Monday, April 15, 2013

የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና !

Published on Addis Admass Newspaper (Click here)
በዓለማችን ውስጥ የሚገኘው አጠቃላይ የምግብ ክምችት በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን በሙሉ ማጥገብ ይችል ነበር፤ ነገር ግን አብዛኛው የዓለማችን ሃብት በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር በመውደቁ ጥቂቶቹ የቅንጦት ኑሮ ሲኖሩ አብዛኛው ደሃ ህዝብ ግን በረሃብ አለንጋ ይገረፋል፤ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ፤ በማለት ማርክሲስቶች እኩልነት ደሃና ሃብታምን እኩል በማድረግ ማረጋገጥ እንደሚቻል ያስተምራሉ፡፡ በሌላ በኩል የካፒታሊዝም መስራቾች የግል ሃብት የማፍራት መብትን በማረጋገጥ የሃብታሞችና የድኆች መደቦችን በመፍጠር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ እንደሚቻል ወይም እኩልነትን በሃብት መበላለጥ ማምጣት እንደሚቻል ይሞግታሉ፡፡ የካፒታሊዝም ሆነ የሶሻሊዝም መስራቾች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልንና እኩልነትን ይሰብካሉ፡፡ ታዲያ ሁለቱም እኩልነትንና ፍትህን የሚሰብኩ ከሆነ አሜሪካ መራሽ ካፒታሊስቶችና ሩሲያ መራሽ ሶሻሊስቶች ዓለምን ለሁለት ከፍለው ከአርባ አመታት በላይ ቀዝቃዘቀውን የሞቀ ጦርነት ለምን አካሄዱ? የካፒታሊዝም ፍልስፍና ኢ-ሥነምግባራዊ ነው ሶሻሊዝምስ
ነገሩ ወዲህ ነው! ሁለቱም የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች የሚያቀነቅኗቸው የምጣኔ ኃብት አስተሳሰቦች እርስ በርሳቸው በተቆላለፉ እጅግ በጣም ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ፣ ሃማኖታዊና ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች የታጠሩ ናቸው፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚመራ ማህበረሰብ ወዶም ይሁን ተገዶ እየተመራበት ስለሚገኘው የኑሮ ፍልስፍና ሐተታ ማቅረብ ነው፡፡
ካፒታሊዝም በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ በተመሰረተ እኩልነት ይመራል፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ሊያስከብራቸው ከተቋቋመበት ዓላማዎች ዋና ዋናዎቹ የመኖር፣ የነጻነት እና ንብረት የማፍራት (right to property) መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ፍልስፍና መነሻቸው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ነው፤ በተለይም ደግሞ የግል ሀብት (private property) የማፍራት መብት፡፡
የዘመናዊው የካፒታሊዝም ምጣኔ ሀብት ፍልስፍና ጀማሪ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋና የምጣኔ ሀብት ሊቅ አዳም ስሚዝ  An Inquiry into the Nature and Causes of the Wealth of Nations  በተባለውና በ1776ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ በካፒታሊዝም ውስጥ የሚገኝ የሀብት ክፍፍል ደመወዝ፣ ኪራይ፣ ትርፍ  በተባሉ ምጣኔ ሀብታዊ ጽንሰ ሃሳቦች ሊመነዘር እንደሚችልና ይህም ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት በሚደረግ ነጻ ገበያ (free market) ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስረዳል፡፡  እንደ ስሚዝ እምነት ለካፒታሊዝም ህልውና ወሳኝ የሆኑት ሦስት ሃሳቦች የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest)፣ የግል ሀብት የማፍራት መብትና (private property) ውድድር (competetion) ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በካፒታሊስቶች አስተሳሰብ የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest) ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ተብሎ ሲታሰብ ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚገኝ ሀብት ላይ ገንዘቡንና ጉልበቱን አፍስሶ የራሴ የሚለው ሀብት የማግኘትና የማከማቸት መብት አለው የሚለውን መርህ የሚያጎላ ነው፡፡ የካፒታሊዝም ፍልስፍና የግለሰብ ፍላጎት ከማህበረሰብ ወይም ከሀገር ፍላጎት እንደሚበልጥ በገሃድ የሚታይበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህም ማለት ካፒታሊስቶች “በእኔ ባዮች” (egoists) የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ሲሆኑ ይህም ሰው በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ስለሆነ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ለአድራጊው ግለሰብ ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
የዚህ ፍልስፍና ሁለተኛው መርህ ግለሰቡ በፈቀደው መንገድ የሰበሰበውን ሀብት የማከማቸት (accumulation) እና ባሻውና ያረካኛል በሚለው መንገድ የማውጣት መብትም የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ አንዱ ነጋዴ ከሌላው ነጋዴ፣ ተወዳድሮ ያሻውን ምርት ሊያመርትና ያዋጣኛል በሚለው ዋጋ በመሸጥ ትርፋማ ሊሆን ይችላል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት መብት (the right to property) የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች የተሳሰሩበት የጋራ መድረክ ነው፡፡ አንድ ሃገር የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚከተል ከሆነ የካፒታሊዝምን ፍልስፍና መቀበል ኖርበታል፤ ለካፒታሊዝም ህልውና ደግሞ የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ጥበቃና ድጋፍ እስትንፋስ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለካፒታሊዝም ምጣኔሃብታዊ ፍልስፍናና ለአሜሪካን ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የእንግሊዙ ፈላስፋ ጆን ሎክ ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ ያገኙት ሃብት ላይ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ የግል ሃብት የማካበት ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸው መሞገቱ የግል ሃብት መብት ምን ያህል ቁልፍ ቦታ እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ሦስተኛው የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና መርህ ውድድር (competetion) ነው፡፡ በእኔ ባይ የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የተቃኘው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና ከትብብር በእጅጉ የራቀ ስለሆነ በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ጥቂት የአለማችን ሃብታም ግለሰቦች በርካታውን የምድራችንን ሃብት የሚይዙበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በአሜሪካን ሀገር በኒዮርክ ከተማ በመስከረም በ2011 ዓ.ም ተነስተው የነበሩት የ Occupy the Wall Street (OWS) ሰልፈኞች “ዘጠና ዘጠኝ በመቶው የዓለም ህዝብ እኛ ድኆቹ ነን! We are the 99 percent!” የሚለው ካፒታሊዝምን በመቃወም ያሰሙ የነበረው መፈክር ለዚህ  በአብነት የሚቀርብ ነው፡፡
ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚካሄደው የካፒታሊዝም የነጻ ገበያ ፍልስፍና ከውድድር፣ ከሃብት ክምችትና ከሉላዊነት መርኆዎች ጋር ተዋህዶ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በግብይት ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳኖራቸው አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ታዳጊ ሃገሮች ውስጥ የሚመረተውም ምርት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አብዛኛው ዜጎች ተወዳድረው መሸመት ስለማይችሉና ምርቱን አቅም ያላቸው የውጪ ሀገር ነጋዴዎች በፍጥነት ስለሚረከቡት በሃገር ውስጥ ምርቱ ተመርቶ (supply) እያለ የዜጎችን የሸቀት ፍላጎት (Demand) ማሟላት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል፡፡  
በካፒታሊዝም የህይወት ፍልስፍና ውስጥ ውድድር እጅግ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ውጤታማነት ማለት በማንኛውም መልኩ፣ በየትኛውም መንገድ ከሌላው በልጦ መገኘት ነው፡፡ በጀርመናዊው የምጣኔሃብትና ማህበረሰብ ሳይንስ ሊቅ ማክስ ዌበር (Max Weber) Formal Rationality መርህ ላይ የተመሰረተው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረ ነው፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በስሌቱ መሰረት ድርጊቱ ሌላውን ለመብለጥ የሚያስችል፣ ከኪሳራው ትርፉ ከበለጠ ወይም አዋጭ መስሎ ከታየው ማንኛውንም ሃላፊነት የጎደለውና ህገ ወጥ የመበልጸጊያ መንገዶችን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ይህንንም ጀርመናዊው ፈላስፋ ሰዎችን እንደሰዎች (life world) ሳይሆን እንደ ሸቀጥ አውርዶ ራስን ባማከለና ሌሎችን ያላገናዘበ ገንዘብ ተኮር (impersonal)  የኑሮ ፍልስፍና  ነው ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዌበር The Protestant Ethic and the spirit of Capitalism (1905) እና The Religions of the East (1920) በተባሉት ስራዎቹ ካፒታሊዝም በምዕራቡ ዓለም በቀላሉ ለመስፋፋት የቻለውና በምስራቁ እንዳይስፋፋ የሆነበት ምክንያት የማህበረሰቡ ስነምግባራዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ብርቱ ተጽዕኖ ስለነበራቸው ነው ይላል፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና ሰዎች በውድድር መንፈስ ውስጥ ስለሚኖሩ እርካታን የሚጎናጸፉት የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት ወይም በማድረግ ሳይሆን የሚፈልጉትን ነገር በማድረግ ነው፡፡ የሚፈልጉት ነገር ደግሞ በውድድሩ ውስጥ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በድረገጾች ላይ በማስታወቂያ ቋንቋ ተውበው የሚቀርቡትን፣ ወይም በኢኮኖሚያቸው ወይም በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው የክብር ስፍራ ላቅ ብለው የሚታዩ ግለሰቦችን ምርጫ አብነት በማድረግ የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሰሌ ምቾት ያለው ወይም ጥሩ ኑሮ እየኖረ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ሰው ገንዘቡን ለሚስፈልገው ነገር (for necessiety) የሚያወጣ ሳይሆን ከቢጤዎቹ ጋር ተወዳድሮ በልጦ ለመታየት ለሚያበቃው ነገር በከፍተኛ ደረጃ የሚያወጣ ነው፡፡ ይህም ፋሽን ልብሶችና ጫማዎች በመከተል፣ የመኪና ሞዴሎችን በመቀያየር፣ እንዲሁም ሌሎች የቅንጦት እቃዎችን በመግዛት የሚገለጽ ነው፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና የአንድን ሸቀጥ ዋጋ ለመተመን በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ሸቀጡ የሚሰጠው አገልግሎት፣ ብዛት ወይም ጥራት ሳይሆን ህብረተሰቡ ለሸቀጡ ያለው ስነልቡናዊ እሴት (value) ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ቱርክ ውስጥ የተመረተ ጫማ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመረተው አንጻር የተሻለ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ጫማው ካለው ጥንካሬ ወይም ከተሰራበት ጥሬ ዕቃ ወይም ከዲዛይኑ ማማር የተነሳ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ስነልቡና ከአፍሪካውያን ምርት ይልቅ የአውሮፓውያን (brand) ተሻለ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚወሰድና ዋጋውም የበለጠ ስለሆነ በተመልካች ዘንድ የተለየ የክብር ቦታ ያሰጣል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተቦጫጨቀና የተጣጣፈ ጂንስ ሱሪ በውድ ገንዘብ ገዝቶ መልበስ እንደ ፋሽን ተይዟል፡፡ ለመሆኑ ፋሽን ምንድን ነው? ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት የሚገባው ለምን ዓይነት ልብስ ነው? ለዚያ ለተቀዳደደ ልብስ በምን አይነት አመክንዮ ያን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት ወሰኑ? በርግጥ ዲዛይነሮቹ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳደደውንና የተጣጣፈውን ልብስ ሲያቀርቡ ዲዛይኑን ላዘጋጁለት የተለየ ማህበረሰብ አንዳች ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው፤ ወይም ከአንድ ሁነታ (event) ጋር አስታከው ሰርተውት ይሆናል፤ ለእኛ ለኢትጵያውያንስ…?! በእኔ አስተሳሰብ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና ከሌሎች መወዳደርና እኩል ሆኖ ወይም በልጦ መታየት ታላቁ የውጤታማነት የኑሮ ፍልስፍና (life success) ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ማንኛውም ሸቀጥ ታላቅነት የሚለካው በሚሰጠው አገልግሎት ብዛትና ጥራት ሳይሆን በሚያወጣው የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ነው፤ ምክንያቱም ፍልስፍናው ከሌሎች በልጦ ወይም ተመሳስሎ መገኘት ነውና፡፡ የሚገርመው ነገር ጥሩ ወይም የሚያምር  የሚባለው ልብስ እንኳ የሚለየው ከብራንዱ ወይም ከተከፈለበት ከፍተኛ ዋጋ አንጻር ነው፡፡ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና በጭፍን የሚመሩ ግለሰቦች አንድ ሸቀጥ ስሪቱ ጥሩም ይሁን መጥፎ ምርጫቸው ዋጋው ከፍተኛ የሆነው ብቻ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አንድ ተመሳሳይ ዕቃ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከትርፍና ኪሳራ ስሌት ውጪ በሆነ እጅግ በጣም የተራራቀ ዋጋ ሲሸመት መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ አሁን አሁንማ ይባስ ብሎ ሸቀጦችን ተገቢ በሆነ ዋጋ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የሸቀጦቻቸው ዋጋው ዝቅተኛ ስለሆነ ብቻ ጥራት እንደሌለው ተደርጎም እየታሰበ ነው፡፡            
የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና የግል ሀብት ማከማቸትን ስለሚያበረታታና የሃብት አሰባሰቡና አጠቃቀሙ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ፍላጎትና በውድድር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በግለሰቦች መካከል ከትብብር ይልቅ የፉክክር ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት ጥማት በራስ ወዳድነት (egoistic) የስነምግባር ፍልስፍና መመራትን የግድ ይላል፡፡ በራስ ወዳድነት የተቃኘ የሃብት ሽሚያ ወይም ስግብግብነት ደግሞ ለሀገር ፍቅር ስሜት መቀዝቀዝ፣ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ይዳርጋል፡፡ ሃገራችን በልማት ጉዞዋ ላይ ዛሬ የተጋደመባት ጋሬጣም ይኸው ነው፡፡ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ሲመደቡ የሚያስጨንቃቸው የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ብመርጥ ለወገን ብሎም ለዓለም የሚተርፍ የምርምር ውጤት አበረክታለሁ ሳይሆን በየትኛው መስክ ብሰማራ ከሌሎች የተሻለ ገንዘብ አገኛለሁ የሚለው ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በምርቃታቸው ዋዜማ ውይይታቸው ተመርቄ እንዴት ሃገሬን አገለግላለሁ ሳይሆን በየትኛው አቋራጭ ተጠቅሜ በአጭር ጊዜ እበለጽጋለሁ የሚል ነው፡፡   
በመጨረሻም የካፒታሊዝምን ፍልስፍና አስከፊ ገጽታ አስቀድሞ መመልከት የቻለው ካርል ማርክስ የካፒታሊዝምን ስርኣት ገርስሶ በሶሻሊዝም ብሎም በኮሚውኒዝም ስርኣት መተካት ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ ከጓደኛው ፍሬዴሪክ ኤንግልስ ጋር በአንድነት ባሳተመው The Communist Manifesto በተባለው መጽሀፉ በዝርዝር አስረድቷል፡፡ ከዚህም አልፎ ምዕራቡ ዓለም ካፒታሊዝምን የሙጥኝ ባለባቸው ዘመናት ምስራቁ ዓለም የማርክስን ፍልስፍና በተግባር ለመተርጎምና የቀረውን ዓለም በማርክሲስት ፍልስፍና አጥምቆ የሃብት እኩልነትን በማረጋገጥ ዓለምአቀፋዊ ትብብርን ለማስፈን የሞት ሽረት ትግል አካሂዶ ነበር፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፡፡ ይህም ውጥረት ከቀድሞዋ ሶቬት ህብረት በመታተን በኋላ ተዳፍኖ ለየት ባለ መልኩ በኩባ፣ በተወሰኑ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች እንዲሁም በቻይና በዝቅተኛ ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካፒታሊዝምን በሶሻሊዝም መተካት ግን ለካፒታሊዝም የስነምግባር ዝቅጠት የተሻለ መፍትሄ መሆን እንደማይችል ከታሪክ ተምረናል እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ አርዌል የእንስሳት እድር (Animal Farm) በተባለው ዘይቤያዊ ድርሰቱም አሳይቶናል፡፡
ይሁንና ባለንበት ዘመን በርካታ ሃገሮች ይህንኑ የካፒታሊዝም ኢሥነ-ምግባራዊ አስተሳሰብ በመገንዘብ ከካፒታሊዝምና ከሶሻሊዝም ፍልስፍና በጎ በጎው ተወጣጥቶ የተሰናዳ ቅይጥ ኢኮኖሚ (Mixed Economy) የሚባል የሚጠራ የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና በመከተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሃቤርማስ (Jurgen Habermas) ደግሞ በበኩሉ ለምዕራባውያን የካፒታሊዝም ፍልስፍና የስነምግባር ዝቅጠት ዋነኛ ምክንያት በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረው የማክስ ዌበር Formal Rationality መርህ ስለሆነ መፍትሄው በምዕራባውያን የኢንዱስትሪ ዲሞክራሲ የሰው ልጆችን ዓለም (life world) በሸቀጥ ደረጃ አውርዶ በሂሳብና በገንዘብ የሚተምነውን ፍልስፍና communicative action በተባለው የሃቤርማስ ፍልስፍና መንገድ መተካትና ዜጎች ከመንግስታቸው ጋር እንደ ካፒታሊዝም ባሉ ስነምግባራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በአመክንዮ ተወያይተው እንዲተማመኑ ማድረግ ነው ይላል፡፡ እርስዎስ ታዲያ ምን ይላሉ?

Monday, April 8, 2013

ያልተጠናው የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና

Published on Addis Admas Newspaper
ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሥነቃላዊና የጽሁፍ ፍልስፍናዎች ባለቤት ናት፡፡ ከአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ መልኩ በርከት ያሉ የፍልስፍና ስራዎችን በመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ከተጻፉት የፍልስፍና ስራዎቿ መካከል ከፊሎቹን በትውልድ ካናዳዊ በምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነው ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ሲያደርግ፤ ሌሎች በርካታ በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋዎች የተጻፉ የጽሁፍ ስራዎች በጥንታዊ ቤተእምነቶችና በቤተመዛግብት ውስጥ ተቀምጠው ክላውድ ሰምነርን የመሰሉ ፈላስፎችንና የጥንታዊ ጽሁፎች ተመራማሪዎችን (philologists) እይታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፍልስፍና በጥቅሉ የተጻፉትንና በቃል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉትን የጋርዮሽ የማህበረሰብ ወጎች፣ ልማዶች፣ጥበቦች፣ የእውቀት ዘርፎችንና አስተሳሰቦችን፤ በጠባቡ አተያይ ደግሞ በግለሰብ ፈላስፋዎች በአንድ ዘመን ተሰርተው በጽሁፍ የተላለፉትን ስራዎች ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች በተረትና ምሳሌ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በዘይቤዎች በቅኔዎችና በወጎች ሊገለጡ ይችላሉ፡፡ ስለ ጾታ ልዩነት፣ እድሜ፣ ፖለቲካ፣ ስነምግበር እንዲሁም ስለ ህጻናትና አረጋውያን ያለውን ነባር ፍልስፍና ማህበረሰቡ ባሉት የሥነቃል መከወኛ መንገዶች ያቀርባል፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌያዊ አነጋገሮች የረዥምና ውስብስብ ማሳመኛዎች አጭር መገለጫዎች ናቸው የሚባለው፡፡ እነ ዶክተር ክላውድ ሰምነር እና ወርቅነህ ቀልቤሳ በሥነቃላዊ መንገድ የተላለፉትን የኢትዮጵያውያንን ፍልስፍና ከኦሮሞ ህዝብ ቋንቋና ባህል ውስጥ አውጥተው ያሳዩባቸውን ስራዎች በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቀደምት አባቶቻችን መላው አፍሪካ ባልሰለጠነበት ዘመን ቀድመው ባህላችንንና ታሪካችንን በድንጋይ ቀርጸው በብራና ጽፈው ስላስተላለፉልን ኢትዮጵያ ከስነቃላዊ ፍልስፍና ባሻገር በጽሁፍ ፍልስፍናም ተጠቃሽ ስራዎች አሏት፡፡ ምንም እንኳን በዘመናዊነት ስም ጥንታዊ ባህላችንንና ቋንቋችንን ረስተን የጽሁፍ ሃብታችንን ሳንመረምር በርካታ ዘመናትን የራሳችንን ስናንቋሽሽ የምዕራባውያንን ስናደንቅ ብናሳልፍም ጉዳዩ ያብሰለሰላቸው በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ምዕራባውን የቻሉትን ያህል ለማሰባሰብ፣ ለማጥናትና ለዓለም ለማስተዋወቅ ችለዋል፡፡ በዚህ ረገድ እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ታደሰ ታምራትና ስርግው ሃብለሥላሴ ከሃገር ውስጥ እንዲሁም ፕሮፌሰር ፓኦሎ ማራሲኒ፣ አሌሳንድሮ ባውዚ፣ ሪቻርድ ፓንክረስትና ክላውድ ሰምነር ከውጪ ሃገር ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ካናዳዊው ክላውድ ሰምነር Classical Ethiopian Philosophy በተባለው መጽሐፉ ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉሞ ያሳተማቸው የፍልስፍና ስራዎች መጽሐፈ ፊሳልግዎስ፣ አንጋረ ፈላስፋ፣ የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ፣ ሀተታ ዘርዓያዕቆብ እና ሀተታ ወልደ ህይወት   ናቸው፡፡ እነዚህ ስራዎች በተለይ አፍሪካውያን የጽሁፍ ፍልስፍና ስለሌላቸው ፍልስፍና በአፍሪካ ውስጥ የለም በሚል ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ሲሞግቱ ለነበሩ ምዕራባውያን የማያዳግም መልስ በመስጠት ለአፍሪካ የፍልስፍና ታሪክ ብርሃን የፈነጠቁ ናቸው፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ዓላማም እነዚህን የፍልስፍና ስራዎች በአጭሩ ማስተዋወቅ ይሆናል፡፡
የጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ፍልስፍና የውጪ የጥበብ ስራዎች ውርስ ትርጉምና፤ ወጥ (original) የፍልስፍና ስራዎች በመባል ይከፈላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያው ክፍለ እንደተጻፈ የሚነገርለት የመጀመሪያው የፍልስፍና የጽሁፍ ስራ መጽሐፈ ፊሳግዎስ (physiologus) ይባላል፡፡ ይህ የፍልስፍና ስራ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚነገርለትን የጥበብ ስራ ከግሪክ ወደ ግእዝ ቋንቋ በመተርጎም የተሰራ ሲሆን ትርጓሜውም ተራ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የባህልና የቋንቋ አውድ ጋር በማዛመድ የተሰራ ነው፡፡ ፊሳላግዎስ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወይም አጋማሽ አካባቢ ከፍተኛ የመጽሐፍ ክምችት በሚገኝበት ምናልባትም በግብጽ ሀገር በሚገኝ ገዳም ውስጥ በሚኖር ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ እንደተጻፈ ይገመታል፡፡ ፈላስፋው ሰምነር የጥንታዊ ድርሳናት ተመራማሪው (philologist) ፍሪትዝ ሆሜል (Hommel) በ1877 ዓ.ም በለንደን፣ ፓሪስና ቬና  ቤተመዛግብት ውስጥ የሚገኙ የግእዝ ብራና ፊሳልግዎስ መጻህፍትን ከጀርመንኛ ትርጓሜው ጋር በማገናዘብ ካዘጋጀው የተስተካከለ ቅጽ (critical edition) ላይ የተረጎመው ሲሆን ከካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ የ1951 ጣልያንኛ ትርጉም ጋርም አመሳክሮታል፡፡ ፊሳልግዎስ ለመጽሐፉ ደራሲ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን ይህም እንስሳትን፣ ዕጽዋትናና የማዕድናትን ምንነት የሚገልጽና በተምሳሌት (symbolism) የሚያስቀምጥ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠውና ሁለተኛው ክፍለ ዘመን በመባል በሚታወቀው የአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት (1434-68) መጽሐፈ ፈላስፋና የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ የተባሉ ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት ወደ ግእዝ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ ምናልባት እነዚህ ትርጉም ስራዎች እንዴት የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው ቻለ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፤ እንደ ሰምነር ማሳመኛ ምንም እንኳ ስራዎቹ ትርጉም ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን የራሳቸው የሆነ ወጥ የአተረጓጎም ስልት ስላላቸው “Ethiopians never translate literally: they adapt, modify, add, subtract. A translation therefore bears a typically Ethiopian stamp:” ማለትም በትርጉም ሂደት ላይ ከራሳቸው ባህልና አውድ ጋር ለማዋሃድ ሆነ ብለው የመጨመር፣ የመቀነስና የማሻሻል ባህል ስላላቸውና ፍጹም ኢትዮጵያዊ አሻራ አንዲኖረው በማድረግ ስለሚተረጉሙ ነው፡፡
መጽሐፈ ፍልስፍና፤ አንጋረ ፈላስፋ ወይም የፈላስፎች አነጋገር በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከ1510-1522 ዓ.ም አባ ሚካኤል በተባለ ኢትዮጵያዊ ከአረብናኛ ቋንቋ ወደ ግእዝ የተተረጎመ ነው፡፡ መጽሐፉ መጀመሪያ በግሪክ እንደተጻፈና በ809 ዓ.ም አካባቢ ሁናይን ኢብን ኢስሐቅ በተባለ የሜሶፖታምያ ተወላጅ ወደ አረብኛ ቋንቋ የተተረጎመ ነው፡፡ መጽሐፈ ፈላስፋ በ1953 ዓ.ም በሊቀመዘምራን ዕቁበጊዮርጊስ አንጋረ ፈላስፋ በሚል ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎመ ሲሆን በውስጡም ከጠቢቡ ሂቃር ጥበብ ጀምሮ፤ የቅድመ ሶቅራጠስ የግሪክ ፈላስፎችን  የሶቅራጠስን፣ የአሪስቶትልን (አሪስጣጣሊስ) በተለይ ደግሞ የፕሌቶንና (አፍላጦን) የፕሌቶን ተከታዮች አነጋገሮች አካቶ የያዘ የፍልስፍና ስራ ነው፡፡
ሦስተኛው የኢትዮጵያውያን የፍልስፍና መጽሐፍ የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ በሚል ርዕስ የተጻፈው ነው፡፡ በጀርመን ሀገር ከሚገኘው የግእዝ ብራና መጽሐፍ ላይ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የመለሰው ይህ መጽሐፍ የሲግመንድ ፍሮይድ (Oedipus complex) ንድፈ ሃሳብ የተመሰረተበትን ታሪክ በጽሁፍ ይዘው ከተገኙት አምስት የዓለማችን ቋንቋዎች (ግሪክ፣ ላቲን፣ ሲራይክ፣ አረቢክ እና ግእዝ) መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራል፤ ክላውድ ሰምነር፡፡ ከአረብኛ ቅጂ ላይ የተተረጎመው ይህ መጽሐፉ በሶስት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የስክንድስን ህይወት ታሪክ፤ ሁለተኛው ክፍል ሃያ አምስት ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን፤ እንዲሁም ሦስተኛው ክፍል ደግሞ አንድ መቶ ስምንት የፍልስፍና ጥያቄዎችንና ጠቢቡ ስክንድስ የሰጣቸውን ምላሾች ይዟል፡፡
የመጨረሻዎቹ ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት ከላይ ከቀረቡት ሦስት ስራዎች በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጽሁፍ ፍልስፍና ከጥበብ (wisdom) ስራዎች ወደ አመክኖአዊ (rational)፤ ከውርስ ትርጉም ወደ ወጥ (original) ስራነት ለመሸጋገሩ ህያው ምስክሮች ናቸውና፤ የዘርዓያዕቆብ (ወርቅዬ) እና የተማሪው የወልደ ህይወት (ምትኩ) ሐተታዎች፡፡ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን (1599-1692) የህይወት ታሪኩንና የፍልስፍና ስራዉን ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ፣ ጽፎ ያቆየልን ኢትዮጵያዊ አመክኗዊ (rational) ፈላስፋ ዘርዓዕቆብ፤ በሃይማኖተኝነቱ፣ በስነጽሁፍ ስራዎቹና በብርቱ አስተዳደሩ ከሚታወቀው የአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን (1434-68) ኢትዮጵያዊ ንጉስ አጼ ዘርዓያዕቆብ የተለየ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ አጼ ዘርዓያዕቆብ ካለፈ ከ1.5 ምዕት ዓመት በኋላ በአጼ ሱስንዮስ የንግስና ዘመን እ.ኤ.አ 1626ዓ.ም የተነሳ ፈላስፋ ሲሆን ሐተታ የተባለውን ፍልስፍና የሰራውም ለሁለት ዓመታት ያህል ለብቻው ዋሻ ውስጥ ተደብቆ በቆየባቸው ጊዜያት ነበር፡፡
የዘርዓ ያዕቆብና የተማሪው ወልደህይወት ሐተታዎች በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ “ሐተታ” የተባለው የፍልስፍና መንገድ አንድን ጉዳይ ደረጃ በደረጃ እየጠየቁ ጥልቅ ወደ ሆነ ምርምር፣ የመግባትና በዚህም አንድ እውነተኛ እውቀት ላይ የመድረስ ሂደትን ያመለክታል፡፡ ዘርዓያዕቆብ በጥንታዊት ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት፤ በንባብ ቤት፣ በዜማ ቤትና በቅኔ/ሰዋስው ቤት ያለፈ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ፈላስፋ ሲሆን እርሱ በነበረበት ዘመን የነበሩ ሃማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ሥነምግባራዊ አስተሳሰቦችን በአመክኗዊ ሐተታ (rational inquiry) በመታገዝ ይመረምርና ይተች ነበር፡፡ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የፈጣሪ ህግን ከሰው ህግ፣ የተፈጥሮ ሥርዓትን ከሰብዓዊ ሥርዓት፤መለየትንና በአንድ አምላክ አማኞች ሃማኖት ውስጥ የሚገኙ ተገቢ ያልሆኑ የሰው ሥርዓቶችን  አስወግዶ በእውነተኛው የተፈጥሮ/የፈጣሪ ህግ ብቻ መመራት ላይ ያተኩራል፡፡ በተፈጥሮ ህግና በምክንያታዊነት መነጽር በመታገዝ ስለሃይማኖት መከፋፈል፣ስለሙሴና ነቢዩ መሀመድ ህጎች፣ ሐሰተኛ እምነትን ስለመለየት፣ ስለአምላክና ስለሰው ህግ፣ስለ እውነተኛ እውቀት ምንጭ እንዲሁም ስለጋብቻና ምንኩስና ተፈላስፏል፡፡   
በአፍሪካ የጽሁፍ ፍልስፍና መገኘት የውስጥ እግር እሳት የሆነባቸው ምዕራባውያን የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የኢትዮጵያውን ስራ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ለምሳሌ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ ስራው የGiusto d’Urbino ነው ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ክላውድ ሰምነር ለዚሁ ሙግት መልስ ለመስጠት በጻፈው Ethiopian Philosophy Vol,II መጽሐፍ ላይ ጊስቶ ዲ አርቢኖ ከጻፋቸው ደብዳቤዎችና ሌሎች ስራዎች፣ ሐተታው ከተጻፈበት የቅኔ ባህል፣ እንዲሁም በጉስቶ ትዕዛዝ ስለተገለበጠው ሐተታ ጸሐፊ የግዕዝ ቋንቋ እጥረት አንጻር የማያዳግም ምላሽ ከሰጠ በኋላ የሚከተለውን ድምዳሜ አስቀምጧል፤ “MODERN PHILOSOPHY, in the sense of a personal rationalistic critical investigation, BEGAN IN ETHIOPIA with Zara’yaecob at the same time as in England and in Fracne.” በግለሰብ ፈላስፋ ደረጃ የሚካሄድ ዘመናዊ የአመክንዮ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ተጀምሯል፤ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ሀገር በተጀመረበት በተመሳሳይ ጊዜ፡፡
ዘመንፈስቅዱስ አብርሃ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ጥበብ ለአሁኑ ትውልድ ለማሳወቅ ለወደፊቱ ለማስተላለፍ ከነበረው ምሁራዊ ሃላፊነት አንጻር ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎችን ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማሳተም ለንባብ አብቅቷል፡፡ ሐተታ ዘርዓያዕቆብ ወወልደህይወትንም እ.ኤ.አ በ1955ዓ.ም በፈረንሳይ ሃገር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ግእዝ ብራና መጽሐፍ ላይ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ አሳትሟል፡፡ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ኪሮስም የፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነርን መንገድ ተከትሎ የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ከፈረንሳዊው የአውሮፓ ዘመናዊ ፍልስፍና መስራች ሬኔ ዴካርት (Rene Descartes) ሥራ ጋር በማነጻጸር የተቀረው ዓለም ኢትዮጵያ በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የነበራትን ሚና አጉልቶ አሳይቷል፡፡ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ዛሬ ሊታወቅ የቻለው ካናዳዊ ዜግነት ባለው ሰምነር አማካኝነት ነው፡፡ የውጪ ሰዎች የኛን ጥንታዊ መጻህፍት ለማጥናት ይህን ያህል ከተጉ እኛ ኢትዮጵያውንማ…፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ያልተጠኑ የበርካታ ጥንታዊ ሥነጽሁፎች ባለቤት ናት፤ ማጥናት አቅቶን ሌሎች አጥንተው የቅጂ መብቱን ከመውሰዳቸውና የታሪክ ክፍትት ተፈጥሮ በመጪው ትውልድ ተወቃሾች ከመሆናችን በፊት የዘርፉ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ ዩኒቨርስቲዎች ጉዳዩን የምርምር አቅጣጫቸው ውስጥ በማስገባት፣ ዜጎችም ጥንታዊ የጽሁፍ ሃብታችንን አስፈላጊነት በመረዳት ከዘራፊዎች በመጠበቅ ልንረባረብ ይገባል እላለሁ፡፡

Thursday, April 4, 2013

የተዛባው የዘመናዊነት አስተሳሰብ!


 Published on Addis Admass Newspaper
ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ አሪፎች፣ ጭሶች፣ ነቄዎች፣ የተማሩ ወይም የሰለጠኑ በመባል የሚታወቁት ምዕራባዊ አስተሳሰብን (የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን) የሚከተሉ፣ “ዘመናዊ ቋንቋ” የሚችሉ፣ “ዘመናዊ” ሙዚቃ የሚያዳምጡ፣ “ዘመናዊ” ምግቦችን የሚመርጡ ወይም “ዘመናዊ” አለባበሶችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ኋላቀር፣ ያልሰለጠኑ፣ ያልተማሩ ወይም ሞኞች ተደርገው የሚታሰቡት ባህላዊ (ኢትዮጵያዊ) አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላልን? ዘመናዊስ ምንድን ነው? ባህላዊና ዘመናዊ ተቃራኒ ሃሳቦች ናቸው? ዘመናዊው አስተሳሰብ ሁሉ ከባህላዊው ይበልጣል? ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ በዘመናዊ ሊተካ ይገባል? የአፍሪካዉያን አስተሳሰብ ባህላዊ ምዕራባውያን ደግሞ ዘመናዊ ማለት ይቻል ይሆን?
ለጥያቄዎቹ ሁሉ በጅምላ የምሰጠው መልስ “አይደለም” የሚል ሲሆን የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ለምን እንዳልሆነ ማስረዳት ይሆናል፡፡  ክዋሜ ጂቼ (Kwame Gyekye) የተባለው የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካዊ ፈላስፋ “Tradition and Modernity” በተባለው መጽሐፉ በአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ የተነሳ የዘመናዊነት ትርጉምና አስተሳሰብ በአፍሪካውያን ዘንድ በእጅጉ ተዛብቷል ይለናል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሳትንበረከክ በአባቶቻችን ጀግንነትና የሃገር ፍቅር ስሜት ተከብራ የቆየች ቢሆንም፤ ከምዕራባውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ከካፒታሊዝም የውድድር መንፈስ፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከሉላዊነት (globalization) የባህል ወረራ የተነሳ ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ የዘመናዊ ተቃራኒ፣ የበታችና ኋላቀር እንደሆነና በ“ዘመናዊው አስተሳሰብ” ሊተካ እንደሚገባ የሚያወሳ የተዛባ ግንዛቤ ይዘው በልበ ሙሉነት የሚሞግቱ ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ምዕራባውያን “ዘመናዊነት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጀማሪ ስለሆኑና ኢትዮጵያ ደግሞ በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ስለሆነች ዘመናዊ ለመሆን ምዕራባውያንን መምሰል አለባት በሚል የአስተሳሰብ ህጸጽ (fallacy) ተነድተው ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር እስከማቆራኘትና የራስን ባህልና ስልጣኔ እስከማንቋሸሽ የደረሱም አሉ፡፡ በአንዳንድ የኮሚውኒቲና የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ ካልሆነ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መናገር፣ ማንበብና መጻፍን እንደ አሳፋሪ ነገር ሲቆጥሩና በሚሞክሯቸው የአውሮፓ ቋንቋዎች ሲመጻደቁ መመልከት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ለጉዳዩ አሳሳቢነት እንደ ምሳሌ  መጥቀስ ይቻላል፡፡ 
በርግጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ቀድመው ከሰለጠኑ ሃገሮች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ልማትን ለማፋጠን መገልገላቸው ከበደል የሚቆጠር ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ የሌሎችን እያደነቁ የራስን ስልጣኔ መናቅ፤ የሌሎችን ባህል እያስፋፉ የራስን ማዳከምና ማጥፋት ግን ተሞክሮ ከመውሰድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር ለሚያመሳስለው የአስተሳሰብ ህጸጽ በርካታ መነሻዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “ዘመናዊ” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ መጀመሪያ ያስተዋወቁት የመካከለኛው ዘመን ምዕራባውያን ፈላስፎች ናቸው፡፡ ሞደርን (Modern) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “modo” ከሚለው የላቲን ስረወ-ቃል የተገኘ ሲሆን አሁን just now, በቅርቡ recently የሚል  ትርጉምን ያለው ነው፡፡ ይህም ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ያለውን አስተሳሰብ የሚወክልና የነባሩ አስተሳሰብ “antiquus vetus” ተቃራኒ ሆኖ እንዲያገለግል የተሰየመ ነው፡፡ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሄደው የምዕራባውያንን ትምህርት ቀስመው ወደሀገራቸው የተመለሱ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ የሚለውን ቃል ዘመኑን፣ ጊዜውን፣ ወቅቱን መሰለ የሚል ተመሳሳይ ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው ተርጉመውታል፡፡ ሀገሪቱን ዘመናዊ ከማድረግ አንጻርም ባህላዊ አሰራር ኋላ ቀር ዘመናዊው (ምዕራባዊው) ግን የተሻለ በሚል ፍልስፍና ነባር ባህላዊ የህክምና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦቻችንና ስልጣኔዎቻችን ሙሉ በሙሉ ተሸረው በምዕራባውያን አሰራሮች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡
የተሻሉ የአውሮፓ አሰራሮችን ተሞክሮ መውሰዱ ባልከፋ ነበር፤ ችግሩ ግን ተሞክሮዎቹን የወሰድነው በራሳችን ነባር ባህላዊ አስተሳሰብና ስልጣኔ ላይ ተመስርተን ወይም በነበረን ባህላዊ እውቀት ላይ ቀጥለን ሳይሆን በዘመናዊነት ስም የነበረንን አቃለን፣ ንቀንና ጥለን የምዕራባውያንን ባህል ከነቋንቋቸው ከእኛ አውድ ጋር ሳናጣጥም መውረሳችን ነው፡፡ ለምሳሌ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በግዕዝ፣ በአረብኛና በአማርኛ የተጻፉ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የህግ፣ የስነጽሁፍ መጻህፍት እያላት በእነርሱ ላይ ያለውን ስልጣኔ ለማጥናት በኢትዮጵያ የኒቨርስቲዎች ውስጥ የፊሎሎጂ (የጥንታዊ ድርሳናት ጥናት) ትምህርት አለመስፋፋቱ ለራሳችን ነባር ስልጣኔ ያለንን ዝቅተኛ ግምት የሚመሰክር ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምዕራባውያን በጀርመን፣ በኢጣልያ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ እንዲሁም በሎሎች ሃገሮች የኒቨርስቲዎቻቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከፍተው ጥንታዊውን ግእዝንና ሌሎች ቋንቋዎቻችንን አጥንተው፤ እኛ የናቅናቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ድርሳናት ገሚሶቹን በግዥ፣ ሌሎችን ባልታወቀ መንገድ፣ የቀሩትን ደግሞ በማይክሮ ፊልም ቀርጸው በማሰባሰብ ጥናትና ምርምር አካሂደውባቸዋል፤ በርካታ ቁም ነገሮችንም ቀስመውባቸዋል፡፡ የሚያስገርመው ነገር ምዕራባውያን ዛሬም ጥንታዊ ጽሁፎቻችንን በዲጂታይዚንግ ቴክኖሎጂ በማሰባሰብና በማጥናት የቅጂ ባለመብት በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
ነባርና ባህላዊ የሆነውን እውቀታችንን ለማቃለልና የምዕራባውያንን አስተሳሰብ ብቻ ትክክል እንደሆነ ተቀብለን ለመጓዝ የበቃንበት ሌላው ምክንያት ዘመናዊና ባህላዊ ተቃራኒዎች እንደሆኑ አድርገን የምናስብበት ስር የሰደደ የተሳሳተ ፍልስፍናችን ነው፡፡ ዘመናዊ የባህላዊ ተቃራኒ ነው የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትክክል የሚቆጠረው “ካለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” እንዲሉ አንድ የተለመደን አስተሳሰብ እንደ እውነተኛ የመቀበል አባዜ ስለተጠናወተን  ነው፡፡ ነገር ግን የዚህን ማሳመኛው አወቃቀር በጥልቀት ብንመረምር ይህ አስተሳሰብ እጅግ ወደ ከፋ ድምዳሜ ሊወስደን እንደሚችል መመልከት ይቻላል፡፡ ዘመናዊ የአሁን፣ የቅርብ ጊዜ፣ ባህላዊ ደግሞ የቆየ፣ የጥንት አስተሳሰብ ነው፤ የሚለውን እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፤ ስልጣኔ ዝግመታዊ እድገት ስለሆነና የቅርብ ጊዜው አስተሳሰብ ከቆው የተሸለ ስለሆነ፤ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው አስተሳሰብ የተሻለ ነው ማለት ነው፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው የተሻለ ነው ብለን ከተቀበልን፤ ዘመናዊው የምዕራባውያኑ ባህልና አስተሳሰብ ከእኛ ባህልና አስተሳሰብ የተሻለ ነው የሚለውን ድምዳሜ አበወንታ መቀበል አመክኗዊ ይሆናል፤ ስለሆነም የኛን ነባር ባህሎች፣ አስተሳሰቦችና አሰራሮች ሙሉ በሙሉ ንቀን በመተው በዘመናዊው የምዕራባውያን አስተሳሰብ መተካት አለብን፤ የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፡፡
ይሁናና ዘመናዊና ባህላዊ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንጂ ተቃራኒ ሃሳቦች አይደሉም፤ ምክንያቱም ሁለት ሃሳቦች ተቃራኒ ናቸው ካልን አንዱ ባለበት ሌላው መገኘት አይኖርበትም ማለታችን ነው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊና ባህላዊ አስተሳሰቦች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ “ዘመናዊ አስተሳሰብ የምዕራባውያን ባህላዊ ደግሞ የአፍሪካውያን ወይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች መገለጫ” የሚለውም አስተሳሰብም አንዲሁ የተሳሳተ ነው፤ ምክንያቱም በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ባህላዊ እና ዘመናዊ አስተሳሰቦች ይኖራሉና፡፡ ይልቁንም የራሳችን ነባር ባህላዊ ዕውቀት ተገቢውን ክብር ሰጥተን በማጥናት የጎደለው ካለ ለመሙላት ከምዕራባውያን ዘመናዊ አሰራር ጋር ማዋሃዱ ብልህነት ነው፡፡   ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከምዕራባውያንን የህክምናና የመድኃኒት ቅመማ ሳይንስን ስንወስድ ነባሩን ባህላዊ ህክምና ጥበብ ሳንንቅ አስቀድመን በማጥናት የሚጠቅመንን ቁም ነገሮች በመውሰድ ሁለቱን ማጣጣም ብንችል ኖሮ በህክምናው ዘርፍ አሁን ከደረስንበት የተሻለ ዕድገት ማስመዘገብ ይቻል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ቻይናውያንን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵውያን ጥንታዊ የሽመና ጥበብ የሚመረቱ ባህላዊ ልብሶችን ኋላቀር ናቸው፣ ለሥራ አይመቹም፤ በሚል ንቀን በመተው በምዕራባውያንን የአለባበስ ባህል ለምሳሌ ጂንስ (jeans) መሰል ልብሶችን ባህላችን ባናደርግ፤ ባህላዊ የሽመና ጥበባችንን ከምዕራባውያን ሳይንስ ጋር ብናዋህደውና፤ ህዝባችን በየዕለቱ ባህላዊ ልብሶቻችንን በጠቀም እንዲችል አድርገነው ቢሆን ኖሮ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ምን ያህል በሄድን፤የውጪ ምንዛሬ ምንያህል በቀነስናና፤ ለዜጎቻችን ምን ያህል የሥራ ዕድል በከፈትን ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በራሳችን ባህላዊ እውቀትና ምርት ላይ እምነት ቢኖረንና እርሱንም በምርምር አዳብረነው ባህላዊ አልባሳቶቻቸንን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ብንችል ኖሮ ቡናና ሰሊጥ ወደውጪ ከምንልከው የበለጠ ኩታና እጀ ጠባብ በላክን ነበር፡፡ 
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘመናዊነት ምንም እንኳ በምዕራባውያን ቢጀመርም የምዕራባውያን ባህል መገለጫ አይደለም፡፡ ልክ አውሮፓ ውስጥ ዘመናዊ ባህል እንዳለ ሁሉ አፍሪካ ውስጥም ከአውሮፓ ያልመጣ የራሷ የሆነ ዘመናዊ ባህል አላት፤ ዘመናዊነትን በተገቢው ሁኔታ ከተቀበልነው፡፡  በተመሳሳይ ልክ አፍሪካ ውስጥ ባህላዊ አስተሳሰብ እንዳለ ሁሉ ምዕራባውያንም የራሳቸው የሆነ ባህላዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የገና በዓል ሲከበር የሚዘጋጀው የገና ዛፍ (christmas tree) ልማድ ለኢትዮጵያውን ዘመናዊ ባህል ሲሆን ለምዕራባውያን ግን ነባር ባህላዊ ተግባራቸው ነው፡፡
የዘመናዊና ባህላዊ ዲስኩር (discourse) ጥልቅ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለውና የምዕራባውንን ስልጣኔ ታሪካዊና ታሪካዊ ዳራ (background) በጥልቀት መገንዘብን የሚጠይቅ ስለሆነ በሁሉም ደረጃ ላሉ ዜጎች በእኩል ደረጃ ሊረዱት አይችሉም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ስሁል መስተሃልይ የሌላቸው ግለሰቦች የተለመደንና ሰፊው ህዝብ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውን ነገር ያለምንም ጥያቄ ትክክል ነው ብለው ስለሚቀበሉና ምንም ዓይነት ፍተሻ ስለማደርጉ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ Africa’s Quest for a Philosophy of Decolonization በተባለ መጽሐፉ ላይ ለዚህ መፍትሄው ዜጎችን በፍልስፍና ትምህርት ቀርጾ በድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካ ያሉትን ነባራዊ ሁነታዎች በድጋሜ በማጥናት ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱና የተዛባ አስተሳሰብ የሚታይባቸውን እንደ ዘመናዊነትን የመሰሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሃሳቦች ትርጉም በመሻር (deconstruction) እንደ አዲስ ከእኛ አውድ ጋር አስታርቆ መበየን (reconstruction) ነው ይላል፡፡ ሌላው አፍሪካዊ ፈላስፋ ፀናይ ሰረቀብርሃን “The Critique of Eurocentrism and the Practice of African Philosophy” በተባለ ጽሁፉ አፍሪካውያን በዘመናዊነትና በሉላዊነት ሳቢያ በአውሮፓውያን እየደረሰባቸው ስላለው የባህል ተጽዕኖና ስለማምለጫ መንገዶቹ ሲጽፍ የአፍሪካውያን ፍልስፍና Historico-Hermeunitical የተባለውን መንገድ በመከተል የአፍሪካውያንን ችግሮች ከታሪካዊ ዳራ ትንታኔ በመነሳት እንደገና ማሰብና የተጣመመውን ማቃናት፤ የጎደለውን መሙላት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ሪቻርድ ቤልና ክዋሜ ጂቼም ዘመናዊና ባህላዊን በማቃረን አንዱን የበላይ አድርጎ በክብር ሌላውን ደግሞ የበታች አድርጎ በንቀት በማየት ነባሩን ባህላዊ እሴቶቻችንን ጨርሶ ከማጥፋታችን በፊት ወደ ኋላ ወደ ነባሩ ባህላዊ አስተሳሰባችን፣ ድርጊታችንና እሴቶቻችን ተመልሰን እያንዳንዱን ባህላዊ እሴት በራሳችን አውድ በድጋሚ ካሰብንና  ከመረመርን (rethinking) በኋላ አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን በድጋሚ ዋጋ ልንሰጣቸው (revaluation) ወይም በድጋሜ ወደ ህይወት ልንመልሳቸው (revitalization) ይገባል በማለት ይመክራሉ፡፡ 

ለሌሎች “ጥሩ” የሆነው ላንተ “መጥፎ” ሊሆን ይችላል !


 Published on Addis Admass Newspaper
ዓለማችን በበርካታ ተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ የተቃራኒዎች መኖር ደግሞ ለዓለም መገኛ ምንጭና የህልውና እስትንፋስ መሆናቸውን ይናገራሉ፤ ሄራክሊተስና ተከታዮቹ፡፡ ጨለማና ብርሃን ፣ጥላቻና ፍቅር ፣ግራና ቀኝ፣ ውሸትና እውነት፣ መሃይምና ምሁር፣ ድህነትና ሃብት፣ ረሃብና ጥጋብ፣ ንፉግነትና ቸርነት፣ ጭካኔና ርህራሄ፣ ፍርሃትና ድፍረት የመሳሰሉት ጥንድ ቃላት በተቃራኒነት ይታወቃሉ፡፡ ምንም እንኳን የአንዱ ጥንድ ቃል  የተቃርኖ ሁኔታ ከሌላው በእጅጉ የሚለያይ ቢሆንም ከጥንዶቹ አንዱ ሁልጊዜ በክፉ ሌላው ደግሞ በበጎ ክፍል መመደባቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጨለማ፣ ግራ፣ ጥላቻ፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ በመጥፎ እንዲሁም ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ሃብት፣ ቀኝ፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ደግሞ በጥሩ ምድብ መካተታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ጥላቻ፣ ውሸት፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ “ሁልጊዜ መጥፎ ናቸው” ብሎ በርግጠኝነት መናገር ይቻል ይሆን?  በሌላ በኩል ደግሞ ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ሁልጊዜ ጥሩ ድርጊቶች ናቸው ብሎ ለመናገርስ የሚደፍር ይኖር ይሆን?
በርግጥ ፍጹማውያን (objectivist) ፈላስፎች ይህን በርግጠኝነት ለማለት ይደፍራሉ፤ ምክንያቱም በእነርሱ እምነት አንድ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት ጥሩ ከተባለ በየትኛውም ዘመን በማንኛውም ቦታ ጥሩ ነው፤ እንዲሁም መጥፎ ከተባለ ምንም ጊዜ የትም ቦታ መጥፎ ነውና፡፡ ለምሳሌ የውሻና የአሳማ ሥጋ መመገብ ነውር ከሆነ በማንኛውም ዘመን በየትኛውም ሀገር ባህል ነውር ነው ማለት ነው፡፡ ይሁንና በሌላ ጎራ የሚገኙ አንጻራውያን (relativist) ፈላስፎች ደግሞ አንድ ድርጊት በተመሳሳይ ጊዜ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል፤ ስለሆነም አንድን የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት አብነት አንስቶ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ ከመበየን በፊት ደርጊቱ በየትኛው ዘመን፣ በማን ባህል፣ በማን ሃይማኖት በአጠቃላይ ከምን አንጻር የሚለውን ነገር ማጥናት ያስፈልጋል ሲሉ ማሳመኛ ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ “አንድ ወንድ ባል ለአንድ ሴት ሚስት ወይም አንድ ሴት ሚስት ለአንድ ወንድ ባል” (monogamy) ብቻ ትክክለኛ የጋብቻ ፍልስፍና እንደሆነ በርካቶች የሚግባቡበት ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በተቃራኒው አንድ ወንድ ባል ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሴት ሚስቶች (polygamy) የጋብቻ ፍልስፍና የሚፈቅዱና የሚያራምዱ በርካታ ባህሎችና ሃይማኖቶችም መኖራቸውም እሙን ነው፡፡ ታዲያ ትክክለኛው የጋብቻ ስነ ምግባር የትኛው ነው? ለምን? ከማን አንጻር?
ከዚህም ባሻገር ለብርሃን መኖር ጨለማ፣ ለእውነት መኖር ውሸት መኖራቸው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ በተቃራኒዎች ውስጥ የሚገኙ የመጥፎ ነገሮች መኖርም በራሱ አስፈላጊ መጥፎነት (necessary evil) ነው በሚል የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለምሳሌ “ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል” እና “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚሉት የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የክፉ ሰዎች በእኛ ዙሪያ መኖር ምን ያህል አስፈላጊና ለትጋታችን መነሻ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡
ፍልስፍና በፍጹማውያንንና በአንጻራውያን እይታ ዘርፈ ብዙ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ መጠን ውስብስብ ከሆኑ የስነ ምግባር ፍልስፍና ንድፈ ሃሳቦች (moral theories) ጀምሮ በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በሳይንስና፣ በአካባቢያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚነሱ አወዛጋቢ በስነ ምግባር አጀንዳዎችን (controversial moral issues) በጥልቀት መርምሮ አንድ  በአመክኗዊ አቋም ላይ እስከ መድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህ የስነ ምግባር አቀራረብ ተግባራዊ ስነ ምግባር (applied ethics) ይባላል፡፡ ተግባራዊ ስነ ምግባር ለሙያዊ የስነ ምግባር (professional ethics) ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚወጡ ህጎችና ደንቦች (legal codes) መንገድ ቀዳጅ ነው፡
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያገኙና ትክክለኛ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የተግባራዊና የሙያዊ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ነገር ግን ጥልቅ ምርምርን የሚሹ አስተሳሰቦች በፍልስፍና መነጽር ሲቃኙ ምን አይነት ስህተት አንዳለባቸው ማሳየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የምናነሳው የሰው ልጅ በእንስሳት፣ በእጽዋት፣ በመሬት፣ በከባቢ አየርና በሌሌች ረቂቅና ግዙፍ ፍጥረታት ላይ ስለሚፈጽመው የስነምግባራዊ ግድፈት የሚያትተውን አካባቢያዊ ስነ ምግባር (environmental ethics) ነው፡፡
በነባሩ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር  አስተምህሮ ስነ ምግባር በዋነኝነት የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው፡፡ ይህም ማለት አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን ለመገምገም የምንችለው ድርጊቱ በሰው ልጆች፣ ለሰው ልጆች ወይም የሰው ልጆች ላይ ብቻ የሚፈጸም ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላን ሰው በጭካኔ ሲደበድብ ብንመለከት ደብዳቢው ግለሰብ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነው እንላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አንድ ውሻን ደብድቦ ሲገድለው ብንመለከት ገዳዩ ስነ ምግባር የጎደለው ሰው ተብሎ አይታሰብም፤ ምክንያቱም እንስሳት እንደ ሰው ልጆች የሞራል አቋም የላቸውምና፡፡
ነገር ግን በዘመናችን የተነሱ የአካባቢ ፍልስፍና ሊቃውንት (environmental philosophers) ስነ ምግባር ለሰው ልጆች ብቻ የሚሰጥ ጽንሰ ሃሳብ ሳይሆን በአጠቃላይ ለፕላኔታችን ለመሬት፣ ለእንስሳት፣ ለእጽዋት እንዲሁም በምድራችን ላይ ለሚገኙ ሌሎች ህይወት ያላቸውና ህይወት ለሌላቸው ነገሮች ሁሉ የሚተገበር ሃሳብ መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ነባሮቹ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር ሊቃውንት (ethicists) “ስነ ምግባር የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው” የሚል ስህተት የፈጸሙት ስለ ተፈጥሮ የነበራቸው አመለካከት ጠባብና የተሳሳተ ስለነበረ ነው ይለናል፤ ኖርዌጅያኑ የአካባቢ ፈላስፋ አረን ኒአስ፡፡ ኒአስ በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ “ተፈጥሮ ለራሷ” (Deep ecology) በመባል የሚታወቀውን የአካባቢ እንክብካቤ ንቅናቄን ሲመሰርት በተፈጥሮ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት ዓላማ የሰውን ልጅ ፍላጎት ለማርካት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሰረተውን የ“ተፈጥሮን ለሰው ልጅ”  (Shallow ecology) አስተምህሮ ይቃወማል፡፡ የ “ተፈጥሮን ለሰው ልጅ” አስተምህሮ ከአንድ አምላክ አማኞች ማለትም ከአይሁድ፣ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖት የስነ-ፍጥረት አስተምህሮት ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ይህም ሰው ፍላጎቱን ለማርካት ደን ቢመነጥር፣ እንስሳትን አርዶ ቢመገብ ወይም አካባቢን ቢበክል ከስነ ምግባር ውጪ እንደሆነ አይቆጠርም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡
የ“ተፈጥሮ ለራሷ” ፍልስፍና በዓለማችን ላይ የሚገኙ ህይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው እንጂ የሰው ልጅ ፍላጎትን ለማሟላት አይደለም፤ ስለሆነም ለሰው ልጅ ፍላጎት በሚል በተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት ብዝበዛ ከተሳሳተ “ሰው ተኮር” (anthropocentric) ምልከታ የመነጨና ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ይላሉ፤ ኒአስና ተከታዮቹ፡፡ “ሰው ተኮር ያልሆነ” (non-anthropocentric) የአካባቢ ስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች የአካባቢ ተቆርቋሪዎች፣ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እና የመሳሰሉትን መለያዎችን አንግበው መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራትን በመመስረት ለአካባቢ ስነ ምግባር መጠበቅ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ ክልሎች በአህዮች ደህንነት ዙሪያ በመስራት ላይ የሚገኘው “The Donkey Sanctuary”  የተባለውና መቀመጫውን በእንግሊዝ ሃገር ያደረገው ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሀገራችን የእንስሳት መብት ተሟጋችነት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእንስሳት መብት ተሟጋቾች እምነት እንስሳት እንደ ሰው የደስታ፣ የሃዘንና የስቃይ ስሜት እንዲሁም የራሳቸው የተፈጠሩበት ዓላማ ያላቸው በመሆኑ ሰው እንደ እቃ ሊቆጥራቸውና ያለአግባቡ ተገልግሎ ሊጥላቸው አይገባም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአህዮችና በጋሪ ፈረሶች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ስነምግባራዊ ብዝበዛ ለማስቆም በጎ ፈቃደኞቹ እንስሳቱ በጉብዝናቸው ወቅት ካቅማቸው በላይ እንዳይሰሩ፣ በህመማቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ጥረት መደረግ አለበት ይላሉ፡፡      
ከእንስሳት መብት ባሻገር ስለ ተፈጥሯዊ አካባቢ ብክለትና መቆርቆዝ፣ እንዲሁም በዚህም ሳቢያ በሰው ልጆችና በሌሎች ፍጥረታት ላይ እየደረሰ ስለሚገኘው ጉዳት የስነምግባር ተጠያቂነትም ድምጻቸውን ያሰማሉ፤ የአካባቢ ስነምግባር ፈላስፎች፡፡ በሉላዊ የካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠን ማሻቀብ ሳቢያ በፕላኔታችን በምድርና በከባቢ አየሯ ላይ እየተፈጠረ ላለው የሙቀት መጨመር፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣ የመሬት መራቆትና ድርቅ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ቀውሶች ሰለባ እየሆነ ያለው በጠቅላላው የዓለም ህዝብ ነው፡፡ በርግጥ የቀውሱ ምክንያት የሆኑት አካላት በሰው ተኮር አካባቢያዊ ፍልስፍና ተገፍተው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዓለምን እየመሩ ያሉት ጥቂት የዓለማችን ሃገራት ናቸው፡፡ ይሁንና የችግሩ ሰለባዎች በኢንዱስትሪው ዓለምን እየመሩ የሚገኙ ሃገሮች ብቻ ሳይሆኑ  ምንም ያላጠፉ በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮችም ጭምር ናቸው፡፡ ይህም ከስነ ምግባር መርኆዎች አንጻር ኢፍትሃዊ ነው፡፡ በመሆኑም ለካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠንም ለየሃገሮቹ ውሱን ኮታ ሊሰጥና የበለጸጉት በካይ ሃገሮች ያለኃጢአታቸው የቀውሱ ሰለባ ለሆኑ ደሃ ሃገሮች ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚል አቋም ይዘውም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጉባዔዎችና አህጉራዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው ቀጣይነት ያለው ልማት (sustainable Development) ስትራተጂና አፍሪካውያንን ወክለው ያቀረቡት የአየር ብክለት ካሳ ጥያቄ በዚህ የስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች ጎራ ሊያስመድባቸው እንደሚችል የአረንጓዴው ኢኮኖሚ ሊቅ ሚካኤል ስትሬት (Michael Street) በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡
ስነ ምግባር የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስ ስኬታማ ከማድረግ ጀምሮ ወንጀል እንዳይስፋፋ፣ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ፣ ሀገር እንደ ሀገር እንዲቀጥል፣ ከዚህም አልፎ የአንድ ሃገር ህዝቦች ከሌላው ጋር መግባባት እንዲችሉና በአጠቃላይ በዓለም ህዝብ ዘንድ መከባበር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲኖር የማድረግ አቅም ያለው የፍልስፍና ጥናት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ሀገር ልማት ላይ ስነ ምግባር ስለሚኖረው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ የልማት ስነ ምግባር (Developmental Ethics) ባለሙያዎች ያስተምራሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ራሞሴ ያሉ የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ፈላስፎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ያደጉት ወይም የልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታት በስነ ምግባር መዝቀጥ በማደግ ላይ ለሚገኙት ሀገሮች የእድገት እንቅፋት መሆናቸውን አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ በኒውክለር ኃይል አጠቃቀም፣ በዓለም አቀፍ የልማት ብርድና እርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ በልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታትና እንደ (IMF, World Bank) ባሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም የስነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በሶሪያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የበሽር አላሳድ መንግስትና ተቃዋሚዎቹ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማብቃት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አወንታዊ ጣልቃ ገብነትን ሩሲያ አጥብቃ መቃወሟ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ገቢዋ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን እንደማይቀር የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል “በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና” በኢራን መንግስት መካከል የተፈጠረው የኒውክለር ኃይል ማብላላት ጋር የተገናኘው ፖለቲካዊ ውጥረት አንዱ መነሻ የስነ ምግባር አጀንዳ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እንደ አሜሪካና ሩሲያ ያሉ የኒውክለር ባለቤቶች ከኒውክለር የጸዳች ሰላማዊ ዓለም የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም ራሳቸው የኒውክለር ጦር መሳሪያዎችን ሳያስወግዱ ሌሎች የማብላላት ፕሮግራማቸውን እንዲያቋርጡ መወትወታቸው ሁኔታውን ከፖለቲካ ወደ ስነምግባር ምህዳር አምጥቶታል፡፡ በኢራንና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ የዚህ እውነታ አንዱ ነጸብራቅ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ልትሰራ ላሰበችው ግድብና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ጠይቃ መከልከሏ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስነ ምግባር መዝቀጥ በታዳጊ ሃገሮች እድገት ላይ ምን ያህል ጫና እንደሚሳርፍ በግልጽ ማሳየት የሚችል ሌላው ሃቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ በህክምና፣ በንግድ፣ ሌሎች ሙያዎች ውስጥ አከራካሪ የሆኑ በርካታ የስነ ምግባር አጀንዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከአድራጊው፣ ከአስደራጊው፣ ከአደራራጊው፣ ከማህበረሰቡ ባህላዊ እሴትና ከህግ እይታ አንጻር ትክክል ወይም ስህተት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በህክምና ሙያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱ የውርጃና የምህረት ግድያን (euthanasia) የመሳሰሉ አወዛጋቢ የስነ ምግባር ጥያቄዎች  ለአንዱ ትክክል ሲሆኑ ለሌላው ደግሞ ስህተት ናቸው፡፡ በመሆኑም ግለሰቦች የሰዎችን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለው ከመፈረጃቸው በፊት እንዲሁም የስነ ምግባር ደንብ አርቃቂዎችና ህግ አውጪዎች ድንጋጌዎቻቸውን ከማወጃቸው በፊት፤ ወይም ሀገሮች በሌላው ሃገር ላይ ጣታቸውን ከማንሳታቸው በፊት በሰነዱ ላይ የተፈቀዱትን ወይም የተከለከሉትን ድርጊቶች በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ፍልስፍና መነጽሮች መቃኘታቸውንና ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡