Published on Addis Admass Newspaper
ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ አሪፎች፣ ጭሶች፣ ነቄዎች፣ የተማሩ ወይም የሰለጠኑ በመባል የሚታወቁት ምዕራባዊ አስተሳሰብን (የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን) የሚከተሉ፣ “ዘመናዊ ቋንቋ” የሚችሉ፣ “ዘመናዊ” ሙዚቃ የሚያዳምጡ፣ “ዘመናዊ” ምግቦችን የሚመርጡ ወይም “ዘመናዊ” አለባበሶችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ኋላቀር፣ ያልሰለጠኑ፣ ያልተማሩ ወይም ሞኞች ተደርገው የሚታሰቡት ባህላዊ (ኢትዮጵያዊ) አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላልን? ዘመናዊስ ምንድን ነው? ባህላዊና ዘመናዊ ተቃራኒ ሃሳቦች ናቸው? ዘመናዊው አስተሳሰብ ሁሉ ከባህላዊው ይበልጣል? ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ በዘመናዊ ሊተካ ይገባል? የአፍሪካዉያን አስተሳሰብ ባህላዊ ምዕራባውያን ደግሞ ዘመናዊ ማለት ይቻል ይሆን?
ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ አሪፎች፣ ጭሶች፣ ነቄዎች፣ የተማሩ ወይም የሰለጠኑ በመባል የሚታወቁት ምዕራባዊ አስተሳሰብን (የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን) የሚከተሉ፣ “ዘመናዊ ቋንቋ” የሚችሉ፣ “ዘመናዊ” ሙዚቃ የሚያዳምጡ፣ “ዘመናዊ” ምግቦችን የሚመርጡ ወይም “ዘመናዊ” አለባበሶችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ኋላቀር፣ ያልሰለጠኑ፣ ያልተማሩ ወይም ሞኞች ተደርገው የሚታሰቡት ባህላዊ (ኢትዮጵያዊ) አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላልን? ዘመናዊስ ምንድን ነው? ባህላዊና ዘመናዊ ተቃራኒ ሃሳቦች ናቸው? ዘመናዊው አስተሳሰብ ሁሉ ከባህላዊው ይበልጣል? ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ በዘመናዊ ሊተካ ይገባል? የአፍሪካዉያን አስተሳሰብ ባህላዊ ምዕራባውያን ደግሞ ዘመናዊ ማለት ይቻል ይሆን?
ለጥያቄዎቹ ሁሉ በጅምላ የምሰጠው መልስ “አይደለም” የሚል ሲሆን የዚህ
ጽሁፍ ዓላማም ለምን እንዳልሆነ ማስረዳት ይሆናል፡፡ ክዋሜ ጂቼ
(Kwame Gyekye) የተባለው የድህረ ቅኝ ግዛት
አፍሪካዊ ፈላስፋ “Tradition and Modernity” በተባለው መጽሐፉ በአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ የተነሳ የዘመናዊነት
ትርጉምና አስተሳሰብ በአፍሪካውያን ዘንድ በእጅጉ ተዛብቷል ይለናል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሳትንበረከክ
በአባቶቻችን ጀግንነትና የሃገር ፍቅር ስሜት ተከብራ የቆየች ቢሆንም፤ ከምዕራባውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ከካፒታሊዝም የውድድር
መንፈስ፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከሉላዊነት (globalization) የባህል ወረራ የተነሳ ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ የዘመናዊ ተቃራኒ፣
የበታችና ኋላቀር እንደሆነና በ“ዘመናዊው አስተሳሰብ” ሊተካ እንደሚገባ የሚያወሳ የተዛባ ግንዛቤ ይዘው በልበ ሙሉነት የሚሞግቱ
ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ምዕራባውያን “ዘመናዊነት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጀማሪ ስለሆኑና ኢትዮጵያ ደግሞ
በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ስለሆነች ዘመናዊ ለመሆን ምዕራባውያንን መምሰል አለባት በሚል የአስተሳሰብ ህጸጽ
(fallacy) ተነድተው ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር እስከማቆራኘትና የራስን ባህልና ስልጣኔ እስከማንቋሸሽ የደረሱም አሉ፡፡
በአንዳንድ የኮሚውኒቲና የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ ካልሆነ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው
መናገር፣ ማንበብና መጻፍን እንደ አሳፋሪ ነገር ሲቆጥሩና በሚሞክሯቸው የአውሮፓ ቋንቋዎች ሲመጻደቁ መመልከት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን
ለጉዳዩ አሳሳቢነት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በርግጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ቀድመው ከሰለጠኑ ሃገሮች የሳይንስ፣
የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ልማትን ለማፋጠን መገልገላቸው ከበደል የሚቆጠር ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን “ፍየል
ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ የሌሎችን እያደነቁ የራስን ስልጣኔ መናቅ፤ የሌሎችን ባህል እያስፋፉ የራስን ማዳከምና ማጥፋት ግን
ተሞክሮ ከመውሰድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር ለሚያመሳስለው የአስተሳሰብ ህጸጽ በርካታ
መነሻዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “ዘመናዊ” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ መጀመሪያ ያስተዋወቁት የመካከለኛው ዘመን ምዕራባውያን ፈላስፎች
ናቸው፡፡ ሞደርን (Modern) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “modo” ከሚለው የላቲን ስረወ-ቃል የተገኘ ሲሆን አሁን just
now, በቅርቡ recently የሚል ትርጉምን ያለው ነው፡፡ ይህም
ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ያለውን አስተሳሰብ የሚወክልና የነባሩ አስተሳሰብ “antiquus vetus” ተቃራኒ ሆኖ እንዲያገለግል
የተሰየመ ነው፡፡ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሄደው የምዕራባውያንን ትምህርት ቀስመው ወደሀገራቸው የተመለሱ ቀደምት ኢትዮጵያውያን
ዘመናዊ የሚለውን ቃል ዘመኑን፣ ጊዜውን፣ ወቅቱን መሰለ የሚል ተመሳሳይ ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው ተርጉመውታል፡፡ ሀገሪቱን ዘመናዊ
ከማድረግ አንጻርም ባህላዊ አሰራር ኋላ ቀር ዘመናዊው (ምዕራባዊው) ግን የተሻለ በሚል ፍልስፍና ነባር ባህላዊ የህክምና፣ የትምህርት፣
የግብርና፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦቻችንና ስልጣኔዎቻችን ሙሉ በሙሉ ተሸረው በምዕራባውያን አሰራሮች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡
የተሻሉ የአውሮፓ አሰራሮችን ተሞክሮ መውሰዱ ባልከፋ ነበር፤ ችግሩ ግን
ተሞክሮዎቹን የወሰድነው በራሳችን ነባር ባህላዊ አስተሳሰብና ስልጣኔ ላይ ተመስርተን ወይም በነበረን ባህላዊ እውቀት ላይ ቀጥለን
ሳይሆን በዘመናዊነት ስም የነበረንን አቃለን፣ ንቀንና ጥለን የምዕራባውያንን ባህል ከነቋንቋቸው ከእኛ አውድ ጋር ሳናጣጥም መውረሳችን
ነው፡፡ ለምሳሌ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በግዕዝ፣ በአረብኛና በአማርኛ የተጻፉ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የህግ፣
የስነጽሁፍ መጻህፍት እያላት በእነርሱ ላይ ያለውን ስልጣኔ ለማጥናት በኢትዮጵያ የኒቨርስቲዎች ውስጥ የፊሎሎጂ (የጥንታዊ ድርሳናት
ጥናት) ትምህርት አለመስፋፋቱ ለራሳችን ነባር ስልጣኔ ያለንን ዝቅተኛ ግምት የሚመሰክር ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምዕራባውያን በጀርመን፣
በኢጣልያ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ እንዲሁም በሎሎች ሃገሮች የኒቨርስቲዎቻቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከፍተው ጥንታዊውን
ግእዝንና ሌሎች ቋንቋዎቻችንን አጥንተው፤ እኛ የናቅናቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ድርሳናት ገሚሶቹን በግዥ፣ ሌሎችን ባልታወቀ
መንገድ፣ የቀሩትን ደግሞ በማይክሮ ፊልም ቀርጸው በማሰባሰብ ጥናትና ምርምር አካሂደውባቸዋል፤ በርካታ ቁም ነገሮችንም ቀስመውባቸዋል፡፡
የሚያስገርመው ነገር ምዕራባውያን ዛሬም ጥንታዊ ጽሁፎቻችንን በዲጂታይዚንግ ቴክኖሎጂ በማሰባሰብና በማጥናት የቅጂ ባለመብት በመሆን
ላይ ይገኛሉ፡፡
ነባርና ባህላዊ የሆነውን እውቀታችንን ለማቃለልና የምዕራባውያንን አስተሳሰብ
ብቻ ትክክል እንደሆነ ተቀብለን ለመጓዝ የበቃንበት ሌላው ምክንያት ዘመናዊና ባህላዊ ተቃራኒዎች እንደሆኑ አድርገን የምናስብበት
ስር የሰደደ የተሳሳተ ፍልስፍናችን ነው፡፡ ዘመናዊ የባህላዊ ተቃራኒ ነው የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትክክል
የሚቆጠረው “ካለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” እንዲሉ አንድ የተለመደን አስተሳሰብ እንደ እውነተኛ የመቀበል አባዜ ስለተጠናወተን ነው፡፡ ነገር ግን የዚህን ማሳመኛው አወቃቀር በጥልቀት ብንመረምር ይህ አስተሳሰብ
እጅግ ወደ ከፋ ድምዳሜ ሊወስደን እንደሚችል መመልከት ይቻላል፡፡ ዘመናዊ የአሁን፣ የቅርብ ጊዜ፣ ባህላዊ ደግሞ የቆየ፣ የጥንት
አስተሳሰብ ነው፤ የሚለውን እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፤ ስልጣኔ ዝግመታዊ እድገት ስለሆነና የቅርብ ጊዜው አስተሳሰብ ከቆው የተሸለ
ስለሆነ፤ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው አስተሳሰብ የተሻለ ነው ማለት ነው፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው የተሻለ ነው ብለን
ከተቀበልን፤ ዘመናዊው የምዕራባውያኑ ባህልና አስተሳሰብ ከእኛ ባህልና አስተሳሰብ የተሻለ ነው የሚለውን ድምዳሜ አበወንታ መቀበል
አመክኗዊ ይሆናል፤ ስለሆነም የኛን ነባር ባህሎች፣ አስተሳሰቦችና አሰራሮች ሙሉ በሙሉ ንቀን በመተው በዘመናዊው የምዕራባውያን አስተሳሰብ
መተካት አለብን፤ የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፡፡
ይሁናና ዘመናዊና ባህላዊ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንጂ ተቃራኒ
ሃሳቦች አይደሉም፤ ምክንያቱም ሁለት ሃሳቦች ተቃራኒ ናቸው ካልን አንዱ ባለበት ሌላው መገኘት አይኖርበትም ማለታችን ነው፡፡ ነገር
ግን ዘመናዊና ባህላዊ አስተሳሰቦች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ “ዘመናዊ አስተሳሰብ የምዕራባውያን
ባህላዊ ደግሞ የአፍሪካውያን ወይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች መገለጫ” የሚለውም አስተሳሰብም አንዲሁ የተሳሳተ ነው፤ ምክንያቱም
በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ባህላዊ እና ዘመናዊ አስተሳሰቦች ይኖራሉና፡፡ ይልቁንም የራሳችን ነባር ባህላዊ ዕውቀት ተገቢውን ክብር
ሰጥተን በማጥናት የጎደለው ካለ ለመሙላት ከምዕራባውያን ዘመናዊ አሰራር ጋር ማዋሃዱ ብልህነት ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከምዕራባውያንን የህክምናና የመድኃኒት ቅመማ ሳይንስን
ስንወስድ ነባሩን ባህላዊ ህክምና ጥበብ ሳንንቅ አስቀድመን በማጥናት የሚጠቅመንን ቁም ነገሮች በመውሰድ ሁለቱን ማጣጣም ብንችል
ኖሮ በህክምናው ዘርፍ አሁን ከደረስንበት የተሻለ ዕድገት ማስመዘገብ ይቻል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ቻይናውያንን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵውያን ጥንታዊ የሽመና ጥበብ የሚመረቱ ባህላዊ ልብሶችን
ኋላቀር ናቸው፣ ለሥራ አይመቹም፤ በሚል ንቀን በመተው በምዕራባውያንን የአለባበስ ባህል ለምሳሌ ጂንስ (jeans) መሰል ልብሶችን
ባህላችን ባናደርግ፤ ባህላዊ የሽመና ጥበባችንን ከምዕራባውያን ሳይንስ ጋር ብናዋህደውና፤ ህዝባችን በየዕለቱ ባህላዊ ልብሶቻችንን
በጠቀም እንዲችል አድርገነው ቢሆን ኖሮ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ምን ያህል በሄድን፤የውጪ ምንዛሬ ምንያህል በቀነስናና፤ ለዜጎቻችን
ምን ያህል የሥራ ዕድል በከፈትን ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በራሳችን ባህላዊ እውቀትና ምርት ላይ እምነት ቢኖረንና እርሱንም በምርምር
አዳብረነው ባህላዊ አልባሳቶቻቸንን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ብንችል ኖሮ ቡናና ሰሊጥ ወደውጪ ከምንልከው የበለጠ ኩታና እጀ ጠባብ
በላክን ነበር፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘመናዊነት ምንም እንኳ በምዕራባውያን ቢጀመርም የምዕራባውያን
ባህል መገለጫ አይደለም፡፡ ልክ አውሮፓ ውስጥ ዘመናዊ ባህል እንዳለ ሁሉ አፍሪካ ውስጥም ከአውሮፓ ያልመጣ የራሷ የሆነ ዘመናዊ
ባህል አላት፤ ዘመናዊነትን በተገቢው ሁኔታ ከተቀበልነው፡፡ በተመሳሳይ
ልክ አፍሪካ ውስጥ ባህላዊ አስተሳሰብ እንዳለ ሁሉ ምዕራባውያንም የራሳቸው የሆነ ባህላዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ
በኢትዮጵያ የገና በዓል ሲከበር የሚዘጋጀው የገና ዛፍ (christmas tree) ልማድ ለኢትዮጵያውን ዘመናዊ ባህል ሲሆን ለምዕራባውያን
ግን ነባር ባህላዊ ተግባራቸው ነው፡፡
የዘመናዊና ባህላዊ ዲስኩር
(discourse) ጥልቅ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለውና የምዕራባውንን ስልጣኔ ታሪካዊና ታሪካዊ ዳራ (background) በጥልቀት
መገንዘብን የሚጠይቅ ስለሆነ በሁሉም ደረጃ ላሉ ዜጎች በእኩል ደረጃ ሊረዱት አይችሉም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ስሁል መስተሃልይ የሌላቸው
ግለሰቦች የተለመደንና ሰፊው ህዝብ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውን ነገር ያለምንም ጥያቄ ትክክል ነው ብለው ስለሚቀበሉና ምንም ዓይነት
ፍተሻ ስለማደርጉ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ Africa’s
Quest for a Philosophy of Decolonization በተባለ መጽሐፉ ላይ ለዚህ መፍትሄው ዜጎችን በፍልስፍና
ትምህርት ቀርጾ በድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካ ያሉትን ነባራዊ ሁነታዎች በድጋሜ በማጥናት ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱና የተዛባ
አስተሳሰብ የሚታይባቸውን እንደ ዘመናዊነትን የመሰሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሃሳቦች ትርጉም በመሻር (deconstruction)
እንደ አዲስ ከእኛ አውድ ጋር አስታርቆ መበየን (reconstruction) ነው ይላል፡፡ ሌላው አፍሪካዊ ፈላስፋ ፀናይ ሰረቀብርሃን
“The Critique of Eurocentrism and the Practice of African Philosophy” በተባለ ጽሁፉ አፍሪካውያን
በዘመናዊነትና በሉላዊነት ሳቢያ በአውሮፓውያን እየደረሰባቸው ስላለው የባህል ተጽዕኖና ስለማምለጫ መንገዶቹ ሲጽፍ የአፍሪካውያን
ፍልስፍና Historico-Hermeunitical የተባለውን መንገድ በመከተል የአፍሪካውያንን ችግሮች ከታሪካዊ ዳራ ትንታኔ በመነሳት
እንደገና ማሰብና የተጣመመውን ማቃናት፤ የጎደለውን መሙላት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ሪቻርድ ቤልና ክዋሜ ጂቼም ዘመናዊና ባህላዊን በማቃረን
አንዱን የበላይ አድርጎ በክብር ሌላውን ደግሞ የበታች አድርጎ በንቀት በማየት ነባሩን ባህላዊ እሴቶቻችንን ጨርሶ ከማጥፋታችን በፊት
ወደ ኋላ ወደ ነባሩ ባህላዊ አስተሳሰባችን፣ ድርጊታችንና እሴቶቻችን ተመልሰን እያንዳንዱን ባህላዊ እሴት በራሳችን አውድ በድጋሚ
ካሰብንና ከመረመርን (rethinking) በኋላ አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን
በድጋሚ ዋጋ ልንሰጣቸው (revaluation) ወይም በድጋሜ ወደ ህይወት ልንመልሳቸው (revitalization) ይገባል በማለት
ይመክራሉ፡፡
No comments:
Post a Comment