክ የዋናውን መኝታ ክፍል ውበት ገምግመህ አስተያየት እንድትሰጥ ብትጠየቅ በጂኦሜትያዊነትና በወደረኝነት ቀመር የክፍሉ የወለል ስፋት ከጣራው ቁመት ጋር ወደረኛ ከሆነ፣ የክፍሉ ግድግዳዎች እንዲሁም በሮቹና መስኮቶቹ አንድ የታወቀ ጆኦሜትሪያዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ተደርጎ ከሆነ፣ እንዲሁም በሥርኣት መርህ ክፍሉ የተቀባው ቀለም ከተገነባበት ዓላማና የብርሃን ጽምረት እንጻር በተገቢው መንገድ ተመርጦ ከሆነ የሚያምር ክፍል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ግለሰብ የግንባሩ፣ የዓይኑ፣ የአፍንጫው ወይም የከንፈሩ መጠን ከጠቅላላው የፊቱ ስፋት ጋር፤ እንዲሁም ቁመቱ ከክብደቱ ጋር ወደረኛ ከሆነ፤ የአካል ክፍሎቹ አቀማመጥ ጂኦሜትሪካል ከሆኑና በአጠቃላይ የሰውነት ክፍሎቹ በተለመደው ተፈጥሯዊ ሥርኣት ከተደረደሩ ቆንጆ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከነዚህ ባሻገር በተለይ እንደ ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ፊልም፣ ቲያትር፣ ሙዚቃ የመሳሰሉት የጥበብ ስራዎችን ለመገምገም መጠቀም ስለሚገባን መስፈርት ከጥበብ ስራዎቹ በአፍአ የሚገኝን ተመልካቾችና አድማጮች ስሜትና አመክኗዊ ግብረ መልስ መሆን እንዳለበት ይሞግታሉ፤ሌሎች የዘርፉ ምሁራን፡፡ የጥበብ ስራው ከሚሰጠው ተዝናኖታዊ ወይም አስተምህሮታዊ ፋይዳ፣ ከስራው ወጥነት (originality)፣ የራስን ማንነትን ከማንጸባረቅ ወይም አዳዲስ ስልት ከማስተዋወቅ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ድምጻዊ ጥላሁን የተጫወተውን ዜማ ድምጻዊት ዘሪቱ አስመስላ በድጋሚ ብትጫወተው የዘፈኑን ውበት መለካት የሚገባን በአዘፋፈናቸው ብቃት፤ ወይስ ከስራው ቅጂነትና ወጥነት አንጻር ነው የሚለውም ሌላው የሁሉን አቀፎች ርዕዮተ ኣለም መገለጫ ነው፡፡             
ሃሳባውያን (idealist) ፈላስፎች በሁሉን አቀፎች አስተሳሰብ ከሚመሩ ሊቃውንት ይመደባሉ፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋና የሂሳብ ሊቅ ፓይታጎረስ በዓለማችን ላይ ሥርዓትንና (harmony ወደረኛነትን (proportionality) ለመሳሰሉ ሃሳቦች መሰረታቸው ቁጥሮች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በዚህም ሙዚቃዊ ውበት በቁጥር ፍልስፍና ውስጥ እንደሚገለጽ በተለያየ መንገድ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ለምሳሌ አንጥረኛው የጋለውን ብረት በመዶሻ ሲደበድበው የሚሰማው ድምጽ በቁጥሮች ቀመር ከተደረደረ ከመዶሻው ክብደት ጋር ተዋህዶ የሚወጣው ድምጽ ጣዕም ያለው ሙዚቃዊ ቃና ሊኖረው እንደሚችል ማለት ነው፡፡
ሌላው የፓይታጎረስ ተከታይ ፕሌቶ በዚህ ዓለም የሚገኙና በስሜት ህዋሳቶቻችን በምናገኘው መረጃ የምንገነዘባቸው ነገሮች በሙሉ በአወቃቀራቸው ግዙፋን፣ ህጸጽ ያለባቸው፣ የሚለዋወጡ፣ የሚከፋፈሉና የተለያዩ ስለሆኑ የውበትን እውነተኛ ምንነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም ይላል፡፡ በሌላ በኩል በሃሳባዊው ዓለም የሚገኙ ነገሮች (Form) ረቂቃን፣ የማይለዋወጡ፣ የማይከፋፈሉ፣ ምንም ህጸጽ የሌለባቸውና ፍጹማን ስለሆኑ የሚታዩና የሚጨበጡ ግዙፋን ነገሮች እውነተኛ ውበት የሚታወቀው በረቂቁ ሃሳባዊ ዓለም (ideal world) ካላቸው ምስል ጋር በማነጻጸር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው የሥጋና የነፍስ ውሁድ ስለሆነ የአንድ ሰው የሥጋ ውበት የሚታወቀው የግለሰቡ ነፍስ ባህርይን ከሥጋው ማንነት ጋር በማነጻጸር በሚገኝ መስተጋብር ነው፡፡ አንድ የክብ (circle) ስዕል ቆንጆ ክበብ ነው የምንለው ስዕሉ በሃሳባችን ውስጥ ከሚገኘው ፍጹም እውነተኛ ክብ ስዕል ጋር ከሚኖረው ቅርበት አንጻር ነው፡፡
የአስራ ሰባተኛው ክፍለዘመን ጀርመናዊ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት ውበትን ከሥነ-ምግባር ጋር ያያይዘዋል “Beauty is a symbol of morality” ይላል:: ካንት በሥነ-ምግባር ፍልስፍናው ውስጥ በሚመራበት የcategorical imperative መርህ እንደ ስነ-ምግባር ጽንጸሃሳቦች ሁሉ ውበት መለካት ያለበት በአንድ ማህበረሰብ ውስት በሚያስከትለው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሳይሆን በራሱ ብቻ (as an end) ነው ይላል፡፡ ይህም ማለት ውበት  የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት የሚያግባባ የጋራ ቋንቋ እንጂ እንደማህበረሰቡ ስሜት የሚፈስ ጅረት አይደለም ማለት ነው፡፡ በፀሀይ ግባት ወቅት አድማስ ላይ የሚፈጠረው ውበት (sunset) በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ዘንድ በጋራ ሊደነቅ የሚችል የተፈጥሮ ውበት ሲሆን ከዚህም የሚገኘው ደስታ በራሱ የመጨረሻ የእርካታ ምንጭ (end) ነው እንጂ ይሄ ውበት ከማህበረሰብ ሊገኝ ወደሚችል ሌላ ደስታ የሚመራ መንገድ (means) አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ተረከዙ በጣም ረጅም የሆነ (heel) “ቆንጆ”፣ ነገር ግን የማይመች፣ ጫማ መጫማቷ ቆንጆ ጫማ አድርጋለች አያስብላትም፡፡ እንደ ካንት እምነት ምክንያቱም በጫማው ልታገኝ ያሰበችውን ደስታ የምታገኘው በቀጥታ ከጫማው ሳይሆን የጫማውን ዋጋ ወይም ማህበራዊ ፋይዳ ከሚገነዘቡ አካላት አድናቆትንና አክብሮትን ለማትረፍ እንደ መንገድ የተጠቀመችነት በመሆኑ ነው፡፡  
ሁለተኛው የሥነ-ውበት ፈላስፎች ጎራ የአንጻራውያን (relativists) ጎራ ይባላል፡፡ ከሁሉን አቀፎች በተቃራኒ አንጻራውያን ውበት የሚለካበት አንድ ወጥ መስፈርት መኖሩን አይቀበሉም፡፡ ይልቁንም “ውበት እንደተመልካቹ ነው” እንደሚባለው ለአንድ ግለሰብ ውብ የሆነው ነገር ለሌላው አስቀያሚ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ ናቸው፡፡ አንጻራውያን ማንም ሰው ቆንጆ ወይም መልከ ጥፉ ሆኖ አይወለድም፡፡ በተፈጥሮ የሚያምር ወይም የሚያስጠላ ፍጡርም ሆነ  የሰው የጥበብ ስራ የለም፡፡ ውበት የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ ነው፡፡ ለምሳሌ የሴት ልጅ ውፍረት በአንዱ ባህል እንደ ውበት ሲቆጠር በሌላው ደግሞ እንደ ውርደት ሲቆጠር አስተውለን ይሆናል፡፡ “ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!” የሚለው የጽሁፌን ርዕስም በአንጻራውያን እይታ ለአንዲት ሴት የጸጉር መርዘም፣ የአፍንጫ መሰልከክ ወይም የወገብ መቅጠን የውበት ምልክት እንደሆነ የነገራት ያደገችበት ማህበረሰብ እንጂ ከማህበረሰቡ ተጽእኖ ውጪ እነዚህ መስፈርቶች ምንም ናቸው የሚለውን ሃሳብ ለማጉላት የመረጥኩት ነው፡፡ በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በፊት ስለውበቱ በሰፊው የተነገረለትና በርካታ ሰዎች የገዙት አንድ ፋሽን ልብስ ወይም ጫማ ዛሬ አስቀያሚና ለመልበስም አሳፋሪ ሆኖ መገኘቱ፤ እንዲሁም  የአንድ ሙዚቃ አልበም ወይም የስነጽሁፍ ሥራ ውበት በተሸጠው ወይም በተሰራጨው የኮፒ ብዛት (best selling) አንጻር መወሰኑ ባለንበት ዘመን ውበት ምን ያህል በማህበረሰቡ  አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር እንደወደቀ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም ውበት ላይ ተመስርተን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት ስለውበት የጠራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል እላለሁ፡፡

Monday, April 22, 2013

ፍልስፍና አፈንጋጭነትና እብደት!


መቼም ፍልስፍና እንደሚባለው ቃል በበጎም ሆነ በክፉ በተደጋጋሚ የሚነሳ የጥበብ ዘርፍ አይኖርም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፍልስፍናን አንዳንዶች  ከእብደት ጋር፣ ሌሎች ደግሞ ከአፈንጋጭነት ጋር በቀጥታ ያያይዙታል፡፡ በርግጥ ፍልስፍናዊ አፈንጋጭነት ከማህበረሰብ ፍልስፍና ተለይቶ በግለሰባዊ ፍልስፍና የመመራት ውጤትና መገለጫ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ “በብዙ እብዶች መካከል የሚገኝ እንድ ጤነኛ እንደ እብድ ይቆጠራል!” እንዲሉ፤ ብዙዎች የአንድን ጉዳይ ትክክለኝነት በአመክንዮ ሳያረጋግጡ በስሜት፣ በሃማኖታዊ አስተሳሰብና በማህበረሰብ ፍልስፍና ብቻ ተነድተው እውነት ነው ብለው የተቀበሉትን ጉዳይ በግለሰባዊ አመክኗዊ ፍልስፍና የሚመራው ፈላስፋ ሀሰት መሆኑን ገልጾ በመቃወም ራሱ የሚያምንበትን ፍልስፍና ማራመዱን የሙጥኝ ካለ እንደ እብድ መቆጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ በርግጥም በፍልስፍና ታሪክ የምናውቃቸው ታላላቅ የዓለማችን ፈላስፎች በራሳቸው መስተሃልይ በመመራት በኖሩበት ዘመን በነበረው ማኅበረሰብ ያልታሰበውን ቀድመው በማሰባቸውና በጭፍን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ቱባ ማህበረሰባዊ እሴት መሰረት በማናጋታቸው አፈንጋጭና እብድ ተብለዋል፤ ከማህበረሰቡ ተገልለዋል፣ ከቀዬያቸው ተሰደዋል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፤ በመርዝም እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ፍልስፍና አፈንጋጭነትና እብደት ከፍልስፍና ጋር የሚገናኙበት መንገድ ቢኖርም ፍልስፍናን፣ አፈንጋጭነትንና እብደትን አንድና ተመሳሳይ አድርጎ መውሰድ ጉልህ ስህተትን መፈጸም ይሆናል፡፡ ብዙዎች ይህን ስህተት የሚፈጽሙት ደግሞ ስለፍልስፍና ምንነት ያላቸው ግንዛቤ በመዛባቱ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው በዛሬው ጽሁፌ ስለፍልስፍና ትክክለኛውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የወሰንኩት፡፡  
ፍልስፍና ያለምንም ውጪያዊ ግፊት በግለሰቡ ውስጣዊ ተነሳሽነት (Curiosity) ብቻ ገንፍሎ የሚወጣ ተፈጥሮአዊ የእውቀት ጥማት ወይም ጉጉት ነው፡፡ ይህም ስለ ራስ ማንነትና ምንነት፣ ስለ ዓለም አፈጣጠር፣ ስለ ውበት፣ ስለእውቀት፣ በአጠቃላይ የሰው መስተሃልይ (mind) ስለሚያመላልሳቸው የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ህልውና፣ አመጣጥ፣ ምንነት፣ አሰራርና ፍጻሜ የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚደረግ ውስጣዊ ትግል ነው፡፡
ይህ ውስጣዊ ትግል የቀለም፣ የዘር ወይም የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበው አእምሮ በተሰጣቸው የሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንም ዑደት ከህጻናት ባህርይ መረዳት  ይቻላል፡፡ የማህበረሰቡን ወግና ባህል ጠንቅቀው የማያውቁ ህጻናት አእምሮአቸው ውስጥ የሚመላለሰውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ካላቸው የተነሳ ብቻ ያለምንም ፍርሃትና ይሉኝታ አውጥተው እንደሚጠይቁ ሁሉ ፍልስፍናን የህይወታቸው መንገድ ያደረጉ ግለሰቦችም ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ፣ የባህል ወይም የሃይማኖት አስተሳሰብ ሳይገድባቸው ነጻ ሆነው አእምሮአቸው ላቀረበላቸውን ጥያቄ የመጨረሻውን እውነተኛ መልስ ለማግኘት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ይከፍላሉ፡፡ በሌላ  በኩል የሚነሳባቸውን መሰረታዊ ጥያቄ ዋጋ ቢስ  አድርጎ በማሰብ ወይም ለጥያቄው አንድ የመጨረሻ እውነተኛ መልስ አይኖረውም ብሎ በማመን፣ ወይም ለጥያቄው በተለምዶ የሚሰጠውን ምላሽ እንደ እውነተኛ መልስ በመቁጠር  የተነሳውን ውስጣዊ ጥያቄ ችላ የሚሉ ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙትን የፍልስፍና ዝንባሌ ስለሚያደበዝዙት ወደ ፍልስፍና መንገድ ለመግባት ወይም የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚኖራቸው ጉጉት በእጅጉ አነስተኛ ይሆናል፤ ሲከፋም እንደሰው እስካለማሰብ ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በተፈጥሮ የተገኘን የፍልስፍና ዝንባሌን በፍልስፍና ትምህርት ወይም በልምምድ በማዳበር ላቅ ወዳለ የፍልስፍና ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል፡፡
ፍልስፍና ከሚመልሳቸው መልሶች ይልቅ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ይበልጥኑ  ዋጋ ይኖራቸዋል፡፡ በፍልስፍና ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ በየትኛውም የጥልቀት ደረጃ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ጥያቄዎች ያነሳው ፈላስፋ ጥያቄዎቹን ሙሉ በሙሉ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲመልስ አይገደድም፤ ይልቁን እያንዳንዱ ፈላስፋ ካመላለሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን ሙሉ በሙሉ ሌሎቹን ደግሞ በከፊል በራሱ አተያይ ሊመልስ ወይም ደግሞ አንዱ ፈላስፋ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሌሎች ፈላስፎች ሊመልሷቸው ይችላሉ፡፡
ይሁን እንጂ በፍልስፍና ለሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ ፈላስፋ የተሰጡ መልሶችን የመጨረሻና ብቸኛ እውነት ብለን በእርግጠኝነት ልንቀበል አይገባም፤ የተሰጠውን መልስ እውነትነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥቄዎችን ልናከታትል እንጂ! በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ፍልስፍና በማያቋርጥ የጥያቄዎች ሰንሰለት የተመሰለውና መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች በየዘመናቱ እንደ አዲስ እንዲነሱ ምክንያት የሆነው፡፡
ፍልስፍና ለመሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር (Logic) ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህ ደግሞ አመክንዮ (reason) ነው፡፡ በምክንያታዊነት የሚመራ ሰው የአስተሳሰብ ህጸጽን (Fallacy) ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድና ውሳኔዎቹን ሁሉ በሰላ አስተሳሰብ (critically) መዝኖ ለማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ አቅም ነው ፈላስፎችን ከእውነተኛ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ሃሳብን ወይም ድርጊትን በጭራሽ እንዳይታገሱና በቀጥታም እንዲተቹ የሚያስገድዳቸው፡፡
ልስፍና አንድን እውነት በራሱ ፈትሾ ካልደረሰበት በቀር ፈጽሞ አይቀበልም፡፡ ፍልስፍና ሰዎች ለአንድ ውሳኔ ምክንያት ነው ብለው ያቀረቡትን ሁሉ እንደ ተገቢ ምክንያት ላይወስደው  ይችላል፤  ምክንያቱም ግለሰቦቹ የእውነተኛ አስተሳሰብ ቀመርን የማይከተሉ ከሆነ ድምዳሜያቸው ከስሜታዊነትና ከጋርዮሽ ፍልስፍና ወይም ከይሉኝታ፣ ከባህላዊና ሃይማኖታዊ እስተሳሰቦች ተጽዕኖ ነጻ ላይሆን ስለሚችል ነው፡፡
ፍልስፍና የአንድ ርዕዮተ ዓለም አገልጋይ ሳይሆን ሁሉም ሃሳቦች የሚገለጹበት የጋራ መሳሪያ ነው፡፡ፍልስፍና የራሱ የሆነ አንድ አቋም (position) የለውም:: በዚህም ምክንያት ፍልስፍና የራሱን ሳይሆን የተጠቃሚውን ግለሰብ የእምነት ፈለግ ተከትሎ በምክንያታዊነት ብርሃን እየተመራ የሚጓዝ ብርቱ የሃሳብ ባቡር ነው፡፡ ለምሳሌ ስለዓለማትና በውስጣቸው ስለያዟቸው ነገሮች ምንነትና የትመጣነት ዙሪያ የሚነሱ ዲበአካላዊ (metaphysical) ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ የተለያየ ዓይነት እምነት ያላቸው ፈላስፎች ሁሉም ፍልስፍናን የሃሳባቸው ማስኬጃ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ እንደ  ቶማስ አኳይናስና፣ቅዱስ ኦገስቲንና አንሰልምና ፓሊ የመሳሰሉ የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች በፈጣሪ ህልውና የሚያምኑ (Theist) ፈላስፎች ሲሆኑ ለዝች ዓለም ፈጣሪ፣ አስገኚ፣ መጋቢ አላት የሚለውን እምነታቸውን ትክክለናነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን ተገልግለውበታል፤ የነርሱ ተከታዮችም እንዲሁ፡፡ በተቃራኒው በፈጣሪ መኖር የማያምኑ (Atheist) አቋም ያላቸው ፈላስፎችም ሆኑ የፈጣሪ መኖርም ሆነ አለመኖር ሊታወቅ ወይም ሊረጋገጥ አይችልም የሚል እምነት ያላቸው ግኖስቲክ (Agnostic)  ፈላስፎች የዚሁ እምነታቸውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን በተመሳሳይ ሁኔታ ይገለገሉበታል፡፡
ፍልስፍና ለሚያጠነጥንበት ርዕሰ ጉዳይ ወሰን ወይም ድንበር (boundry) የለውም፡፡ ፍልስፍና በሁሉም የጥበብና የዕውቀት ዘርፎች ውስጥ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡ ከልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎች ቀዳሚ እንደመሆኑ መጠን ፍልስፍና ለሌሎች ዘርፎች መነሻ ወይም አባት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍልስፍና መነሻ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የእውቀትና የጥበብ ዘርፎች እንዲዳብሩ፣ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚኮተኩት፤ ለሁሉም በሚሰጠው የሰላ ትችት ዘርፎቹ ድክመቶቻተውን እንዲመለከቱና ለተሻለ እውነት እንዲተጉ የሚቀሰቅስ ንቁ አሰልጣኝ ነው፡፡ በተጨማሪም ፍልስፍና ባሉት መሰረታዊና ተግባራዊ ቅርንጫፎች ማለትም በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስ፣ በኪነጥበብ፣ በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በባህል፣ በስነምግባር፣ በስነውበት፣ በለውጥ (በልማት) እንዲሁም  በሞትና ህይወት ወዘተ ላይ ለየት ያሉና እጅግ ጠቃሚ ጥታቄዎችን የሚያነሳና አዲስ ዓይነት ምልከታ እንዲኖራቸው የሚቆሰቁስ ነው፡፡
ምንም እንኳ ፍልስፍና ግላዊ አስተሳሰብ ነው የሚለው ሃሳብ በፍልስፍና ባለቤትነት ላይ የበላይነት የሚኖረው ቢሆንም ፍልስፍና ሁልጊዜ ግላዊ ነው የሚል መደምደሚ ላይ መድረስ ግን ስህተት ይሆናል፡፡ የአንድ ሰው የግል ፍልስፍና በጊዜ ሂደት ተቋማዊ ወይም ማህበረሰባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ዲሞክራሲ ካፒታሊዝምና ሲሻሊዝም ያሉ በርካታ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናዎች መነሻ ምንጮቻቸው ግላዊ ፍልስፍና (individualistic Philosophy) ሲሆን ባለንበት ወቅት ግን ሀገራዊ ወይም ማህበረሰባዊ ፍልስፍናዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ወርቃማው ህግን የሚመስሉ የስነ-ምግባር ፍልስፍናዎች መነሻቸው ሃይማኖት ወይም ባህል (Communal Philosophy) ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ፍልስፍና አስተሳሰብ ነው በሚል የፍልስፍናን ትርጉም አስፍተው በመመልከት የማንኛውም ግለሰብ፣ ተቋም ወይም ማህበረሰብ አስተሳሰብ፣ እምነት (belief)፣ እሴት (value) ሁሉ ፍልስፍና ነው ሲሉ ይደመጠሉ፡፡ ይሁንና በበርካታ ግለሰቦች፣ ተቋምና በማህበረሰብ ውስጥ ያለው ፍልስፍና በቡድን እምነት (dogma) ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ በመሆኑ በሰላ አስተሳሰብና በምክንያታዊነት  ሚዛን ያልተቃኘ እንዲሁም ለትችት ዝግ የሆነ ነው፡፡ ለትችት ወይም ለለውጥ ክፍት ያልሆነ አስተሳሰብ ደግሞ የፍልስፍና ዋነኛ መገለጫዎች ስለማይታዩበት መደቡ ከፍልስፍና ወገን አይደለም ማለት ነው፡፡
ፍልስፍና ፍልስፍናን በትምህርት ቤት ገብተው በተማሩ ባለሙያዎች (professional philosophers) ወይም በተፈጥሮ ብርቱ የፍልስፍና ዝንባሌ ባላቸው ግለሰቦች ሊካሄድ ይችላል፡፡
በመጨረሻም አንድን የጥበብ ስራ ፍልስፍና ነው ለማለት ከሚያበቁን መስፈርቶች አንዱ ፍልስፍናው በጹሁፍ መቅረቡ ነው የሚል የሙግት ነጥብ ይዘው የሚቀርቡ ሰወች አይጠፉም፡፡ ይሁንና ፍልስፍና በጽሁፍ ወይም በቃል ሊቀርብ እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡
እንደ ኢትዮጽያ ባሉ  ባህላቸው ሃማኖታዊ እሴቱ የሚያመዝንባቸው ወይም የስነ-ጽሁፍ ባህላቸው ያልዳበረ ሃገሮች የግለሰቦችን ፍልስፍና በጽሁፍ የማስቀረት ባህላቸው በእጅጉ ደካማ በመሆኑ በርካታ ፍልስፍናቸው በቃላዊ በቅኔ፣ በተረት፣ በዘይቤ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በወጎች እና በመሳሰሉት የሥነ-ቃል ዘርፎች አማካኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላል ኖሯል፤ ይተላላፋልም፡፡ በዚህም የተነሳ ነው በእንደዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ በርካታ ፍልስፍናዎች የጋርዮሽ (communal) መስለው የሚታዩት ወይም መጀመሪያ ፍልስፍናውን ያመነጨው ግለሰብ ማንነት የማይታወቀው፡፡
ግለሰባዊ የስነ-ጸሁፍ ባህላቸው በእጅጉ ከዳበረ ማህበረሰብ ውስጥ የወጡ ፈላስፎች ሃሳባቸውን በቀጥታ በጽሁፍ ሊያሰፍሩ ካልሆነም ተማሪዎቻቸውና ተከታዮቻቸው ፍልስፍናቸውን በፈላስፎቹ ስም ጽፈው እንዲተላለፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

Monday, April 15, 2013

የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና !

Published on Addis Admass Newspaper (Click here)
በዓለማችን ውስጥ የሚገኘው አጠቃላይ የምግብ ክምችት በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን በሙሉ ማጥገብ ይችል ነበር፤ ነገር ግን አብዛኛው የዓለማችን ሃብት በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር በመውደቁ ጥቂቶቹ የቅንጦት ኑሮ ሲኖሩ አብዛኛው ደሃ ህዝብ ግን በረሃብ አለንጋ ይገረፋል፤ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ፤ በማለት ማርክሲስቶች እኩልነት ደሃና ሃብታምን እኩል በማድረግ ማረጋገጥ እንደሚቻል ያስተምራሉ፡፡ በሌላ በኩል የካፒታሊዝም መስራቾች የግል ሃብት የማፍራት መብትን በማረጋገጥ የሃብታሞችና የድኆች መደቦችን በመፍጠር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ እንደሚቻል ወይም እኩልነትን በሃብት መበላለጥ ማምጣት እንደሚቻል ይሞግታሉ፡፡ የካፒታሊዝም ሆነ የሶሻሊዝም መስራቾች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልንና እኩልነትን ይሰብካሉ፡፡ ታዲያ ሁለቱም እኩልነትንና ፍትህን የሚሰብኩ ከሆነ አሜሪካ መራሽ ካፒታሊስቶችና ሩሲያ መራሽ ሶሻሊስቶች ዓለምን ለሁለት ከፍለው ከአርባ አመታት በላይ ቀዝቃዘቀውን የሞቀ ጦርነት ለምን አካሄዱ? የካፒታሊዝም ፍልስፍና ኢ-ሥነምግባራዊ ነው ሶሻሊዝምስ
ነገሩ ወዲህ ነው! ሁለቱም የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች የሚያቀነቅኗቸው የምጣኔ ኃብት አስተሳሰቦች እርስ በርሳቸው በተቆላለፉ እጅግ በጣም ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ፣ ሃማኖታዊና ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች የታጠሩ ናቸው፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚመራ ማህበረሰብ ወዶም ይሁን ተገዶ እየተመራበት ስለሚገኘው የኑሮ ፍልስፍና ሐተታ ማቅረብ ነው፡፡
ካፒታሊዝም በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ በተመሰረተ እኩልነት ይመራል፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ሊያስከብራቸው ከተቋቋመበት ዓላማዎች ዋና ዋናዎቹ የመኖር፣ የነጻነት እና ንብረት የማፍራት (right to property) መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ፍልስፍና መነሻቸው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ነው፤ በተለይም ደግሞ የግል ሀብት (private property) የማፍራት መብት፡፡
የዘመናዊው የካፒታሊዝም ምጣኔ ሀብት ፍልስፍና ጀማሪ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋና የምጣኔ ሀብት ሊቅ አዳም ስሚዝ  An Inquiry into the Nature and Causes of the Wealth of Nations  በተባለውና በ1776ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ በካፒታሊዝም ውስጥ የሚገኝ የሀብት ክፍፍል ደመወዝ፣ ኪራይ፣ ትርፍ  በተባሉ ምጣኔ ሀብታዊ ጽንሰ ሃሳቦች ሊመነዘር እንደሚችልና ይህም ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት በሚደረግ ነጻ ገበያ (free market) ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስረዳል፡፡  እንደ ስሚዝ እምነት ለካፒታሊዝም ህልውና ወሳኝ የሆኑት ሦስት ሃሳቦች የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest)፣ የግል ሀብት የማፍራት መብትና (private property) ውድድር (competetion) ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በካፒታሊስቶች አስተሳሰብ የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest) ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ተብሎ ሲታሰብ ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚገኝ ሀብት ላይ ገንዘቡንና ጉልበቱን አፍስሶ የራሴ የሚለው ሀብት የማግኘትና የማከማቸት መብት አለው የሚለውን መርህ የሚያጎላ ነው፡፡ የካፒታሊዝም ፍልስፍና የግለሰብ ፍላጎት ከማህበረሰብ ወይም ከሀገር ፍላጎት እንደሚበልጥ በገሃድ የሚታይበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህም ማለት ካፒታሊስቶች “በእኔ ባዮች” (egoists) የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ሲሆኑ ይህም ሰው በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ስለሆነ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ለአድራጊው ግለሰብ ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
የዚህ ፍልስፍና ሁለተኛው መርህ ግለሰቡ በፈቀደው መንገድ የሰበሰበውን ሀብት የማከማቸት (accumulation) እና ባሻውና ያረካኛል በሚለው መንገድ የማውጣት መብትም የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ አንዱ ነጋዴ ከሌላው ነጋዴ፣ ተወዳድሮ ያሻውን ምርት ሊያመርትና ያዋጣኛል በሚለው ዋጋ በመሸጥ ትርፋማ ሊሆን ይችላል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት መብት (the right to property) የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች የተሳሰሩበት የጋራ መድረክ ነው፡፡ አንድ ሃገር የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚከተል ከሆነ የካፒታሊዝምን ፍልስፍና መቀበል ኖርበታል፤ ለካፒታሊዝም ህልውና ደግሞ የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ጥበቃና ድጋፍ እስትንፋስ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለካፒታሊዝም ምጣኔሃብታዊ ፍልስፍናና ለአሜሪካን ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የእንግሊዙ ፈላስፋ ጆን ሎክ ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ ያገኙት ሃብት ላይ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ የግል ሃብት የማካበት ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸው መሞገቱ የግል ሃብት መብት ምን ያህል ቁልፍ ቦታ እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ሦስተኛው የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና መርህ ውድድር (competetion) ነው፡፡ በእኔ ባይ የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የተቃኘው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና ከትብብር በእጅጉ የራቀ ስለሆነ በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ጥቂት የአለማችን ሃብታም ግለሰቦች በርካታውን የምድራችንን ሃብት የሚይዙበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በአሜሪካን ሀገር በኒዮርክ ከተማ በመስከረም በ2011 ዓ.ም ተነስተው የነበሩት የ Occupy the Wall Street (OWS) ሰልፈኞች “ዘጠና ዘጠኝ በመቶው የዓለም ህዝብ እኛ ድኆቹ ነን! We are the 99 percent!” የሚለው ካፒታሊዝምን በመቃወም ያሰሙ የነበረው መፈክር ለዚህ  በአብነት የሚቀርብ ነው፡፡
ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚካሄደው የካፒታሊዝም የነጻ ገበያ ፍልስፍና ከውድድር፣ ከሃብት ክምችትና ከሉላዊነት መርኆዎች ጋር ተዋህዶ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በግብይት ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳኖራቸው አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ታዳጊ ሃገሮች ውስጥ የሚመረተውም ምርት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አብዛኛው ዜጎች ተወዳድረው መሸመት ስለማይችሉና ምርቱን አቅም ያላቸው የውጪ ሀገር ነጋዴዎች በፍጥነት ስለሚረከቡት በሃገር ውስጥ ምርቱ ተመርቶ (supply) እያለ የዜጎችን የሸቀት ፍላጎት (Demand) ማሟላት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል፡፡  
በካፒታሊዝም የህይወት ፍልስፍና ውስጥ ውድድር እጅግ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ውጤታማነት ማለት በማንኛውም መልኩ፣ በየትኛውም መንገድ ከሌላው በልጦ መገኘት ነው፡፡ በጀርመናዊው የምጣኔሃብትና ማህበረሰብ ሳይንስ ሊቅ ማክስ ዌበር (Max Weber) Formal Rationality መርህ ላይ የተመሰረተው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረ ነው፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በስሌቱ መሰረት ድርጊቱ ሌላውን ለመብለጥ የሚያስችል፣ ከኪሳራው ትርፉ ከበለጠ ወይም አዋጭ መስሎ ከታየው ማንኛውንም ሃላፊነት የጎደለውና ህገ ወጥ የመበልጸጊያ መንገዶችን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ይህንንም ጀርመናዊው ፈላስፋ ሰዎችን እንደሰዎች (life world) ሳይሆን እንደ ሸቀጥ አውርዶ ራስን ባማከለና ሌሎችን ያላገናዘበ ገንዘብ ተኮር (impersonal)  የኑሮ ፍልስፍና  ነው ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዌበር The Protestant Ethic and the spirit of Capitalism (1905) እና The Religions of the East (1920) በተባሉት ስራዎቹ ካፒታሊዝም በምዕራቡ ዓለም በቀላሉ ለመስፋፋት የቻለውና በምስራቁ እንዳይስፋፋ የሆነበት ምክንያት የማህበረሰቡ ስነምግባራዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ብርቱ ተጽዕኖ ስለነበራቸው ነው ይላል፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና ሰዎች በውድድር መንፈስ ውስጥ ስለሚኖሩ እርካታን የሚጎናጸፉት የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት ወይም በማድረግ ሳይሆን የሚፈልጉትን ነገር በማድረግ ነው፡፡ የሚፈልጉት ነገር ደግሞ በውድድሩ ውስጥ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በድረገጾች ላይ በማስታወቂያ ቋንቋ ተውበው የሚቀርቡትን፣ ወይም በኢኮኖሚያቸው ወይም በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው የክብር ስፍራ ላቅ ብለው የሚታዩ ግለሰቦችን ምርጫ አብነት በማድረግ የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሰሌ ምቾት ያለው ወይም ጥሩ ኑሮ እየኖረ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ሰው ገንዘቡን ለሚስፈልገው ነገር (for necessiety) የሚያወጣ ሳይሆን ከቢጤዎቹ ጋር ተወዳድሮ በልጦ ለመታየት ለሚያበቃው ነገር በከፍተኛ ደረጃ የሚያወጣ ነው፡፡ ይህም ፋሽን ልብሶችና ጫማዎች በመከተል፣ የመኪና ሞዴሎችን በመቀያየር፣ እንዲሁም ሌሎች የቅንጦት እቃዎችን በመግዛት የሚገለጽ ነው፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና የአንድን ሸቀጥ ዋጋ ለመተመን በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ሸቀጡ የሚሰጠው አገልግሎት፣ ብዛት ወይም ጥራት ሳይሆን ህብረተሰቡ ለሸቀጡ ያለው ስነልቡናዊ እሴት (value) ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ቱርክ ውስጥ የተመረተ ጫማ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመረተው አንጻር የተሻለ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ጫማው ካለው ጥንካሬ ወይም ከተሰራበት ጥሬ ዕቃ ወይም ከዲዛይኑ ማማር የተነሳ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ስነልቡና ከአፍሪካውያን ምርት ይልቅ የአውሮፓውያን (brand) ተሻለ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚወሰድና ዋጋውም የበለጠ ስለሆነ በተመልካች ዘንድ የተለየ የክብር ቦታ ያሰጣል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተቦጫጨቀና የተጣጣፈ ጂንስ ሱሪ በውድ ገንዘብ ገዝቶ መልበስ እንደ ፋሽን ተይዟል፡፡ ለመሆኑ ፋሽን ምንድን ነው? ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት የሚገባው ለምን ዓይነት ልብስ ነው? ለዚያ ለተቀዳደደ ልብስ በምን አይነት አመክንዮ ያን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት ወሰኑ? በርግጥ ዲዛይነሮቹ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳደደውንና የተጣጣፈውን ልብስ ሲያቀርቡ ዲዛይኑን ላዘጋጁለት የተለየ ማህበረሰብ አንዳች ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው፤ ወይም ከአንድ ሁነታ (event) ጋር አስታከው ሰርተውት ይሆናል፤ ለእኛ ለኢትጵያውያንስ…?! በእኔ አስተሳሰብ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና ከሌሎች መወዳደርና እኩል ሆኖ ወይም በልጦ መታየት ታላቁ የውጤታማነት የኑሮ ፍልስፍና (life success) ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ማንኛውም ሸቀጥ ታላቅነት የሚለካው በሚሰጠው አገልግሎት ብዛትና ጥራት ሳይሆን በሚያወጣው የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ነው፤ ምክንያቱም ፍልስፍናው ከሌሎች በልጦ ወይም ተመሳስሎ መገኘት ነውና፡፡ የሚገርመው ነገር ጥሩ ወይም የሚያምር  የሚባለው ልብስ እንኳ የሚለየው ከብራንዱ ወይም ከተከፈለበት ከፍተኛ ዋጋ አንጻር ነው፡፡ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና በጭፍን የሚመሩ ግለሰቦች አንድ ሸቀጥ ስሪቱ ጥሩም ይሁን መጥፎ ምርጫቸው ዋጋው ከፍተኛ የሆነው ብቻ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አንድ ተመሳሳይ ዕቃ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከትርፍና ኪሳራ ስሌት ውጪ በሆነ እጅግ በጣም የተራራቀ ዋጋ ሲሸመት መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ አሁን አሁንማ ይባስ ብሎ ሸቀጦችን ተገቢ በሆነ ዋጋ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የሸቀጦቻቸው ዋጋው ዝቅተኛ ስለሆነ ብቻ ጥራት እንደሌለው ተደርጎም እየታሰበ ነው፡፡            
የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና የግል ሀብት ማከማቸትን ስለሚያበረታታና የሃብት አሰባሰቡና አጠቃቀሙ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ፍላጎትና በውድድር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በግለሰቦች መካከል ከትብብር ይልቅ የፉክክር ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት ጥማት በራስ ወዳድነት (egoistic) የስነምግባር ፍልስፍና መመራትን የግድ ይላል፡፡ በራስ ወዳድነት የተቃኘ የሃብት ሽሚያ ወይም ስግብግብነት ደግሞ ለሀገር ፍቅር ስሜት መቀዝቀዝ፣ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ይዳርጋል፡፡ ሃገራችን በልማት ጉዞዋ ላይ ዛሬ የተጋደመባት ጋሬጣም ይኸው ነው፡፡ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ሲመደቡ የሚያስጨንቃቸው የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ብመርጥ ለወገን ብሎም ለዓለም የሚተርፍ የምርምር ውጤት አበረክታለሁ ሳይሆን በየትኛው መስክ ብሰማራ ከሌሎች የተሻለ ገንዘብ አገኛለሁ የሚለው ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በምርቃታቸው ዋዜማ ውይይታቸው ተመርቄ እንዴት ሃገሬን አገለግላለሁ ሳይሆን በየትኛው አቋራጭ ተጠቅሜ በአጭር ጊዜ እበለጽጋለሁ የሚል ነው፡፡   
በመጨረሻም የካፒታሊዝምን ፍልስፍና አስከፊ ገጽታ አስቀድሞ መመልከት የቻለው ካርል ማርክስ የካፒታሊዝምን ስርኣት ገርስሶ በሶሻሊዝም ብሎም በኮሚውኒዝም ስርኣት መተካት ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ ከጓደኛው ፍሬዴሪክ ኤንግልስ ጋር በአንድነት ባሳተመው The Communist Manifesto በተባለው መጽሀፉ በዝርዝር አስረድቷል፡፡ ከዚህም አልፎ ምዕራቡ ዓለም ካፒታሊዝምን የሙጥኝ ባለባቸው ዘመናት ምስራቁ ዓለም የማርክስን ፍልስፍና በተግባር ለመተርጎምና የቀረውን ዓለም በማርክሲስት ፍልስፍና አጥምቆ የሃብት እኩልነትን በማረጋገጥ ዓለምአቀፋዊ ትብብርን ለማስፈን የሞት ሽረት ትግል አካሂዶ ነበር፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፡፡ ይህም ውጥረት ከቀድሞዋ ሶቬት ህብረት በመታተን በኋላ ተዳፍኖ ለየት ባለ መልኩ በኩባ፣ በተወሰኑ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች እንዲሁም በቻይና በዝቅተኛ ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካፒታሊዝምን በሶሻሊዝም መተካት ግን ለካፒታሊዝም የስነምግባር ዝቅጠት የተሻለ መፍትሄ መሆን እንደማይችል ከታሪክ ተምረናል እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ አርዌል የእንስሳት እድር (Animal Farm) በተባለው ዘይቤያዊ ድርሰቱም አሳይቶናል፡፡
ይሁንና ባለንበት ዘመን በርካታ ሃገሮች ይህንኑ የካፒታሊዝም ኢሥነ-ምግባራዊ አስተሳሰብ በመገንዘብ ከካፒታሊዝምና ከሶሻሊዝም ፍልስፍና በጎ በጎው ተወጣጥቶ የተሰናዳ ቅይጥ ኢኮኖሚ (Mixed Economy) የሚባል የሚጠራ የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና በመከተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሃቤርማስ (Jurgen Habermas) ደግሞ በበኩሉ ለምዕራባውያን የካፒታሊዝም ፍልስፍና የስነምግባር ዝቅጠት ዋነኛ ምክንያት በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረው የማክስ ዌበር Formal Rationality መርህ ስለሆነ መፍትሄው በምዕራባውያን የኢንዱስትሪ ዲሞክራሲ የሰው ልጆችን ዓለም (life world) በሸቀጥ ደረጃ አውርዶ በሂሳብና በገንዘብ የሚተምነውን ፍልስፍና communicative action በተባለው የሃቤርማስ ፍልስፍና መንገድ መተካትና ዜጎች ከመንግስታቸው ጋር እንደ ካፒታሊዝም ባሉ ስነምግባራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በአመክንዮ ተወያይተው እንዲተማመኑ ማድረግ ነው ይላል፡፡ እርስዎስ ታዲያ ምን ይላሉ?