Thursday, April 4, 2013

የተዛባው የዘመናዊነት አስተሳሰብ!


 Published on Addis Admass Newspaper
ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ አሪፎች፣ ጭሶች፣ ነቄዎች፣ የተማሩ ወይም የሰለጠኑ በመባል የሚታወቁት ምዕራባዊ አስተሳሰብን (የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን) የሚከተሉ፣ “ዘመናዊ ቋንቋ” የሚችሉ፣ “ዘመናዊ” ሙዚቃ የሚያዳምጡ፣ “ዘመናዊ” ምግቦችን የሚመርጡ ወይም “ዘመናዊ” አለባበሶችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ኋላቀር፣ ያልሰለጠኑ፣ ያልተማሩ ወይም ሞኞች ተደርገው የሚታሰቡት ባህላዊ (ኢትዮጵያዊ) አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላልን? ዘመናዊስ ምንድን ነው? ባህላዊና ዘመናዊ ተቃራኒ ሃሳቦች ናቸው? ዘመናዊው አስተሳሰብ ሁሉ ከባህላዊው ይበልጣል? ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ በዘመናዊ ሊተካ ይገባል? የአፍሪካዉያን አስተሳሰብ ባህላዊ ምዕራባውያን ደግሞ ዘመናዊ ማለት ይቻል ይሆን?
ለጥያቄዎቹ ሁሉ በጅምላ የምሰጠው መልስ “አይደለም” የሚል ሲሆን የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ለምን እንዳልሆነ ማስረዳት ይሆናል፡፡  ክዋሜ ጂቼ (Kwame Gyekye) የተባለው የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካዊ ፈላስፋ “Tradition and Modernity” በተባለው መጽሐፉ በአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ የተነሳ የዘመናዊነት ትርጉምና አስተሳሰብ በአፍሪካውያን ዘንድ በእጅጉ ተዛብቷል ይለናል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሳትንበረከክ በአባቶቻችን ጀግንነትና የሃገር ፍቅር ስሜት ተከብራ የቆየች ቢሆንም፤ ከምዕራባውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ከካፒታሊዝም የውድድር መንፈስ፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከሉላዊነት (globalization) የባህል ወረራ የተነሳ ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ የዘመናዊ ተቃራኒ፣ የበታችና ኋላቀር እንደሆነና በ“ዘመናዊው አስተሳሰብ” ሊተካ እንደሚገባ የሚያወሳ የተዛባ ግንዛቤ ይዘው በልበ ሙሉነት የሚሞግቱ ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ምዕራባውያን “ዘመናዊነት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጀማሪ ስለሆኑና ኢትዮጵያ ደግሞ በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ስለሆነች ዘመናዊ ለመሆን ምዕራባውያንን መምሰል አለባት በሚል የአስተሳሰብ ህጸጽ (fallacy) ተነድተው ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር እስከማቆራኘትና የራስን ባህልና ስልጣኔ እስከማንቋሸሽ የደረሱም አሉ፡፡ በአንዳንድ የኮሚውኒቲና የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ ካልሆነ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መናገር፣ ማንበብና መጻፍን እንደ አሳፋሪ ነገር ሲቆጥሩና በሚሞክሯቸው የአውሮፓ ቋንቋዎች ሲመጻደቁ መመልከት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ለጉዳዩ አሳሳቢነት እንደ ምሳሌ  መጥቀስ ይቻላል፡፡ 
በርግጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ቀድመው ከሰለጠኑ ሃገሮች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ልማትን ለማፋጠን መገልገላቸው ከበደል የሚቆጠር ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ የሌሎችን እያደነቁ የራስን ስልጣኔ መናቅ፤ የሌሎችን ባህል እያስፋፉ የራስን ማዳከምና ማጥፋት ግን ተሞክሮ ከመውሰድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር ለሚያመሳስለው የአስተሳሰብ ህጸጽ በርካታ መነሻዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “ዘመናዊ” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ መጀመሪያ ያስተዋወቁት የመካከለኛው ዘመን ምዕራባውያን ፈላስፎች ናቸው፡፡ ሞደርን (Modern) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “modo” ከሚለው የላቲን ስረወ-ቃል የተገኘ ሲሆን አሁን just now, በቅርቡ recently የሚል  ትርጉምን ያለው ነው፡፡ ይህም ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ያለውን አስተሳሰብ የሚወክልና የነባሩ አስተሳሰብ “antiquus vetus” ተቃራኒ ሆኖ እንዲያገለግል የተሰየመ ነው፡፡ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሄደው የምዕራባውያንን ትምህርት ቀስመው ወደሀገራቸው የተመለሱ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ የሚለውን ቃል ዘመኑን፣ ጊዜውን፣ ወቅቱን መሰለ የሚል ተመሳሳይ ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው ተርጉመውታል፡፡ ሀገሪቱን ዘመናዊ ከማድረግ አንጻርም ባህላዊ አሰራር ኋላ ቀር ዘመናዊው (ምዕራባዊው) ግን የተሻለ በሚል ፍልስፍና ነባር ባህላዊ የህክምና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦቻችንና ስልጣኔዎቻችን ሙሉ በሙሉ ተሸረው በምዕራባውያን አሰራሮች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡
የተሻሉ የአውሮፓ አሰራሮችን ተሞክሮ መውሰዱ ባልከፋ ነበር፤ ችግሩ ግን ተሞክሮዎቹን የወሰድነው በራሳችን ነባር ባህላዊ አስተሳሰብና ስልጣኔ ላይ ተመስርተን ወይም በነበረን ባህላዊ እውቀት ላይ ቀጥለን ሳይሆን በዘመናዊነት ስም የነበረንን አቃለን፣ ንቀንና ጥለን የምዕራባውያንን ባህል ከነቋንቋቸው ከእኛ አውድ ጋር ሳናጣጥም መውረሳችን ነው፡፡ ለምሳሌ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በግዕዝ፣ በአረብኛና በአማርኛ የተጻፉ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የህግ፣ የስነጽሁፍ መጻህፍት እያላት በእነርሱ ላይ ያለውን ስልጣኔ ለማጥናት በኢትዮጵያ የኒቨርስቲዎች ውስጥ የፊሎሎጂ (የጥንታዊ ድርሳናት ጥናት) ትምህርት አለመስፋፋቱ ለራሳችን ነባር ስልጣኔ ያለንን ዝቅተኛ ግምት የሚመሰክር ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምዕራባውያን በጀርመን፣ በኢጣልያ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ እንዲሁም በሎሎች ሃገሮች የኒቨርስቲዎቻቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከፍተው ጥንታዊውን ግእዝንና ሌሎች ቋንቋዎቻችንን አጥንተው፤ እኛ የናቅናቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ድርሳናት ገሚሶቹን በግዥ፣ ሌሎችን ባልታወቀ መንገድ፣ የቀሩትን ደግሞ በማይክሮ ፊልም ቀርጸው በማሰባሰብ ጥናትና ምርምር አካሂደውባቸዋል፤ በርካታ ቁም ነገሮችንም ቀስመውባቸዋል፡፡ የሚያስገርመው ነገር ምዕራባውያን ዛሬም ጥንታዊ ጽሁፎቻችንን በዲጂታይዚንግ ቴክኖሎጂ በማሰባሰብና በማጥናት የቅጂ ባለመብት በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
ነባርና ባህላዊ የሆነውን እውቀታችንን ለማቃለልና የምዕራባውያንን አስተሳሰብ ብቻ ትክክል እንደሆነ ተቀብለን ለመጓዝ የበቃንበት ሌላው ምክንያት ዘመናዊና ባህላዊ ተቃራኒዎች እንደሆኑ አድርገን የምናስብበት ስር የሰደደ የተሳሳተ ፍልስፍናችን ነው፡፡ ዘመናዊ የባህላዊ ተቃራኒ ነው የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትክክል የሚቆጠረው “ካለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” እንዲሉ አንድ የተለመደን አስተሳሰብ እንደ እውነተኛ የመቀበል አባዜ ስለተጠናወተን  ነው፡፡ ነገር ግን የዚህን ማሳመኛው አወቃቀር በጥልቀት ብንመረምር ይህ አስተሳሰብ እጅግ ወደ ከፋ ድምዳሜ ሊወስደን እንደሚችል መመልከት ይቻላል፡፡ ዘመናዊ የአሁን፣ የቅርብ ጊዜ፣ ባህላዊ ደግሞ የቆየ፣ የጥንት አስተሳሰብ ነው፤ የሚለውን እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፤ ስልጣኔ ዝግመታዊ እድገት ስለሆነና የቅርብ ጊዜው አስተሳሰብ ከቆው የተሸለ ስለሆነ፤ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው አስተሳሰብ የተሻለ ነው ማለት ነው፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብ ከባህላዊው የተሻለ ነው ብለን ከተቀበልን፤ ዘመናዊው የምዕራባውያኑ ባህልና አስተሳሰብ ከእኛ ባህልና አስተሳሰብ የተሻለ ነው የሚለውን ድምዳሜ አበወንታ መቀበል አመክኗዊ ይሆናል፤ ስለሆነም የኛን ነባር ባህሎች፣ አስተሳሰቦችና አሰራሮች ሙሉ በሙሉ ንቀን በመተው በዘመናዊው የምዕራባውያን አስተሳሰብ መተካት አለብን፤ የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፡፡
ይሁናና ዘመናዊና ባህላዊ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንጂ ተቃራኒ ሃሳቦች አይደሉም፤ ምክንያቱም ሁለት ሃሳቦች ተቃራኒ ናቸው ካልን አንዱ ባለበት ሌላው መገኘት አይኖርበትም ማለታችን ነው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊና ባህላዊ አስተሳሰቦች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ “ዘመናዊ አስተሳሰብ የምዕራባውያን ባህላዊ ደግሞ የአፍሪካውያን ወይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች መገለጫ” የሚለውም አስተሳሰብም አንዲሁ የተሳሳተ ነው፤ ምክንያቱም በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ባህላዊ እና ዘመናዊ አስተሳሰቦች ይኖራሉና፡፡ ይልቁንም የራሳችን ነባር ባህላዊ ዕውቀት ተገቢውን ክብር ሰጥተን በማጥናት የጎደለው ካለ ለመሙላት ከምዕራባውያን ዘመናዊ አሰራር ጋር ማዋሃዱ ብልህነት ነው፡፡   ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከምዕራባውያንን የህክምናና የመድኃኒት ቅመማ ሳይንስን ስንወስድ ነባሩን ባህላዊ ህክምና ጥበብ ሳንንቅ አስቀድመን በማጥናት የሚጠቅመንን ቁም ነገሮች በመውሰድ ሁለቱን ማጣጣም ብንችል ኖሮ በህክምናው ዘርፍ አሁን ከደረስንበት የተሻለ ዕድገት ማስመዘገብ ይቻል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ቻይናውያንን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵውያን ጥንታዊ የሽመና ጥበብ የሚመረቱ ባህላዊ ልብሶችን ኋላቀር ናቸው፣ ለሥራ አይመቹም፤ በሚል ንቀን በመተው በምዕራባውያንን የአለባበስ ባህል ለምሳሌ ጂንስ (jeans) መሰል ልብሶችን ባህላችን ባናደርግ፤ ባህላዊ የሽመና ጥበባችንን ከምዕራባውያን ሳይንስ ጋር ብናዋህደውና፤ ህዝባችን በየዕለቱ ባህላዊ ልብሶቻችንን በጠቀም እንዲችል አድርገነው ቢሆን ኖሮ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ምን ያህል በሄድን፤የውጪ ምንዛሬ ምንያህል በቀነስናና፤ ለዜጎቻችን ምን ያህል የሥራ ዕድል በከፈትን ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በራሳችን ባህላዊ እውቀትና ምርት ላይ እምነት ቢኖረንና እርሱንም በምርምር አዳብረነው ባህላዊ አልባሳቶቻቸንን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ብንችል ኖሮ ቡናና ሰሊጥ ወደውጪ ከምንልከው የበለጠ ኩታና እጀ ጠባብ በላክን ነበር፡፡ 
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘመናዊነት ምንም እንኳ በምዕራባውያን ቢጀመርም የምዕራባውያን ባህል መገለጫ አይደለም፡፡ ልክ አውሮፓ ውስጥ ዘመናዊ ባህል እንዳለ ሁሉ አፍሪካ ውስጥም ከአውሮፓ ያልመጣ የራሷ የሆነ ዘመናዊ ባህል አላት፤ ዘመናዊነትን በተገቢው ሁኔታ ከተቀበልነው፡፡  በተመሳሳይ ልክ አፍሪካ ውስጥ ባህላዊ አስተሳሰብ እንዳለ ሁሉ ምዕራባውያንም የራሳቸው የሆነ ባህላዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የገና በዓል ሲከበር የሚዘጋጀው የገና ዛፍ (christmas tree) ልማድ ለኢትዮጵያውን ዘመናዊ ባህል ሲሆን ለምዕራባውያን ግን ነባር ባህላዊ ተግባራቸው ነው፡፡
የዘመናዊና ባህላዊ ዲስኩር (discourse) ጥልቅ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለውና የምዕራባውንን ስልጣኔ ታሪካዊና ታሪካዊ ዳራ (background) በጥልቀት መገንዘብን የሚጠይቅ ስለሆነ በሁሉም ደረጃ ላሉ ዜጎች በእኩል ደረጃ ሊረዱት አይችሉም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ስሁል መስተሃልይ የሌላቸው ግለሰቦች የተለመደንና ሰፊው ህዝብ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውን ነገር ያለምንም ጥያቄ ትክክል ነው ብለው ስለሚቀበሉና ምንም ዓይነት ፍተሻ ስለማደርጉ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ Africa’s Quest for a Philosophy of Decolonization በተባለ መጽሐፉ ላይ ለዚህ መፍትሄው ዜጎችን በፍልስፍና ትምህርት ቀርጾ በድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካ ያሉትን ነባራዊ ሁነታዎች በድጋሜ በማጥናት ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱና የተዛባ አስተሳሰብ የሚታይባቸውን እንደ ዘመናዊነትን የመሰሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሃሳቦች ትርጉም በመሻር (deconstruction) እንደ አዲስ ከእኛ አውድ ጋር አስታርቆ መበየን (reconstruction) ነው ይላል፡፡ ሌላው አፍሪካዊ ፈላስፋ ፀናይ ሰረቀብርሃን “The Critique of Eurocentrism and the Practice of African Philosophy” በተባለ ጽሁፉ አፍሪካውያን በዘመናዊነትና በሉላዊነት ሳቢያ በአውሮፓውያን እየደረሰባቸው ስላለው የባህል ተጽዕኖና ስለማምለጫ መንገዶቹ ሲጽፍ የአፍሪካውያን ፍልስፍና Historico-Hermeunitical የተባለውን መንገድ በመከተል የአፍሪካውያንን ችግሮች ከታሪካዊ ዳራ ትንታኔ በመነሳት እንደገና ማሰብና የተጣመመውን ማቃናት፤ የጎደለውን መሙላት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ሪቻርድ ቤልና ክዋሜ ጂቼም ዘመናዊና ባህላዊን በማቃረን አንዱን የበላይ አድርጎ በክብር ሌላውን ደግሞ የበታች አድርጎ በንቀት በማየት ነባሩን ባህላዊ እሴቶቻችንን ጨርሶ ከማጥፋታችን በፊት ወደ ኋላ ወደ ነባሩ ባህላዊ አስተሳሰባችን፣ ድርጊታችንና እሴቶቻችን ተመልሰን እያንዳንዱን ባህላዊ እሴት በራሳችን አውድ በድጋሚ ካሰብንና  ከመረመርን (rethinking) በኋላ አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን በድጋሚ ዋጋ ልንሰጣቸው (revaluation) ወይም በድጋሜ ወደ ህይወት ልንመልሳቸው (revitalization) ይገባል በማለት ይመክራሉ፡፡ 

ለሌሎች “ጥሩ” የሆነው ላንተ “መጥፎ” ሊሆን ይችላል !


 Published on Addis Admass Newspaper
ዓለማችን በበርካታ ተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ የተቃራኒዎች መኖር ደግሞ ለዓለም መገኛ ምንጭና የህልውና እስትንፋስ መሆናቸውን ይናገራሉ፤ ሄራክሊተስና ተከታዮቹ፡፡ ጨለማና ብርሃን ፣ጥላቻና ፍቅር ፣ግራና ቀኝ፣ ውሸትና እውነት፣ መሃይምና ምሁር፣ ድህነትና ሃብት፣ ረሃብና ጥጋብ፣ ንፉግነትና ቸርነት፣ ጭካኔና ርህራሄ፣ ፍርሃትና ድፍረት የመሳሰሉት ጥንድ ቃላት በተቃራኒነት ይታወቃሉ፡፡ ምንም እንኳን የአንዱ ጥንድ ቃል  የተቃርኖ ሁኔታ ከሌላው በእጅጉ የሚለያይ ቢሆንም ከጥንዶቹ አንዱ ሁልጊዜ በክፉ ሌላው ደግሞ በበጎ ክፍል መመደባቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጨለማ፣ ግራ፣ ጥላቻ፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ በመጥፎ እንዲሁም ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ሃብት፣ ቀኝ፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ደግሞ በጥሩ ምድብ መካተታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ጥላቻ፣ ውሸት፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ “ሁልጊዜ መጥፎ ናቸው” ብሎ በርግጠኝነት መናገር ይቻል ይሆን?  በሌላ በኩል ደግሞ ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ሁልጊዜ ጥሩ ድርጊቶች ናቸው ብሎ ለመናገርስ የሚደፍር ይኖር ይሆን?
በርግጥ ፍጹማውያን (objectivist) ፈላስፎች ይህን በርግጠኝነት ለማለት ይደፍራሉ፤ ምክንያቱም በእነርሱ እምነት አንድ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት ጥሩ ከተባለ በየትኛውም ዘመን በማንኛውም ቦታ ጥሩ ነው፤ እንዲሁም መጥፎ ከተባለ ምንም ጊዜ የትም ቦታ መጥፎ ነውና፡፡ ለምሳሌ የውሻና የአሳማ ሥጋ መመገብ ነውር ከሆነ በማንኛውም ዘመን በየትኛውም ሀገር ባህል ነውር ነው ማለት ነው፡፡ ይሁንና በሌላ ጎራ የሚገኙ አንጻራውያን (relativist) ፈላስፎች ደግሞ አንድ ድርጊት በተመሳሳይ ጊዜ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል፤ ስለሆነም አንድን የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት አብነት አንስቶ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ ከመበየን በፊት ደርጊቱ በየትኛው ዘመን፣ በማን ባህል፣ በማን ሃይማኖት በአጠቃላይ ከምን አንጻር የሚለውን ነገር ማጥናት ያስፈልጋል ሲሉ ማሳመኛ ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ “አንድ ወንድ ባል ለአንድ ሴት ሚስት ወይም አንድ ሴት ሚስት ለአንድ ወንድ ባል” (monogamy) ብቻ ትክክለኛ የጋብቻ ፍልስፍና እንደሆነ በርካቶች የሚግባቡበት ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በተቃራኒው አንድ ወንድ ባል ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሴት ሚስቶች (polygamy) የጋብቻ ፍልስፍና የሚፈቅዱና የሚያራምዱ በርካታ ባህሎችና ሃይማኖቶችም መኖራቸውም እሙን ነው፡፡ ታዲያ ትክክለኛው የጋብቻ ስነ ምግባር የትኛው ነው? ለምን? ከማን አንጻር?
ከዚህም ባሻገር ለብርሃን መኖር ጨለማ፣ ለእውነት መኖር ውሸት መኖራቸው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ በተቃራኒዎች ውስጥ የሚገኙ የመጥፎ ነገሮች መኖርም በራሱ አስፈላጊ መጥፎነት (necessary evil) ነው በሚል የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለምሳሌ “ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል” እና “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚሉት የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የክፉ ሰዎች በእኛ ዙሪያ መኖር ምን ያህል አስፈላጊና ለትጋታችን መነሻ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡
ፍልስፍና በፍጹማውያንንና በአንጻራውያን እይታ ዘርፈ ብዙ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ መጠን ውስብስብ ከሆኑ የስነ ምግባር ፍልስፍና ንድፈ ሃሳቦች (moral theories) ጀምሮ በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በሳይንስና፣ በአካባቢያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚነሱ አወዛጋቢ በስነ ምግባር አጀንዳዎችን (controversial moral issues) በጥልቀት መርምሮ አንድ  በአመክኗዊ አቋም ላይ እስከ መድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህ የስነ ምግባር አቀራረብ ተግባራዊ ስነ ምግባር (applied ethics) ይባላል፡፡ ተግባራዊ ስነ ምግባር ለሙያዊ የስነ ምግባር (professional ethics) ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚወጡ ህጎችና ደንቦች (legal codes) መንገድ ቀዳጅ ነው፡
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያገኙና ትክክለኛ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የተግባራዊና የሙያዊ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ነገር ግን ጥልቅ ምርምርን የሚሹ አስተሳሰቦች በፍልስፍና መነጽር ሲቃኙ ምን አይነት ስህተት አንዳለባቸው ማሳየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የምናነሳው የሰው ልጅ በእንስሳት፣ በእጽዋት፣ በመሬት፣ በከባቢ አየርና በሌሌች ረቂቅና ግዙፍ ፍጥረታት ላይ ስለሚፈጽመው የስነምግባራዊ ግድፈት የሚያትተውን አካባቢያዊ ስነ ምግባር (environmental ethics) ነው፡፡
በነባሩ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር  አስተምህሮ ስነ ምግባር በዋነኝነት የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው፡፡ ይህም ማለት አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን ለመገምገም የምንችለው ድርጊቱ በሰው ልጆች፣ ለሰው ልጆች ወይም የሰው ልጆች ላይ ብቻ የሚፈጸም ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላን ሰው በጭካኔ ሲደበድብ ብንመለከት ደብዳቢው ግለሰብ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነው እንላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አንድ ውሻን ደብድቦ ሲገድለው ብንመለከት ገዳዩ ስነ ምግባር የጎደለው ሰው ተብሎ አይታሰብም፤ ምክንያቱም እንስሳት እንደ ሰው ልጆች የሞራል አቋም የላቸውምና፡፡
ነገር ግን በዘመናችን የተነሱ የአካባቢ ፍልስፍና ሊቃውንት (environmental philosophers) ስነ ምግባር ለሰው ልጆች ብቻ የሚሰጥ ጽንሰ ሃሳብ ሳይሆን በአጠቃላይ ለፕላኔታችን ለመሬት፣ ለእንስሳት፣ ለእጽዋት እንዲሁም በምድራችን ላይ ለሚገኙ ሌሎች ህይወት ያላቸውና ህይወት ለሌላቸው ነገሮች ሁሉ የሚተገበር ሃሳብ መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ነባሮቹ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር ሊቃውንት (ethicists) “ስነ ምግባር የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው” የሚል ስህተት የፈጸሙት ስለ ተፈጥሮ የነበራቸው አመለካከት ጠባብና የተሳሳተ ስለነበረ ነው ይለናል፤ ኖርዌጅያኑ የአካባቢ ፈላስፋ አረን ኒአስ፡፡ ኒአስ በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ “ተፈጥሮ ለራሷ” (Deep ecology) በመባል የሚታወቀውን የአካባቢ እንክብካቤ ንቅናቄን ሲመሰርት በተፈጥሮ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት ዓላማ የሰውን ልጅ ፍላጎት ለማርካት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሰረተውን የ“ተፈጥሮን ለሰው ልጅ”  (Shallow ecology) አስተምህሮ ይቃወማል፡፡ የ “ተፈጥሮን ለሰው ልጅ” አስተምህሮ ከአንድ አምላክ አማኞች ማለትም ከአይሁድ፣ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖት የስነ-ፍጥረት አስተምህሮት ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ይህም ሰው ፍላጎቱን ለማርካት ደን ቢመነጥር፣ እንስሳትን አርዶ ቢመገብ ወይም አካባቢን ቢበክል ከስነ ምግባር ውጪ እንደሆነ አይቆጠርም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡
የ“ተፈጥሮ ለራሷ” ፍልስፍና በዓለማችን ላይ የሚገኙ ህይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው እንጂ የሰው ልጅ ፍላጎትን ለማሟላት አይደለም፤ ስለሆነም ለሰው ልጅ ፍላጎት በሚል በተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት ብዝበዛ ከተሳሳተ “ሰው ተኮር” (anthropocentric) ምልከታ የመነጨና ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ይላሉ፤ ኒአስና ተከታዮቹ፡፡ “ሰው ተኮር ያልሆነ” (non-anthropocentric) የአካባቢ ስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች የአካባቢ ተቆርቋሪዎች፣ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እና የመሳሰሉትን መለያዎችን አንግበው መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራትን በመመስረት ለአካባቢ ስነ ምግባር መጠበቅ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ ክልሎች በአህዮች ደህንነት ዙሪያ በመስራት ላይ የሚገኘው “The Donkey Sanctuary”  የተባለውና መቀመጫውን በእንግሊዝ ሃገር ያደረገው ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሀገራችን የእንስሳት መብት ተሟጋችነት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእንስሳት መብት ተሟጋቾች እምነት እንስሳት እንደ ሰው የደስታ፣ የሃዘንና የስቃይ ስሜት እንዲሁም የራሳቸው የተፈጠሩበት ዓላማ ያላቸው በመሆኑ ሰው እንደ እቃ ሊቆጥራቸውና ያለአግባቡ ተገልግሎ ሊጥላቸው አይገባም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአህዮችና በጋሪ ፈረሶች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ስነምግባራዊ ብዝበዛ ለማስቆም በጎ ፈቃደኞቹ እንስሳቱ በጉብዝናቸው ወቅት ካቅማቸው በላይ እንዳይሰሩ፣ በህመማቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ጥረት መደረግ አለበት ይላሉ፡፡      
ከእንስሳት መብት ባሻገር ስለ ተፈጥሯዊ አካባቢ ብክለትና መቆርቆዝ፣ እንዲሁም በዚህም ሳቢያ በሰው ልጆችና በሌሎች ፍጥረታት ላይ እየደረሰ ስለሚገኘው ጉዳት የስነምግባር ተጠያቂነትም ድምጻቸውን ያሰማሉ፤ የአካባቢ ስነምግባር ፈላስፎች፡፡ በሉላዊ የካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠን ማሻቀብ ሳቢያ በፕላኔታችን በምድርና በከባቢ አየሯ ላይ እየተፈጠረ ላለው የሙቀት መጨመር፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣ የመሬት መራቆትና ድርቅ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ቀውሶች ሰለባ እየሆነ ያለው በጠቅላላው የዓለም ህዝብ ነው፡፡ በርግጥ የቀውሱ ምክንያት የሆኑት አካላት በሰው ተኮር አካባቢያዊ ፍልስፍና ተገፍተው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዓለምን እየመሩ ያሉት ጥቂት የዓለማችን ሃገራት ናቸው፡፡ ይሁንና የችግሩ ሰለባዎች በኢንዱስትሪው ዓለምን እየመሩ የሚገኙ ሃገሮች ብቻ ሳይሆኑ  ምንም ያላጠፉ በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮችም ጭምር ናቸው፡፡ ይህም ከስነ ምግባር መርኆዎች አንጻር ኢፍትሃዊ ነው፡፡ በመሆኑም ለካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠንም ለየሃገሮቹ ውሱን ኮታ ሊሰጥና የበለጸጉት በካይ ሃገሮች ያለኃጢአታቸው የቀውሱ ሰለባ ለሆኑ ደሃ ሃገሮች ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚል አቋም ይዘውም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጉባዔዎችና አህጉራዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው ቀጣይነት ያለው ልማት (sustainable Development) ስትራተጂና አፍሪካውያንን ወክለው ያቀረቡት የአየር ብክለት ካሳ ጥያቄ በዚህ የስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች ጎራ ሊያስመድባቸው እንደሚችል የአረንጓዴው ኢኮኖሚ ሊቅ ሚካኤል ስትሬት (Michael Street) በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡
ስነ ምግባር የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስ ስኬታማ ከማድረግ ጀምሮ ወንጀል እንዳይስፋፋ፣ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ፣ ሀገር እንደ ሀገር እንዲቀጥል፣ ከዚህም አልፎ የአንድ ሃገር ህዝቦች ከሌላው ጋር መግባባት እንዲችሉና በአጠቃላይ በዓለም ህዝብ ዘንድ መከባበር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲኖር የማድረግ አቅም ያለው የፍልስፍና ጥናት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ሀገር ልማት ላይ ስነ ምግባር ስለሚኖረው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ የልማት ስነ ምግባር (Developmental Ethics) ባለሙያዎች ያስተምራሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ራሞሴ ያሉ የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ፈላስፎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ያደጉት ወይም የልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታት በስነ ምግባር መዝቀጥ በማደግ ላይ ለሚገኙት ሀገሮች የእድገት እንቅፋት መሆናቸውን አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ በኒውክለር ኃይል አጠቃቀም፣ በዓለም አቀፍ የልማት ብርድና እርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ በልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታትና እንደ (IMF, World Bank) ባሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም የስነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በሶሪያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የበሽር አላሳድ መንግስትና ተቃዋሚዎቹ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማብቃት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አወንታዊ ጣልቃ ገብነትን ሩሲያ አጥብቃ መቃወሟ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ገቢዋ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን እንደማይቀር የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል “በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና” በኢራን መንግስት መካከል የተፈጠረው የኒውክለር ኃይል ማብላላት ጋር የተገናኘው ፖለቲካዊ ውጥረት አንዱ መነሻ የስነ ምግባር አጀንዳ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እንደ አሜሪካና ሩሲያ ያሉ የኒውክለር ባለቤቶች ከኒውክለር የጸዳች ሰላማዊ ዓለም የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም ራሳቸው የኒውክለር ጦር መሳሪያዎችን ሳያስወግዱ ሌሎች የማብላላት ፕሮግራማቸውን እንዲያቋርጡ መወትወታቸው ሁኔታውን ከፖለቲካ ወደ ስነምግባር ምህዳር አምጥቶታል፡፡ በኢራንና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ የዚህ እውነታ አንዱ ነጸብራቅ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ልትሰራ ላሰበችው ግድብና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ጠይቃ መከልከሏ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስነ ምግባር መዝቀጥ በታዳጊ ሃገሮች እድገት ላይ ምን ያህል ጫና እንደሚሳርፍ በግልጽ ማሳየት የሚችል ሌላው ሃቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ በህክምና፣ በንግድ፣ ሌሎች ሙያዎች ውስጥ አከራካሪ የሆኑ በርካታ የስነ ምግባር አጀንዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከአድራጊው፣ ከአስደራጊው፣ ከአደራራጊው፣ ከማህበረሰቡ ባህላዊ እሴትና ከህግ እይታ አንጻር ትክክል ወይም ስህተት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በህክምና ሙያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱ የውርጃና የምህረት ግድያን (euthanasia) የመሳሰሉ አወዛጋቢ የስነ ምግባር ጥያቄዎች  ለአንዱ ትክክል ሲሆኑ ለሌላው ደግሞ ስህተት ናቸው፡፡ በመሆኑም ግለሰቦች የሰዎችን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለው ከመፈረጃቸው በፊት እንዲሁም የስነ ምግባር ደንብ አርቃቂዎችና ህግ አውጪዎች ድንጋጌዎቻቸውን ከማወጃቸው በፊት፤ ወይም ሀገሮች በሌላው ሃገር ላይ ጣታቸውን ከማንሳታቸው በፊት በሰነዱ ላይ የተፈቀዱትን ወይም የተከለከሉትን ድርጊቶች በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ፍልስፍና መነጽሮች መቃኘታቸውንና ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡  

ሥነ-ምግባር በሃይማኖት ወይስ በፍልስፍና?


 Published on Addis Admass Newspaper
ማህበረሰብ ከሌለ ወግና ስርዓት አይኖርም፡፡ ወግና ስርዓት ከሌለ ደግሞ ነውር ወይም ክብር አይኖርም፤ ሥነ-ምግባር ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ድርጊት መለየትና ነውር የሆነውን ድርጊት የማስወገድ ሂደት ነው፤ ስለሆነም ለማህበረሰባዊ ስነ ምግባር (morality) መከሰት የመጀመሪው ቅድመ ሁኔታ የማህበረሰብ መገኘት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ባዶ ቤት ውስጥ ሙሉ ቀን ራቁቱን ቢዘዋወር ምንም ነውር የለውም፤ ነገር ግን ያው ግለሰብ ለአንድ ደቂቃ ያህል ከተማ ውስጥ እርቃኑን ቢዘዋወር እንደ “ነውረኛ” ወይም “እብድ” መቆጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ታላቁ አትዮጵያዊ ጸሐፊ ከበደ ሚካኤል በግጥማቸው “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም::” ብለዋል፡፡ ስለ ወግና ስርዓት፣ ነውርና ክብር፣ ክፋትና ደግነት፣ ጥሩነትና መጥፎነት፣ እንዲሁም ስለ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ትክክለኝነትና ስህተትነት ምንነት፣መስፈርትና አስፈላጊነት የመሳሰሉትን  ሃሳቦች የሚያጠና ዓቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሥነ-ምግባር (Ethics) ይባላል፡፡
ሥነ ምግባር “አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን የምንመዝነው ከምን አንጻር ነው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄን ማብራራት ላይ ያጠነጥናል፡፡ በዚህ ሂደት ላይም “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” ማለት ራሱ ምን ማለት እንደሆነና ሰዎች ለምን መልካም ምግባርን ለማድረግ እንደሚነሳሱ “የሥነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ወጥ ትርጉም ያላቸው ናቸው ከሚለው የሁሉንአቀፎች (universalist) አቋምና፤ ስነ ምግባር ከሰው ሰው፣ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል ከሚለው የአንጻራውያን (subjectivist) እይታ አንጻር አመክኗዊ ማብራሪያ  ይሰጣል፤ የስነምግባር ፍልስፍና፡፡
ሥነ-ምግባር የግለሰቦችን ማህበራዊ ኑሮ ከማስመሩም ባሻገር በሀገር ልማት አጀንዳ ላይ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡ በአንድ ሃገር ውስጥ ሙስና፣ ስርዓት አልበኝነትና ወንጀል ከተንሰራፋ፤ እንዲሁም ዜጎች የሃገርን ክብር፣ የወገንን ፍቅር የማያውቁ ከሆነና ራስ ወዳድነት ከነገሰ፤ ግለሰቦች ለሃገር ልማት ምንም ዓይነት ቦታ ስለማኖራቸውና ሃላፊነት ስለማይሰማቸው ለሀገራቸው ዕድገት እንቅፋት መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ነው በራሳችን ሀገር ስነ ምግባር የጎደላቸው ዜጎች ለህዝብ አገልግሎትና ለሀገር ልማት የተመደበ በጀት ለግለሰቦች ጥቅም ሲውል፣ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን፣ በቆሻሻ ሲደፈኑ፣ የትቦዎቹ መሸፈኛ ብረቶች፣ የመንገድ ላይ ምልክቶች፣ በህዝብ ስልኮች ላይ የተገጠሙትን ሶላር ፓኔሎች ፣ በመንግስት የትምህርት ተቋማት ህንዎች ላይ የሚገኙትን ማብሪያ ማጥፊያና ሶኬቶች ተነቅለው ሲወሰዱ፣ በመንገድ ዳር የተተከሉ ዛፎች በለጋነታቸው ሲቀጠፉ፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ዕቃ ባለበት ሁኔታ ቆሻሻ በየቦታው ሲጣልና ይህን የመሳሰለውን ነውር በተደጋጋሚ መመልከትና መስማት የተለመደ እየሆነ የመጣው፡፡
የዜጎች በሥነ-ምግባር መዝቀጥ በግለሰቦች የዕለት ተዕለት ህይወትና በሀገር እድገት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጅ ልጆቹን፣ የሃማኖት መሪም ከታዮቹን፣ መንግስትም ዜጎቹን በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የማድረግ ቀዳሚ ሃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ትልቁ ፈታኝ ጉዳይ “ስነ ምግባርን እንዴት ማስተማር ይቻላል?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይሆናል፡፡ ይህም ከሃይማኖታዊና ከፍልስፍናዊ ስነ ምግባርን የማስተማሪያ አቀራረቦች መካከል የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚቻለው በየትኛው መንገድ እንደሆነ ለማጥናት የሚሞክር ነው፡፡
የሰው ልጅ ስለ ሥነ-ምግባር ምንነት፣ መኖር ወይም አለመኖር እንዲሁም መቼ እንደጀመረና ስለ ሥነ-ምግባር የተሸለ የማስተማሪ መንገዶች የሚሰጠው ምላሽ እንደየመላሾቹ ማንነትና እምነት በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ፕሮታጎረስ የተባለው ሶፊስት (sophist) የግሪክ ፈላስፋ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ጥሩ ወይም መጥፎ ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፤ ጥሩነታቸውም ሆነ መጥፎነታቸው የሚወሰነው በድርጊቱ ፈጻሚ ግለሰብ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ስነምግባርን ማስተማር አይቻልም፤ አያስፈልግምም ሲል ትራዚማከስ ደግሞ ማንኛውንም ድርጊት ትክክል የሚያደርገው ኃይል (ገንዘብ ወይም ጉልበት) ነው “might makes right” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ሶቅራጠስ የመልካም ስራ ምንጭ ዕውቀት፤ የክፋት ሁሉ ምንጭ ደግሞ አለማወቅ በመሆኑ ሰዎች መልካምነት ምን እንደሆነ ሲያውቁ ብቻ መልካም ይሆናሉ፤በመሆኑም በትምህርት ሰዎችን ስነ ምግባር ማሻሻል ይቻላል ብሎ ይደመድማል፡፡ የአፍላጦን ተማሪ አሪስጣጣሊስ “Nicomachean Ethics” በተባለው የስነ ምግባር ስራው ውስጥ ስነ ምግባር ሁልጊዜ በሁለት ጽንፎች መሃል የሚገኝ ድርጊት ነው ይላል፡፡   
የስነ መለኮት ምሁራን የስነ ምግባርን ህግጋት በአምላክ የተሰጡና በፍጡራን ህሊና (በህገ ልቡና) ውስጥ በደመነፍስ የሚታወቁ ፍጹማዊና ሁለንተናዊ፤ በቦታና በጊዜ የማይቀያሩ ዘለዓለማዊ ሃሳቦች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የሰው ልጅም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የስነ ምግባር ህግጋቱ አብረውት እንደነበሩ ኋላም በየዘመናቱ በፍጡራን ልቡና ውስጥ የታተሙትን የስነ ምግባር ህግጋትን ለማደስ አምላክ የጽሁፍ ህግን እንደሰጠ፣ በነብያትና በሐዋርያት አድሮም እንዳስተማረ ያብራራሉ፤ የመለኮታዊ ትዕዛዝ (Divine Command theory) ንድፈ ሃሳብ አራማጆች፡፡
በሃይማኖታዊ ሥነ-ምግባር መርህ መሰረት አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ተብሎ የሚፈረጀው ድርጊቱ በቅዱሳት መጻህፍት “አድርግ” ወይም “አታድርግ” ተብሎ ከመጻፉ ወይም ካለመጻፉ አንጻር እንጂ ጥሩ ወይም መጥፎ ለመሆኑ በሚቀርብ ዝርዝር ምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ምክንያቱ የሰውን ህይወት ለማዳንም ይሁን ለማጥፋት በሀሰት መመስከር ሁልጊዜ በማንኛውም ቦታ መጥፎ ድርጊት ነው፤ ምክንያቱም የአምላክ ቃል “በሀሰት አትመስክር” ይላልና፡፡
ሁለተኛው ሥነ-ምግባር ንድፈ ሃሳብ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን የሰዎች ወይም የማህበረሰብ ስምምነት ውጤት (social contact theory) መሆናቸውን ይሰብካል፡፡ የዚህ ስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ ሊቃውንት ጆን ሎክና (Locke) ራውልስ (Rawls) የሰው ልጅ ራሱ በፈጠራቸው የስነ ምግባር ህግጋት ተገዝቶ ለመኖር ከመስማማቱ በፊት በተፈጥሮ እንዳለ (state of nature) ይኸውም ስለ ዘር፣ ብሄር፣ ጎሳ፣ ወሲባዊ ባህርይ ትክክል ወይም ስህተት የሚለውን ውሱን አስተሳሰብ ከመያዙ በፊት በኖረባቸው በነዚያ ዘመናት፤ ወይም ሃይማኖት፣ ህግ፣ መንግስትና ስነምግባር ህግ ባልነበረበት ሁኔታ በምን ዓይነት ትርምስና የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ይኖር አንደነበር በምናባችን እንድንስለው በማድረግ ማሳመኛቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህ የማያቋርጥ ጦርነት ብርቱዎቹ ደካሞቹን በኃይል በመርታት ንብረታቸውን ይዘርፋሉ፣ ነጻነታቸውን በመግፈፍ በባርነት ይይዛሉ ህይወታቸውንም ያጠፋሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ትክክል እንደሆነ ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ከኃይል በስተቀር የስነ ምግባርም ሆነ የፖለቲካ ህግ የለምና፡፡ እንደ ንድፈ ሃሳቡ አራማጆች ከዚህ ችግር ለመውጣት የሰው ልጅ በስምምነት መንግስትን፣ ህግን፣ የስነምግባር እሴቶችን መሰረተ፡፡ በመሆኑም ስነ ምግባርን ለማስተማር ስምምነቶቹ ለጋራ ጥቅም ያላቸውን ፋይዳና የስነ ምግባር ህግጋትን አለማክበር በጋራ ደህንነት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ዜጎች እንዲገነዘቡት በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰውን ንብረት መስረቅ መጥፎ የሆነበት ምክንያት አምላክ “አትስረቅ” የሚል ትዕዛዝ ስለሰጠ ሳይሆን የጋራ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የማህበረሰቡ አባላት በአንድ ወቅት ስለተስማሙበትና ይህን የሚጥሱ ሰዎችን ነውረኛ አድርጎ ከማህበረሰቡ በማግለልና ክብር በመንሳት ለመቅጣት ስለወሰኑ ነው፡፡ ስምምነት የተደረገባቸው የስነ ምግባር ልማዶች አስፈላጊነታቸው ሲጎላና በማያከብሯቸው ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት መጣል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የስነ ምግባር ወጎችና ልማዶች ወደ ህግ ደረጃ እንዲድጉ ይደረጋል፡፡ በፍትሃብሄርም ሆነ በወንጀል ህግጋት ላይ የተከለከሉት አብዛኞቹ ህጎች መነሻቸው የማህበረሰቡ ነባር የስነ ምግባር እሴቶች ናቸው፡፡
ሶስተኛው የስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ የሚታወቀው ድርጊቱ ከሚያስከትለው ውጤት (consequence) አንጻር እንጂ በራሱ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባል ድርጊት የለም የሚል ነው፡፡ ድርጊቱ በመጨረሻ ውጤቱ ጥሩ ከሆነ ድርጊቱ ጥሩ ነበር ማለት ነው፤ ነገር ግን ውጤቱ መጥፎ ከሆነ ግለሰቡ የተነሳበት ሃሳብ ምንም ይሁን ድርጊቱ በመጥፎነት ይፈረጃል፤ ይህም “The end justifies the means” ከሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ለምሳሌ መዋሸት ለማስታረቅ ከሆነ መልካም፤ ሰውን ለመጉዳት ከሆነ ግን መጥፎ ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡ ሄዶኒዝም (hedonism) የዚህ ንድፈ ሃሳብ ዋነኛ መገለጫ ሲሆን ይህም አንድ ድርጊት ጥሩ ነው የሚባለው እርካታን የሚያስገኝ ከሆነ ብቻ ነው፤ መጥፎ የሚባለውም ስቃይ ካለው ነው የሚል መሰረተ እምነት የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ መስረቅ፣ ማመንዘር፣ መዝፈን፣ መስከር፣ ራስን ማጥፋት የመሳሰሉት ድርጊቶች እርካታን የሚያስገኙ ከሆነ ወይም ስቃይን የሚያስወግዱ ከሆነ በጥሩ ድርጊትነት ይፈረጃሉ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ የመጨረሻው ጽንፍ ላይ የምናገኘው ኤፒኪውረስ (Epicurus) የተባለው የግሪክ ፈላስፋ በዓለም ላይ ትልቁ የህይወት ግብ ሥጋዊ እርካታን ማግኘት ነው ይላል፤ በተለይ ከወሲብ ስሜት ጋር የተገናኘና ህሊናን የሚቃወም ዓይነት፡፡
የአንድን ድርጊት ጥሩና መጥፎነት ድርጊቱ ከሚያስከትለው ውጤት ወይም እርካታ  አንጻር ስንመዝን የሚገጥመን ትልቁ ፈተና “ለማን ያስከተለው ውጤት/ ያስገኘው እርካታ” የሚለውን መወሰኑ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዚህ ንድፈ ሃሳብ አራማጆች በሶስት ጎራ ይከፈላሉ፡፡
የመጀመሪዎቹ “ለእኔ ባዮች” (egoists) ሲሆኑ እነዚህም ሰው በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ስለሆነ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ለአድራጊው ግለሰብ ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሌሎችን (ሃገርን፣ ወገንን) ከግምት የማያስገባ ስለሆነ እንደ ሃገር አደገኛ ፍልስፍና ነው፡፡ በዚህ ፍልስፍና የሚመራ ሰው ለሌሎች ደንታ ስለማይኖረው በሙስናና መሰል የራስ ወዳድነት አፍራሽ ተግባራት ከመሰማራቱም በላይ በድርጊቱ የአሸናፊነት እንጂ የጸጸት ስሜት አይኖረውም፤ ከስህተቱም አይታረምም፡፡
የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ከአድራጊው ግለሰብ ውጪ ላሉ ለሌሎት ሰዎች ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው የሚሉ ሲሆኑ እነዚህም “ለወገኔ ባዮች” (altruists) ይባላሉ፡፡ በዚህ የሥነ ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ግለሰቦች ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች ወገኖች አብልጠው ስለሚያስቡ ለስነ ምግባር ብለው ህይወታቸውን አሳልፈው እስከመስጠት ይደርሳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃገሬንና ህዝቤን ለጨካኙ የጣልያኖች አገዛዝ አሳልፌ አልሰጥም፤ አልክድም በሚል ህይወታቸውን ስለሃገራቸውና ስለወገናቸው ክብር አሳልፈው የሰጡትና ለሰማዕትነት የበቁት በዚህ የስነምግባር ፍልስፍና ይመሩ ስለነበር ነው፡፡      
“ለእኛ ባዮች” (utilitarianism) የሥነ ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ሥነ ምግባር ከሚያስከትለው ውጤት አንጻር ብቻ መመዘን አለበት የሚል አስተሳሰብ ከሚያራምዱ ግለሰቦች በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ አድራጊው ግለሰብ ጨምሮ ለብዙሃኑ ወይም በርካታ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው ብለው ያምናሉ፤ የ“ለእኛ ባዮች” የሥነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች፡፡ የዚህ ፍልስፍና መስራች እንግሊዛዊው ፈላስፋ ጀረሚ ቤንታም አንድን ድርጊት ጥሩ ነው ብሎ የሚያምነው ድርጊቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች እጅግ ከፍተኛ ደስታ (እርካታ) የሚያመነጭ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ቤንታምና ተከታዮቹ አንድ ድርጊት የሚያመነጨውን የደስታ ወይም የስቃይ መጠን ለመለካት የሂሳብ ስሌት መጠቀም ይቻላል የሚል ማሳመኛ አቅርቧል፡፡ በዚህም መሰረት እንድ ድርጊት ከፍተኛ እርካታ ያመነጫል ማለት የሚቻለው ድርጊቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጠቅላላ እርካታ ላይ ድርጊቱ ሊያመጣ የሚችለውን ጠቅላላ ስቃይ በመቀነስ የሚገኘው የተጣራ እርካታ  ሲሰላና ጠቅላላ እርካታው ከጠቅላላ ስቃይ የበለጠ ሲሆን ብቻ ነው፡፡   
ሌላው ዓቢይ የስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ ኃላፊነት ተኮር (Duty Based theory) ይባላል፡፡ ከዚህ ንድፈ ሃሳብ መገለጫዎች አንዱ በሆነው የኢማኑኤል ካንት ህሊናዊ ትዕዛዝ (categorical imperative) የስነ ምግባር ማሳመኛ መሰረት አንድ ድርጊት መልካም ወይም ክፉ መሆኑ የሚታወቀው ድርጊቱ በሚያስከትለው ውጤት ሳይሆን ግለሰቡ ድርጊቱን ለመፈጸም ከተነሳበት ውስጣዊ ምክንያት አንጻር ነው፡፡ መጀመሪያ በጎ ህሊና ይኑርህ፤ከዚያ ህሊናህ ትክክል ነው የሚልህን ነገር አድርገው፤ ጥሩ ስራ ነውና፤ ነገር ግን ህሊናህ የሚቃወምህ ከሆነ ክፉ ስራ ነውና አታድርገው ይላል፤ ካንት፡፡ ህሊናህ ትክክል ያለህ ነገር በርግጥ ትክክል መሆኑን ለመፈተሸ እንድትችል ትክክል ነው ብለህ ያሰብከው ነገር ከወርቃማው ህግ ማለትም “አንተ በሌሎች ላይ ልታደርግ ያሰብከውን ነገር ሌሎች አንተ ላይ ቢያደርጉብህ እንደምትፈቅድ ራስህን ጠይቅ” ይላል፡፡ “Act as if the principle on which your action is based were to become by your will a universal law of nature.” በሌላ በኩል ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ ያለባቸው የሚመጣላቸውን በጎ ነገር አስበው ወይም የሚመጣባቸውን ክፉ ነገር ፈርተው ሳይሆን ያለምንም ውጫዊ ምክንያት መልካም ስራ መስራት እንዲሁ ሃላፊነታቸው ስለሆነ ብቻ (as an end in itself) መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
በመጨረሻ የምናገኘው የስነ ምግባር ፍልስፍናዊ ንድፈ ሃሳብ የክፉ-ደግ ጥናት (virtue ethics theory) ይባላል፡፡ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባለው ከአድራጊው አንጻር ነው ይላሉ፡፡ ምድራችን በተቃራኒዎች የተሞላች እንደመሆኗ መጠን ሰዎችም ክፉ ወይም ደግ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መጥፎ ሰዎች ስራቸውም ሁልጊዜ መጥፎ ሲሆን ጥሩ ሰዎችም ስራቸው ሁልጊዜ ጥሩ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ስነ ምግባርን ማስተማር የሚቻለው ጥሩ ሰዎችንና በጎ ስራቸውን በአንድ ወገን፤ክፉ ሰዎችንና መጥፎ ስራዎቻቸውን በሌላ ወገን በዝርዝር በማስጠናትና ተከታዮች በጎ ሰዎችን አብነት እንዲያደርጉና ክፉ ስራን እንዲያወግዙ በማለማመድ እንጂ ስለድርጊቱ ውጤት ወይም ምክንያት በማስላት አይደለም ይላሉ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ባህሎችና አስተሳሰቦች መናኸሪያ በሆኑ ሃገሮች ውስጥ አንድ የስነ ምግባር ፍልስፍናን ብቻ በመከተል ዜጎችን በስነ ምግባር ለማነጽ የሚቻል አይደለም፡፡ ይልቁንም የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን ከሚያስከትሉት እርካታና ስቃይ፣ከህሊና ፍርድና ከህግ እንዲሁም እንደየግለሰቡ የህይወት ፍልስፍና ከሃይማኖትም አንጻር በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ማስተማሩ በእጅጉ የሚመከር ነው፡፡

Friday, March 8, 2013

ትክክለኛ አስተሳሰብ ሲኖርህ ትክክለኛ ሰው ትሆናለህ


I wrote for Addis Admas Weekly Newspaper (Yeketit 16, 2005E.C) 
የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን ያዘዘው ዋነኛ ትእዛዝ  “ሰው ሁን” የሚል እንደነበር በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ እናነባለን፡፡ ሰው ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ሁን ተብሎ መታዘዙ ሰው መሆን በስጋና በደም ጸንቶ ከመንቀሳቀስ የዘለለ መለኪያ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው::” ሲል ደግሞ አንዱ መስፈሪያ ማሰብ (thinking) መሆኑን ይመሰክራል፡፡ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው::” በሚለው ዓረፍተ ነገር የተስማማ ሰው “ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ትክክለኛ ሰው ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር እውነትነትም በአመክንዮ መርህ መቀበል ይኖርበታል፡፡ በርግጥም ሁሉም ሰዎች ማሰባቸው እውነታ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች በትክክል ማሰባቸው ግን በጥያቄ ምልክት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በህጸጽ የተሞላ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ህጸጾቻቸውንና የተሳሳተ ድምዳሜያቸውን በየደቂቃው በንግግራቸውም ሆነ በጽሁፋቸው ሲገልጹ ይስተዋላሉና፡፡ ለመሆኑ ትክክለኛ አስተሳሰብ ምንድን ነው?
ትክክለኛ አስተሳሰብ (correct thinking) በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ የሚሰጥበት የአስተሳሰብ ስልት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው (Logic) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሃሳብ ሎጎስ (logos) ቃል ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ሲሆን የትክክለኛ አስተሳሰብ ጥበብ የሚል ትርጉም ያዘለ ነው፡፡ ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚከተለው የራሱ የሆነ ቀመር አለው፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ የትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር ማሳመኛ አንቀጽ (argumnet) ይባላል፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ አንድ ወይም ከአንድ በላይ እውነት ወይም ሀሰት ሊባሉ የሚችሉ ዓረፍተ ነገሮችን ወይም ማስረጃዎችን (premises)፤ እንዲሁም ከእነዚህ ማስረጃዎች የመነጨ አንድ መደምደሚያ ዓረፍተ ነገር (conclusion) ሊኖረው ይገባል፡፡
ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር ማናኛውንም ፍልስፍና ለመረዳትም ሆነ ለመስራት የምንገለገልበት የፍልስፍና ቋንቋ ነው፡፡ በዚህ ቀመር የሚመነጨው ድምዳሜ ፍጹማዊ (deductive) ወይም ምናልባታዊ (inductive) መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ፍጹማዊ የሚባለው ቀመር የማሳመኛ አንቀጹ ድምዳሜ ከቀረበው ማስረጃ  በፍጹም እርግጠኝነት (certainity) የመነጨ ሲሆን ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው ባቀረበው ማሳመኛ ውስጥ የዘረዘራቸው ማስረጃዎች በሙሉ እውነት ከሆኑ ከዚህ የመነጨው ድምዳሜ በምንም መንገድ ሀሰት ሊሆን አይችልም፡፡በሂሳብ ስሌት፣ በብያኔ ወይም በሲሎጂዝም ላይ ተመስርቶ የሚሰጡ ድምዳሜዎች የፍጹማዊ ድምዳሜ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ “ኢትዮጵያውን በሙሉ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው”፤ እና “አቶ ኦንጋዬ ኢትዮጵያዊ ናቸው”፤ የሚሉት ሁለት የማስረጃ ዓረፍተ ነገሮች “እውነት” መሆናቸውን ካረጋገጥንና ከዚህም  “አቶ ኦንጋዬ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በፍጹም ርግጠኝነት እንጂ በምናልባት አይደለም ማለት ነው፡፡  
በሌላ በኩል በማሳመኛ አንቀጹ መደምደሚያ ላይ የተቀመጠው ዓረፍተ ነገር ከቀረቡት ማስረጃዎች በምናልባት (probability) የመነጨ ማሳመኛ ምናልባታዊ (Inductive) ቀመር ተከትሏል ይባላል፡፡ ይህም ማለት በማሳመኛው አንቀጽ ውስጥ በማስረጃነት የቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች በሙሉ እውነት መሆናቸውን ብናረጋግጥ እንኳን ከማስረጃዎቹ የመነጨው መደምደሚያ እውነት ወይም ሀሰት የመሆኑ ጉዳይ በምናልባት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በትንበያ፣ በምስስሎሽ፣ በምልክት፣ እንዲሁም በምክንያትና በውጤት ትስስር ላይ ተመስርተው የሚቀርቡ ማሳመኛዎች የምናልባታዊ አስተሳሰብ ቀመርን መርህ የተከተሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አስር ክፍለ ከተማዎች ይገኛሉ፡፡” እና “በየካ፣ በቦሌ ፣በጉለሌ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በአቃቂ-ቃሊቲ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ” የሚሉት በማስረጃነት የቀረቡ ዓረፍተ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ካረጋገጥንና ከዚህም ተነስተን “በተቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ውስጥም እንዲሁ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ፡፡” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በምናልባት እንጂ በፍጹም ርግጠኝነት አይደለም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ስለቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ይዞታ በማሳመኛ አንቀጹ የቀረበ ግልጽ ማስረጃ ስለሌለና ድምዳሜውን የምናመነጨው በይሆናል ስለሆነ ነው፡፡  
ከህጸጽ የጸዳና ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ጥርት አድርጎ የማሰብ አቅም ይኖረዋል፡፡ ጥርት አድርጎ የሚያስብ ሰው ደግሞ ጥርት ያለና ትክክለኛ ቋንቋ ይናገራል፡፡ ትክክለኛ ቋንቋና ትክክለኛ አስተሳሰብ የተቆራኙ ናቸው፡፡ ማለትም ፍልስፍና ያለ ቋንቋ ሊገለጽ አይችልም፤ ቋንቋም በፍልስፍና ካልተቃኘ ጥርት ያለና ትክክለኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ ሊመጣ የሚችለው በማንኛውም ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ ቃላትን ትክክለኛ ፍቺና ብያኔ አውቆ በተገቢው ቦታ ላይ ብቻ መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ ቀደምት የግሪክ ፈላስፎች ፍልስፍናቸውን የጀመሩትም በዚሁ የቃላት ፍቺ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአፍላጦን መምህር ሶቅራጥስ (dialectic) ተብሎ በሚታወቀው የፍልስፍና ዘዴው በጥያቄና መልስ ከበርካታ ሰዎች ጋር በሚያደርገው ምልልስ የሥነ-ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን ትክክለኛ ብያኔና ምንነት ጥርት አድርጎ ለማወቅና ለማሳወቅ ከፍተኛ ትግል ያደርግ እንደነበር ከምዕራባውያን የፍልስፍና ታሪክ እንማራለን፡፡ ሶቅራጥስ ተማሪዎቹ ፍትህ፣ ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትዕግስት የመሳሰሉት የስነምግባር ቃላት ትርጉም በራሳቸው ተመራምረው እንዲደርሱበት በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር የቃላቱ ፍቺ ነው ብለው የሚሰነዝሩትን ምላሽ ጎዶሎነት ወይም ስህተት በአመክንዮ ያሳያቸውና የተሻለና የመጨረሻውን ትክክለኛ ብያኔ እንዲፈልጉ ያበረታታቸው ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር የጥያቄና መልስ ተሳታፊዎቹ የሶቅራጥስን ተቋቁሞ (defense) መከላከል ሲያቅታቸውና ለቀረበው ቃል አንድ የተለመደ ፍቺ እንዲነግራቸው ሲጠይቁት በማህበረሰብ አስተሳሰብ (communal thinking) ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑና በግል ፍልስፍና (individual thinking) መኖርን እንዲማሩ “የማውቀው አለማወቄን ብቻ ነው” የሚል መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡
ለቃላት ትክክለኛና ጥርት ያለ ትርጉም ለመስጠት ብሎም የቃላትን ብዥታና (vagueness) አሻሚነትን (ambiguity) ለማስወገድ ለእንዳንዱ ቃል በተለያየ አውድ ውስጥ የሚኖረውን ብያኔ በትክክል መረዳትና እያንዳንዱንም ቃል በተገቢውና በትክክለኛ ቦታ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የቋንቋ ፍልስፍና ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ “ደረቅ እንጀራ አለ” እና “ለምለም እንጀራ አለ” የሚሉትን በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች የተለመዱ ሁለት የእንጀራ ሽያጭ ማስታወቂዎችን የቃላት አጠቃቀም ትክክለኝነትን ብናነጻጽር “ደረቅ እንጀራ” የሚለው ቃል “ድርቆሽ እንጀራ” የሚለውንም ትርጉም በውስጡ ስለሚይዝ የበለጠ አሻሚ (ambigious) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ሲባል በዚህ ሐረግ ሰዎች አይግባቡበትም ማለት ሳይሆን ትክክለኛና ጥርት ያለ አስተሳሰብ ባለው ሰው የተጻፈ የጽሁፍ ሥራ መለኪያ አንባቢያን ጽሁፉን ብቻ አንብበው በቀጥታና በትክክል እንዲረዱ እንጂ በጸሐፊው አእምሮ ውስጥ የሚመላለሰውን ወይም ጸሐፊው ለመግለጽ የፈለገውን በመገመት ሞልተው እንዲገነዘቡ የማይጋብዝ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ (ሎጂክ) ወደ አንድ እውነት ወይም እውቀት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ቁልፍ ቦታ አለው፡፡ ለምሳሌ በሰይንሳዊ ጥናትና ምርምር ሂደት ውስጥ ተመራማሪው የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን በሚገባ ካልተከተለ አንድ አዲስ ግኝት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይችልም፡፡ አንድ ሃኪምም የታካሚውን ትክክለኛ በሽታ ለማወቅ መጀመሪያ ለግለሰቡ ከሚያቀርበው ቃለ መጠይቅ፣ ኋላም ከቤተ ሙከራ በግለሰቡ የጤና ችግር ዙሪያ ከሚሰበስባቸው ልዩ ልዩ መረጃዎች ላይ በመንተራስ ስለታካሚው የበሽታ ምንነት አንድ ትክክለኛ እውቀት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቻሉ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን ጉልህ ሚና የሚያመላክት ነው፡፡  
አንድ ሰው አንድን አዲስ ግኝት ወይም እውቀት እውነት ነው ብሎ ከመቀበሉ በፊት   በትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር መነጽር በጥልቀት መመርመር ይገባዋል፡፡ አንድን ድምዳሜ እውነት ወይም ሀሰት ነው ብሎ ከመደምደሙ በፊትም እንዲሁ ስለእውነት ምንነት እውነተኛ እውቀትና ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተመራማሪው የዓለም የሳይንስ ፍልስፍና (Philosophy of Science) ሊቃውንት ስለ እውነት ምንነትና ባህርይ ያቀረቧቸውን ዘርፈ ብዙ አመለካከቶች በስፋት ሊመረምርና ከእነዚህ ውስጥም እርሱ ከተሰማራበት አውድ ጋር የሚስማማ አንድ ጥርት ያለ አመክኗዊ አቋም እንደያዘ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ “እውነት አንድ ነች ወይስ ብዙ?፤ እውነት አንጻራዊ ነች ወይስ ፍጹማዊ?፤ እውነት ጊዜያዊ ነች ወይስ ዘለዓለማዊ?፤ እውነተኛ እውቀት ሳይንሳዊ ነው ወይስ ሃማኖታዊና ባህላዊ?፤ ሁሉንም እውቀት የምናገኘው ከተወለድን በኋላ በስሜት ህዋሶቻች አማካኝነት በምናካብተው ገጠመኝ ነው ወይስ አብሮን የሚወለድ እውቀት አለ?፤ እውቀት በአመክንዮና በሰብኣዊ ምልከታ ይገኛል ወይስ  በመለኮታዊ ኃይል ይገለጻል?” ወዘተ የሚሉትን አወዛጋቢ ሃሳቦች በአጽንኦት መርምሮ አንድ ትክክለኛ አቋም ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ ይህም ከትክክለኛ አስተሳሰብ (Logic) ውጪ የሚቻል አይሆንም፡፡
የራሳችንን ወይም የሌላን ሰው አስተሳሰብ በመገምገም ጥሩ ወይም መጥፎ አስተሳሰብ በማለት ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ አንድን አስተሳሰብ ትክክለኛ ወይም ህጸጽ ያለበት ብሎ ለመፈረጅ ከማሳመኛ አንቀጹ (argumnet) አወቃቀርና በማስረጃነት ከቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች የእውነታ እሴት (truth value) አንጻር በጥንቃቄ መገምገምን ይሻል፡፡ ማሳመኛ አንቀጹ ተገቢ (valid) ወይም እውነተኛ (sound) ከሆነ በድምዳሜው የተመለከተው አስተሳሰብ ትክክለኛ አስተሳሰብ ይባላል፡፡ ይሁንና ማሳመኛ አንቀጹ የማይገባ (Invalid) ከሆነ ህጸጽ ያለበት (fallacious) መሆኑ ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ ተገቢ ነው የሚባለው ድምዳሜው ከማስረጃው ከማስረጃው(ዎቹ) በትክክል የመነጨ ከሆነ፤ ወይም የቀረቡት ማስረጃዎች  በመደምደሚያው የቀረበውን ሃሳብ በትክክል ለመደገፍ የቀረቡ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ካልሆነ ወይም በአንቀጹ ውስጥ የሚገኙ ዓረፍተ ነገሮች በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር መሰረት በአመክንዮ ካልተሳሰሩ በማሳመኛ አንቀጹ የተመለከተው መደምደሚያ የተሳሳተ፤ አስተሳሰቡም ህጸጽ (Fallacy) ያለበት ነው እንላለን፡
የአስተሳሰብ ህጸጽ (Logical fallacy) የሚከሰተው በማሳመኛ አንቀጽ ላይ የቀረበው መደምደሚያ ከቀረቡት ማስረጃዎች በተገቢ (valid) መንገድ ያልወጣ ከሆነ ነው፡፡ አንድ መደመደሚያ ከማስረጃው በተገቢ መንገድ አልወጣም የሚባለው ግለሰቡ ድምዳሜውን ለመስጠት ያቀረባቸው ማስረጃዎች በመደምደሚያው ላይ ለቀረበው ይዘት አመክኖያዊ አስፈላጊነት የሌላቸው ከሆኑ፣በማሳመኛነት የቀረበው ምስስሎሽ (Analogy) ደካማ ከሆነ፣ ማሳመኛው ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ አሻሚ (ambigious) ቃላትን በመጠቀም የተገነባ ከሆነ፣ በማሳመኛው የቀረበው ድምዳሜ በቀጥታ ከማስረጃዎቹ የመነጨ ሳይሆን የግለሰቡን አመለካከትና ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ከሆነ እንዲሁም በጽሁፍ ውስጥ በስዋስው የትርጉም ምስስሎሽ ስህተት የተሳሳተ ድምዳሜ ከተሰጠ ነው፡፡