Friday, March 8, 2013

ትክክለኛ አስተሳሰብ ሲኖርህ ትክክለኛ ሰው ትሆናለህ


I wrote for Addis Admas Weekly Newspaper (Yeketit 16, 2005E.C) 
የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን ያዘዘው ዋነኛ ትእዛዝ  “ሰው ሁን” የሚል እንደነበር በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ እናነባለን፡፡ ሰው ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ሁን ተብሎ መታዘዙ ሰው መሆን በስጋና በደም ጸንቶ ከመንቀሳቀስ የዘለለ መለኪያ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው::” ሲል ደግሞ አንዱ መስፈሪያ ማሰብ (thinking) መሆኑን ይመሰክራል፡፡ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው::” በሚለው ዓረፍተ ነገር የተስማማ ሰው “ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ትክክለኛ ሰው ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር እውነትነትም በአመክንዮ መርህ መቀበል ይኖርበታል፡፡ በርግጥም ሁሉም ሰዎች ማሰባቸው እውነታ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች በትክክል ማሰባቸው ግን በጥያቄ ምልክት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በህጸጽ የተሞላ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ህጸጾቻቸውንና የተሳሳተ ድምዳሜያቸውን በየደቂቃው በንግግራቸውም ሆነ በጽሁፋቸው ሲገልጹ ይስተዋላሉና፡፡ ለመሆኑ ትክክለኛ አስተሳሰብ ምንድን ነው?
ትክክለኛ አስተሳሰብ (correct thinking) በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ የሚሰጥበት የአስተሳሰብ ስልት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው (Logic) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሃሳብ ሎጎስ (logos) ቃል ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ሲሆን የትክክለኛ አስተሳሰብ ጥበብ የሚል ትርጉም ያዘለ ነው፡፡ ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚከተለው የራሱ የሆነ ቀመር አለው፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ የትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር ማሳመኛ አንቀጽ (argumnet) ይባላል፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ አንድ ወይም ከአንድ በላይ እውነት ወይም ሀሰት ሊባሉ የሚችሉ ዓረፍተ ነገሮችን ወይም ማስረጃዎችን (premises)፤ እንዲሁም ከእነዚህ ማስረጃዎች የመነጨ አንድ መደምደሚያ ዓረፍተ ነገር (conclusion) ሊኖረው ይገባል፡፡
ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር ማናኛውንም ፍልስፍና ለመረዳትም ሆነ ለመስራት የምንገለገልበት የፍልስፍና ቋንቋ ነው፡፡ በዚህ ቀመር የሚመነጨው ድምዳሜ ፍጹማዊ (deductive) ወይም ምናልባታዊ (inductive) መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ፍጹማዊ የሚባለው ቀመር የማሳመኛ አንቀጹ ድምዳሜ ከቀረበው ማስረጃ  በፍጹም እርግጠኝነት (certainity) የመነጨ ሲሆን ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው ባቀረበው ማሳመኛ ውስጥ የዘረዘራቸው ማስረጃዎች በሙሉ እውነት ከሆኑ ከዚህ የመነጨው ድምዳሜ በምንም መንገድ ሀሰት ሊሆን አይችልም፡፡በሂሳብ ስሌት፣ በብያኔ ወይም በሲሎጂዝም ላይ ተመስርቶ የሚሰጡ ድምዳሜዎች የፍጹማዊ ድምዳሜ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ “ኢትዮጵያውን በሙሉ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው”፤ እና “አቶ ኦንጋዬ ኢትዮጵያዊ ናቸው”፤ የሚሉት ሁለት የማስረጃ ዓረፍተ ነገሮች “እውነት” መሆናቸውን ካረጋገጥንና ከዚህም  “አቶ ኦንጋዬ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በፍጹም ርግጠኝነት እንጂ በምናልባት አይደለም ማለት ነው፡፡  
በሌላ በኩል በማሳመኛ አንቀጹ መደምደሚያ ላይ የተቀመጠው ዓረፍተ ነገር ከቀረቡት ማስረጃዎች በምናልባት (probability) የመነጨ ማሳመኛ ምናልባታዊ (Inductive) ቀመር ተከትሏል ይባላል፡፡ ይህም ማለት በማሳመኛው አንቀጽ ውስጥ በማስረጃነት የቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች በሙሉ እውነት መሆናቸውን ብናረጋግጥ እንኳን ከማስረጃዎቹ የመነጨው መደምደሚያ እውነት ወይም ሀሰት የመሆኑ ጉዳይ በምናልባት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በትንበያ፣ በምስስሎሽ፣ በምልክት፣ እንዲሁም በምክንያትና በውጤት ትስስር ላይ ተመስርተው የሚቀርቡ ማሳመኛዎች የምናልባታዊ አስተሳሰብ ቀመርን መርህ የተከተሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አስር ክፍለ ከተማዎች ይገኛሉ፡፡” እና “በየካ፣ በቦሌ ፣በጉለሌ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በአቃቂ-ቃሊቲ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ” የሚሉት በማስረጃነት የቀረቡ ዓረፍተ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ካረጋገጥንና ከዚህም ተነስተን “በተቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ውስጥም እንዲሁ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ፡፡” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በምናልባት እንጂ በፍጹም ርግጠኝነት አይደለም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ስለቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ይዞታ በማሳመኛ አንቀጹ የቀረበ ግልጽ ማስረጃ ስለሌለና ድምዳሜውን የምናመነጨው በይሆናል ስለሆነ ነው፡፡  
ከህጸጽ የጸዳና ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ጥርት አድርጎ የማሰብ አቅም ይኖረዋል፡፡ ጥርት አድርጎ የሚያስብ ሰው ደግሞ ጥርት ያለና ትክክለኛ ቋንቋ ይናገራል፡፡ ትክክለኛ ቋንቋና ትክክለኛ አስተሳሰብ የተቆራኙ ናቸው፡፡ ማለትም ፍልስፍና ያለ ቋንቋ ሊገለጽ አይችልም፤ ቋንቋም በፍልስፍና ካልተቃኘ ጥርት ያለና ትክክለኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ ሊመጣ የሚችለው በማንኛውም ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ ቃላትን ትክክለኛ ፍቺና ብያኔ አውቆ በተገቢው ቦታ ላይ ብቻ መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ ቀደምት የግሪክ ፈላስፎች ፍልስፍናቸውን የጀመሩትም በዚሁ የቃላት ፍቺ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአፍላጦን መምህር ሶቅራጥስ (dialectic) ተብሎ በሚታወቀው የፍልስፍና ዘዴው በጥያቄና መልስ ከበርካታ ሰዎች ጋር በሚያደርገው ምልልስ የሥነ-ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን ትክክለኛ ብያኔና ምንነት ጥርት አድርጎ ለማወቅና ለማሳወቅ ከፍተኛ ትግል ያደርግ እንደነበር ከምዕራባውያን የፍልስፍና ታሪክ እንማራለን፡፡ ሶቅራጥስ ተማሪዎቹ ፍትህ፣ ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትዕግስት የመሳሰሉት የስነምግባር ቃላት ትርጉም በራሳቸው ተመራምረው እንዲደርሱበት በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር የቃላቱ ፍቺ ነው ብለው የሚሰነዝሩትን ምላሽ ጎዶሎነት ወይም ስህተት በአመክንዮ ያሳያቸውና የተሻለና የመጨረሻውን ትክክለኛ ብያኔ እንዲፈልጉ ያበረታታቸው ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር የጥያቄና መልስ ተሳታፊዎቹ የሶቅራጥስን ተቋቁሞ (defense) መከላከል ሲያቅታቸውና ለቀረበው ቃል አንድ የተለመደ ፍቺ እንዲነግራቸው ሲጠይቁት በማህበረሰብ አስተሳሰብ (communal thinking) ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑና በግል ፍልስፍና (individual thinking) መኖርን እንዲማሩ “የማውቀው አለማወቄን ብቻ ነው” የሚል መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡
ለቃላት ትክክለኛና ጥርት ያለ ትርጉም ለመስጠት ብሎም የቃላትን ብዥታና (vagueness) አሻሚነትን (ambiguity) ለማስወገድ ለእንዳንዱ ቃል በተለያየ አውድ ውስጥ የሚኖረውን ብያኔ በትክክል መረዳትና እያንዳንዱንም ቃል በተገቢውና በትክክለኛ ቦታ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የቋንቋ ፍልስፍና ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ “ደረቅ እንጀራ አለ” እና “ለምለም እንጀራ አለ” የሚሉትን በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች የተለመዱ ሁለት የእንጀራ ሽያጭ ማስታወቂዎችን የቃላት አጠቃቀም ትክክለኝነትን ብናነጻጽር “ደረቅ እንጀራ” የሚለው ቃል “ድርቆሽ እንጀራ” የሚለውንም ትርጉም በውስጡ ስለሚይዝ የበለጠ አሻሚ (ambigious) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ሲባል በዚህ ሐረግ ሰዎች አይግባቡበትም ማለት ሳይሆን ትክክለኛና ጥርት ያለ አስተሳሰብ ባለው ሰው የተጻፈ የጽሁፍ ሥራ መለኪያ አንባቢያን ጽሁፉን ብቻ አንብበው በቀጥታና በትክክል እንዲረዱ እንጂ በጸሐፊው አእምሮ ውስጥ የሚመላለሰውን ወይም ጸሐፊው ለመግለጽ የፈለገውን በመገመት ሞልተው እንዲገነዘቡ የማይጋብዝ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ (ሎጂክ) ወደ አንድ እውነት ወይም እውቀት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ቁልፍ ቦታ አለው፡፡ ለምሳሌ በሰይንሳዊ ጥናትና ምርምር ሂደት ውስጥ ተመራማሪው የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን በሚገባ ካልተከተለ አንድ አዲስ ግኝት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይችልም፡፡ አንድ ሃኪምም የታካሚውን ትክክለኛ በሽታ ለማወቅ መጀመሪያ ለግለሰቡ ከሚያቀርበው ቃለ መጠይቅ፣ ኋላም ከቤተ ሙከራ በግለሰቡ የጤና ችግር ዙሪያ ከሚሰበስባቸው ልዩ ልዩ መረጃዎች ላይ በመንተራስ ስለታካሚው የበሽታ ምንነት አንድ ትክክለኛ እውቀት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቻሉ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን ጉልህ ሚና የሚያመላክት ነው፡፡  
አንድ ሰው አንድን አዲስ ግኝት ወይም እውቀት እውነት ነው ብሎ ከመቀበሉ በፊት   በትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር መነጽር በጥልቀት መመርመር ይገባዋል፡፡ አንድን ድምዳሜ እውነት ወይም ሀሰት ነው ብሎ ከመደምደሙ በፊትም እንዲሁ ስለእውነት ምንነት እውነተኛ እውቀትና ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተመራማሪው የዓለም የሳይንስ ፍልስፍና (Philosophy of Science) ሊቃውንት ስለ እውነት ምንነትና ባህርይ ያቀረቧቸውን ዘርፈ ብዙ አመለካከቶች በስፋት ሊመረምርና ከእነዚህ ውስጥም እርሱ ከተሰማራበት አውድ ጋር የሚስማማ አንድ ጥርት ያለ አመክኗዊ አቋም እንደያዘ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ “እውነት አንድ ነች ወይስ ብዙ?፤ እውነት አንጻራዊ ነች ወይስ ፍጹማዊ?፤ እውነት ጊዜያዊ ነች ወይስ ዘለዓለማዊ?፤ እውነተኛ እውቀት ሳይንሳዊ ነው ወይስ ሃማኖታዊና ባህላዊ?፤ ሁሉንም እውቀት የምናገኘው ከተወለድን በኋላ በስሜት ህዋሶቻች አማካኝነት በምናካብተው ገጠመኝ ነው ወይስ አብሮን የሚወለድ እውቀት አለ?፤ እውቀት በአመክንዮና በሰብኣዊ ምልከታ ይገኛል ወይስ  በመለኮታዊ ኃይል ይገለጻል?” ወዘተ የሚሉትን አወዛጋቢ ሃሳቦች በአጽንኦት መርምሮ አንድ ትክክለኛ አቋም ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ ይህም ከትክክለኛ አስተሳሰብ (Logic) ውጪ የሚቻል አይሆንም፡፡
የራሳችንን ወይም የሌላን ሰው አስተሳሰብ በመገምገም ጥሩ ወይም መጥፎ አስተሳሰብ በማለት ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ አንድን አስተሳሰብ ትክክለኛ ወይም ህጸጽ ያለበት ብሎ ለመፈረጅ ከማሳመኛ አንቀጹ (argumnet) አወቃቀርና በማስረጃነት ከቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች የእውነታ እሴት (truth value) አንጻር በጥንቃቄ መገምገምን ይሻል፡፡ ማሳመኛ አንቀጹ ተገቢ (valid) ወይም እውነተኛ (sound) ከሆነ በድምዳሜው የተመለከተው አስተሳሰብ ትክክለኛ አስተሳሰብ ይባላል፡፡ ይሁንና ማሳመኛ አንቀጹ የማይገባ (Invalid) ከሆነ ህጸጽ ያለበት (fallacious) መሆኑ ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ ተገቢ ነው የሚባለው ድምዳሜው ከማስረጃው ከማስረጃው(ዎቹ) በትክክል የመነጨ ከሆነ፤ ወይም የቀረቡት ማስረጃዎች  በመደምደሚያው የቀረበውን ሃሳብ በትክክል ለመደገፍ የቀረቡ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ካልሆነ ወይም በአንቀጹ ውስጥ የሚገኙ ዓረፍተ ነገሮች በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር መሰረት በአመክንዮ ካልተሳሰሩ በማሳመኛ አንቀጹ የተመለከተው መደምደሚያ የተሳሳተ፤ አስተሳሰቡም ህጸጽ (Fallacy) ያለበት ነው እንላለን፡
የአስተሳሰብ ህጸጽ (Logical fallacy) የሚከሰተው በማሳመኛ አንቀጽ ላይ የቀረበው መደምደሚያ ከቀረቡት ማስረጃዎች በተገቢ (valid) መንገድ ያልወጣ ከሆነ ነው፡፡ አንድ መደመደሚያ ከማስረጃው በተገቢ መንገድ አልወጣም የሚባለው ግለሰቡ ድምዳሜውን ለመስጠት ያቀረባቸው ማስረጃዎች በመደምደሚያው ላይ ለቀረበው ይዘት አመክኖያዊ አስፈላጊነት የሌላቸው ከሆኑ፣በማሳመኛነት የቀረበው ምስስሎሽ (Analogy) ደካማ ከሆነ፣ ማሳመኛው ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ አሻሚ (ambigious) ቃላትን በመጠቀም የተገነባ ከሆነ፣ በማሳመኛው የቀረበው ድምዳሜ በቀጥታ ከማስረጃዎቹ የመነጨ ሳይሆን የግለሰቡን አመለካከትና ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ከሆነ እንዲሁም በጽሁፍ ውስጥ በስዋስው የትርጉም ምስስሎሽ ስህተት የተሳሳተ ድምዳሜ ከተሰጠ ነው፡፡         

ስትሠራ እንጂ ስታስብ መሳሳት የለብህም


“የማይሠራ ሰው አይሳሳትም” የሚለው አባባል የሰው ልጅ በስራ ላይ ሳለ ስህተት ቢፈጽም እንኳ ሰብዓዊ ባህርይ ነውና ከስህተቱ እንዲማር መምከር እንደሚገባ እንጂ በአግራሞት የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ነገር ግን በስራው ላይ የተፈጠረው ስህተት ከተግባር ሳይሆን ከተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ከሆነ ነገሩ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም   በአስተሳሰቡ ላይ ህጸጽ ያለበት ሰው የሚሰራው ወይም የሚናገረው ሁሉ ስህተት ስለሆነና ለእርሱ ለባለቤቱ ግን ስህተቱ ሁሉ ትክክል ስለሚመስለው በቀላሉ እውነት ላይ ለመድረስ ወይም ትክክለኛ ስራ ለመስራት እጅግ በጣም ከባድ ይሆንበታልና፡፡   
የሚናገሩና የሚጽፉ ሰዎች ስለትክክለኛ አስተሳሰብ ምንነት ባለማወቅ ወይም እያወቁ ሌሎችን ለማታለል በማሰብ የአስተሳሰብን ህጸጾችን (ፋላሲ) ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ህጸጾች በቅዱሳት መጻህፍት አረዳድና አተናተን፣ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የማስታወቂያ ቋንቋ፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች፣በፖሊስ ምርመራና በፍርድ ቤት ችሎት ሂደት፣ በታላላቅ ስብሰባዎችና ክርክር መድረኮች፣ በአሰሪና ሰራተኛ የስራ ምልልስ እንዲሁም በግለሰቦች የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስና በመሳሰሉት ማናቸውም የህይወት መድረኮች ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡
አሪስጣጣሊስና ከእርሱ በኋላ የተነሱ የትክክለኛ አስተሳሰብ ጠበብት የአስተሳሰብ ህጸጾችን በተለያዩ ፈርጆች ከፋፍለው አቅርበዋል፡፡ የዚህ ጹሁፍ ዋና ዓላማም አንባብያን የአስተሳሰብ ህጸጾችን ምንነት፣ እንዲሁም የሚፈጸሙበትን ምክንያት በዝርዝር በማጥናት የተሳሳተ ውሳኔ ከመስጠት ራሳቸውን እንዲቆጥቡና በሌሎች ከተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ንግግርና ጽሁፍ  እንዳይታለሉ  መታደግ ነው፡፡         
የመጀመሪው የአስተሳሰብ ህጸጽ ከዕውቀት ማነስ (ignorance) የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “ስለ መላዕክት ህልውና በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም፡፡” ከሚል አንድ ማስረጃ ላይ ተነስቶ “በዓለም ላይ መላዕክት የሚባሉ ነገሮች የሉም” የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርስ ስህተት ላይ ይወድቃል፤ ምክንያቱም አንድን ድምዳሜ ለመስጠት አለማወቅን እንደ አመክንዮ መጠቀም የአስተሳሰብ ህጸጽ ከመሆኑም ባሻገር ትክክለኛው የአስተሳሰብ መርህ ነገሩን አስከምናውቀው ድረስ ድምዳሜ ከመስጠት መቆጠብን ያስተምራልና፡፡
ሁለተኛው የአስተሳሰብ ህጸጽ አካላዊ ወይም ስነልቦናዊ ኃይልን በመጠቀም ወይም በማስፈራራት ለማሳመን በሚደረግ ሙከራ የሚፈጠር ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ግለሰብ ፈጸመ ስለተባለው ወንጀል ለማሳመን ልዩ ልዩ የድምጽ፣ የምስልና የሰው ማስረጃዎችን በማቅረብ ፈንታ ተጠርጣሪው ላይ አካላዊ ጥቃት (ድብደባ) በማድረስ ወይም በማስፈራራት ግለሰቡ ያልሰራውን ሰርቻለሁ፣ ያልፈጸመውን ፈጽሜያለሁ ብሎ የእምነት ቃሉን እንዲሰጥ በማስገደድ አሳምኖት ተጠርጣሪው ወንጀሉን እንደፈጸመ አምኗል የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርስ በትክክለኛ አስተሳሰብ መርህ መሰረት ኃይልን መጠቀም (Appeal to Force) የተባለውን የአስተሳሰብ ህጸጽ ፈጽሟል ማለት ነው፡፡
በአድማጭ ወይም በአንባቢው ልብ ውስጥ የሐዘን ስሜትን በመጫር (Appeal to Pity) ለማሳመን የሚደረግ ሙከራ ሶስተኛው የአስተሳሰብ ህጸጽ መገለጫ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በግል ኑሮው ላይ የገጠመውን ችግር እንባ በተቀላቀለበት ሁኔታ ዘርዝሮ ለመምህሩ በማስረዳት ምንም እንኳን የትምህርቱን ይዘት በሚፈለገው ደረጃ ባያውቀውም መምህሩ እንዲያዝንለትና ጥሩ ውጤት እንዲመዘግብለት አስተዛዝኖ ቢለምንና ቢሳካለት ተማሪው መምህሩን የአስተሳሰብ ህጸጽ ውስጥ ዘፍቆታል ማለት ነው፡፡          
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ አብዛኞቹ የተማሪዎች የብሄር ግጭቶች የብዙሃኑን ስሜት በጅምላ ማነሳሳት (Mob mentality) በሚባል ለሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ በአብነት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ትክክለኛ አስተሳሰብ ከስሜታዊነትና ከቡድን መንፈስ የጸዳ፤ በአመክንዮና በተረጋጋ ግላዊ ተመስጦ የሚደረስበት መንገድ ነው፡፡ ሰዎች የበለጠ ስሜታውን እየሆኑ በመጡ ቁጥር ይበልጡኑ ከአመክንዮ እየራቁ ይመጣሉ፤ ይበልጡኑ ከአመክንዮ በራቁ ቁጥር ይበልጡኑ የአስተሳሰብ ህጸጽ ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ለዚህም ነው የተለያየ ብሄረሰብ አባላት በሆኑ ሁለት ግለሰብ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረን ተራ ዕለታዊ ግጭት “የብሄራችን ልጅ ተነካ!” በሚል የቡድን (mob) ስሜት ተነሳስተው በማይመለከታቸው ጉዳይ በርካታ ተማሪዎች አላስፈላጊ የብሄር ግጭት ውስጥ ሲገቡና ራሳቸውን ችግር ላይ ሲጥሉ የምንመለከተው፡፡
በማስታወቂያ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የአስተሳሰብ ህጸጾች አንድ ግለሰብ ራሱን ከብዙሃኑ ጋር በማነጻጸር የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት እንዲፈጠርበት በማድረግ እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ከአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ጋር በማቆራኘት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውና (Bandwagon Argument) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ ግለሰቡ ራሱን ከብዙሃኑ ጋር በማነጻጸር የበታችነት ስሜት እንዲሰማውና ከዚህ አሉታዊ ስሜትም ለመውጣት ሲል ብቻ ተገቢ ምክንያት ሳያገኝ በማሳመኛው መደምደሚያ ላይ የቀረበውን ዓረፍተ ነገር እውነትነት እንዲቀበል የሚገደድበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የፊልም ማስታወቂያ “በድፍን አዲስ አበባ መነጋገሪያ የሆነ ድንቅ ፊልም…” ወይም አንድ የቢራ ካምፓኒ “በመላ ሃገሪቱ ተወዳጅ የሆነ ድንቅ ቢራ…” የሚሉ ሃረጎችን በመጠቀም ምርቶቻቸውን ሲያስተዋዉቁ ሰምተው ይሆናል፡፡ “በድፍን” ወይም “በመላ”  የሚሉትን የብዙሃን መገለጫ ቃላትን በመጠቀም አድማጩ ግለሰብ “እኔ ከብዙሃኑ ወደኋላ ቀርቻለሁ” የሚል ስሜት እንዲያጭርበትና ምርቱን ወይም አገልግሎቱን እንዲጠቀም የሚደረግበት ነው፡፡ ሁለተኛው አድማጩ ግለሰብ ራሱን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር “እኔ እንደ ሌላው ተራ ተርታ ሰው አይደለሁም!” የሚል ስሜት እንዲፈጠርበትና ምርቱን ወይም አገልግሎቱን በመጠቀም ራሱን ከተራ ሰዎች እንደለየና ልዩ ክብር እንዳለው በማሰብ የሚኮፈስበት የአስተሳሰብ ህጸጽ (Appeal to Snobbery) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ለምሳሌ ልዩ ልዩ የሙዚቃ ኮንሰርቶች በሚዘጋጁበት ጊዜ በአንደኛ ማዕረግና በተራ የመግቢያ ትኬት መሃል ያለውን እጅግ በጣም የገዘፈን የዋጋ ልዩነት በርካታ ሰዎች እንደ ተገቢ (reasonable) የዋጋ ልዩነት የሚቀበሉት በዚህ የአሰተሳሰብ ህጸጽ ተገፍተው ነው፡፡ ሶስተኛውና (Appeal to Vanity) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ የሚፈጠረው ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ታዋቂና በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ካላቸው ስፖርተኞች፣ የፊልም ተዋናዮች፣የቁንጅና ንግስቶችና ሌሎች ዝነኛ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ጋር በማቆራኘት ህዝቡ ለግለሰቦቹ ወይም ለቡድኖቹ ያለውን አድናቆት ሳያስበው ወደሚተዋወቀው ምርትም እንዲያስተላልፍ በማድረግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልናስተውል የሚገባው በትክክለኛ የአስተሳሰብ መርህ መሰረት አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ለመጠቀምም ሆነ ላለመጠቀም ከግምት ሊገባ የሚገባው የምርቱ ወይም የአገልግሎቱ የጥራት ደረጃና ለዚህም የሚቀርበው ዝርዝር ማሳመኛ እንጂ ራስን ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር ማነጻጸር ወይም ምርትን ከዝነኛ ሰዎች ጋር በማቆራኘት የሚገኝ የስሜት እርካታ አለመሆኑን ነው፡፡   
በፓለቲካዊ የክርክር መድረኮች በተደጋጋሚ የሚደመጠው የአስተሳሰብ ህጸጽ ደግሞ የተከራካሪውን ግለሰብ ሀሳብ በመቃወም ፈንታ ራሱን ተከራካሪውን ግለሰብ በመንቀፍ ወይም  ስብዕናውን በልዩ ልዩ መንገድ በመንካት (against the person) የሚፈጸም ነው፡፡ ይህም በሦስት መንገድ ሊተገበር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ክርክር ወቅት ፕሬዚደንት ኦባማ ተቃራኒያቸው የአቶ ሩምኒን የምጣኔ ሃብት ፓሊሲ ሲያጣጥሉ ካቀረቧቸው በርካታ ተገቢ ማሳመኛዎች በተጨማሪ አቶ ሩምኒ “በፖሊሲያቸው ላይ ወጥ አቋም የሌላቸው ባለ ሁለት ምላስ ሰው ናቸው” በሚል ዘለፋ የተቀላቀለበት ንግግር ተቃራኒያቸውን ሲያሸማቅቁ ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ ይህ አቀራረብ በብዙዎች ዘንድ ትክክል መስሎ ቢታይም  የተቃራኒን ሃሳብ እንጂ ተቃራኒውን ግለሰብ ራሱን በቀጥታ በመንቀፍ የሚቀርብ ማሳመኛ (Abusive) ለሚባለው መሰረታዊ የአስተሳሰብ ህጸጽ የተጋለጠ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ሁለት ግለሰቦች በሃገራችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የማስተማሪያ ቀንቋ “በአፍ መፍቻ ወይስ በሁለተኛ” በሚል ክርክር በሚያደርጉበት አንድ መድረክ ላይ “የአፍ መፍቻን የትምህርት ቋንቋ ማድረግ አይገባም” የሚል አቋም ይዞ የሚሟገተው ግለሰብ በተቃራኒው ላይ  በማሳመኛነት ካነሳቸው ነጥቦች አንዱ “የአፍ መፍቻ ቋንቋን ደግፎ የቀረበው ተቃራኒው ግለሰብ እንዲህ ብሎ የሚከራከረው ‘ካድሬ’ ስለሆነ ነው እንጂ እውነታን ይዞ አይደለም!” የሚል ነበር፡፡ ከአመክንዮ ራቅ ብሎ ለሚያዳምጥ ሰው ጥሩ ማሳመኛ የቀረበ ቢመስለውም በትክክለኛ የአስተሳሰብ መርህ ሚዛን ግን (circumstantial) የሚባል ህጸጽ ተፈጽሟል እንላለን፤ ምክንያቱም የተገቢ አጸፋ ማሳመኛ (counter-argument) ዋና መገለጫ በቀጥታ ተቃራኒውን ግለሰብ ሃሳብ ውድቅ ማድረግ እንጂ ተቃራኒው ግለሰብ ስለሚገኝበት ሁኔታ በመተረክ አድማጭ ሃሳቡን እንዲያጣጥለው ማድረግ አይደለምና፡፡        
በተለይ ከፍተኛ ማህበራዊና ሙያዊ ኃላፊነት ላይ የሚገኙና ለሌሎች አርአያ መሆን የሚገባቸው ግለሰቦች የሚያስተምሩትና የሚተገብሩት ድርጊት ተቃራኒ የሆነበትን አጋጣሚ ፈልፍሎ በማውጣት ይህንን ድክመታቸውን እንደ ምክንያት ለራሳቸው መልሰው በማቅረብ መልስ አልባ አድርጎ ለማሳመን የሚሞከርበት የተሳሳተ የአስተሳሰብ መንገድ (you too) ይባላል፡፡ ለምሳሌ አንድ የድርጅት መሪ ሙስና ወንጀል ነው ብሎ እያስተማረ በሆነ አጋጣሚ እርሱ ራሱ በሙስና ተዘፍቆ ቢገኝ ከግለሰቡ ድርጊት ተነስተው ከተከታዮቹ አንዳንዶቹ ሙስና ወንጀል አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ ግንዛቤያቸው (you too) በተባለው የአስተሳሰብ ህጸጽ የተቃኘ ስለሆነ የተሳሳተ ነው ማለት ነው፡፡
በተለምዶ ማስቀየስ (Red Herring) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ስህተት በርካታ ሰዎች በየዕለቱ ሲጠቀሙበት የሚስተዋል ሲሆን ይህም ግለሰቡ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ተገቢ ማስረጃ አቅርቦ በማሳመን ፈንታ ሃሳብን በእጅጉ የሚሰርቅ አጓጊ ርዕስ በመፍጠር የአድማጭን ሃሳብ በመበታተን የሚፈጸም ነው፡፡
በማስረጃዎቹና በድምዳሜው መሃል የተፈጠረው ግነኑኝነት ምናባዊ በሆኑ የምክንያትና ውጤት ትስስር ላይ ተመስርቶ ከሆነ ወይም ለአንድ ድምዳሜ ምክንያት የሆነውን ነገር እንደ ውጤት፤ ውጤቱን ደግሞ እንደ ምክንያት አዟዙሮ በማሰብ፤ ወይም ለአንድ ውጤት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችል እየታወቀ አንድን ምክንያት ብቻ መርጦ በማቅረብ እንደ ዋናና ብቸኛ ምክንያት በማቅረብ ወይም አንድ ቀላል ኩነት (event) ሊያደርስ የሚችለውን ምናባዊ አደጋ ካለምንም ማስረጃ እጅግ በጣም አግዝፎ (አካብዶ) በማቅረብ አድማጭን አምታትቶ በምናባዊ ፍርሃት አሳቅቆ ለማሳመን በሚደረግ ሙከራ የሚፈጸም የአስተሳሰብ ስህተት የሀሰት ሰበብ (False cause) በመባል ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል በትክክለኛ ማሳመኛ ውስጥ የሚገኝ መደምደሚያ ከቀረቡት ማስረጃዎች መመንጨት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ጀማሪ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች በጥናታቸው መደምደሚያ ላይ የሚያመጡትን ውጤት ጥናቱን ከመጀመራቸው በፊት በመገመት መላምታቸውን (hypothesis) በሚሰበስቡት መረጃዎች ላይ ተመስርተው በመፈተሽ ፈንታ ግምታቸውን በድምዳሜ ላይ በማስቀመጥ መረጃዎቻቸውን ጠምዝዘው የእነርሱን ሃሳብ በግድ እንዲደግፍ ለማድረግ በመሞከር የሚፈጠር ስህተት ፕሪዘምሽን ህጸጽ (Fallacy of Presumption) ይባላል፡፡ ይህ ህጸጽ በማሳመኛ ውስጥ የሚገኝንና መደምደሚያውን ሃሰት የማድረግ አቅም ያለውን አንድ ቁልፍ ማስረጃ በመሰወር ወይም በመደምደሚያው ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ በማስረጃነት ደግሞ በማቅረብ ሊፈጸም ይችላል፡፡
በፍርድ ቤት ችሎት የምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የአስተሳሰብ ስህተቶች በመስቀለኛ ጥያቄ አቀራረብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ይህም መስቀለኛ ጥያቄ የሚያቀርበው አካል ለመስካሪው አንድ ውስብስብ ጥያቄ (complex question) ያቀርብና ምስክሩ ለዚህ ጥያቄ አንድ “አዎ” ወይም “አይደለም” የሚል መልስ እንዲሰጥ ይጠየቃል፤ ይሁንና ግለሰቡ የሚሰጠው ማንኛውም መልስ በሁለት መንገድ ሊተነተን የሚችል በመሆኑ ምስክሩ ባላሰበበት መንገድ ድምዳሜ በመስጠት ከምስክሩ አፍ ማረጋገጫ እንደተገኘ አድርጎ በማቅረብ የሚፈጠር ህጸጽ ወይም ማደናገሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት ከማንም ጋር ግኑኝነት ላልነበረው ሰው “ከወንጀለኞቹ ጋር ማታ ማታ መገናኝት ትተሃል?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብለትና ግለሰቡም “አዎ” የሚል መልስ ቢሰጥ አሁን ትቷል ነገር ግን ከዚህ በፊት ማታ ማታ ይገናኝ ነበር የሚል መደምደሚያ ይሰጥበታል፤ “አልተውኩም” ቢልም እንዲሁ ግኑኝነት አለኝ የሚል እምነት ቃል እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው “አዎ” ወይም “አልተውኩም” ከሚል መልስ ተቆጥቦ ጥርት ባለ ቋንቋ “እስከ ዛሬ ከማንም ጋር ግኑኝነት አልነበረኝም::” የሚል መልስ በመስጠት ራሱን መከላከል ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም በሰዋስው ምስስሎሽ (gramatical analogy) ባለቸው ቅርበት ሳቢያ የቡድንን መገለጫ ለነጠላ እንዲሁም ነገሮች በነጠላ ያላቸውን ባህርይ ለቡድን በማይገባ ሁኔታ በማስተላለፍ የሚፈጠር ህጸጽ እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ “ኢትዮጵያውያን በጨዋነትና በእንግዳ ተቀባይነት የታወቁ ናቸው” ከሚለው የቡድን መገለጫ ተነስተን “ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጨዋና እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ ወይም “በዋልዎቹ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ የሚገኝ እንዳንዱ ተጨዋች ምርጥ ነው፡፡” ከሚል የነጠላ ብቃት ተነስተን “ስለዚህ የዋልያዎቹ ቡድን ምርጥ የእግር ኳስ ቡድን ነው፡፡” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ስህተት ይሆናል፤ ምክንያቱም እንደ ቡድን ምርጥ ለመሆን ምርጥ ተጨዋቾችን ብቻ መያዝ በቂ ምክንያት አይደለምና፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊ መጻህፍትን አንብቦ በትክክል የመተንተንና የመረዳት ሂደት (hermeunitics) ላይ የሚፈጠሩ በርካታ ህጸጾች (exegetical fallacies) የሚገኙ ሲሆን የጥንታዊ መጻህፍት ተመራማሪዎች (philologists) በተለይ የቅዱሳት መጻህፍት መምህራን፣ ሰባክያን ወይም የሥነ-መለኮት ምሁራን (theologians) በጥልቀት ሊያጠኗቸውና ራሳቸውን የተሳሳተ ትንታኔ ላይ ከመጣል ይጠብቁባቸው ዘንድ የትክክለኛ አስተሳበስ ጠበብት ይመክራሉ፡፡ 
                                ›››››…..‹‹‹‹‹

Monday, March 4, 2013

የአምላክን መኖር በፍልስፍና ማረጋገጥ ይቻላልን?



የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም (universe) ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣ የሚቆጣጠር፣ ከሰው ልጆች እውቀትና ኃይል በላይ የሆነ አምላክ (God) የሚባል ላዕላይ ነገር (Being) የመኖሩ ወይም ያለመኖሩ ጥያቄ የዓለም ጠቢባንን ለበርካታ ዘመናት ሲያስጨንቅ የሰነበተና ዛሬም ድረስ ብዙዎችን በማወዛገብ ላይ የሚገኝ ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡
ለመሆኑ አምላክ አለ? መኖሩን ወይም አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል? እንዴት? በእምነት ብቻ? በፍልስፍና ? በሳይንስ? በእምነትና በፍልስፍና?
መልሱ እንደየዘመናቱና እንደየመላሾቹ ግለሰቦች ማንነት ሃማኖታዊ፣ ሳይንሳዊ ወይም ፍልስፍናዊ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሃይማኖታዊው ምላሽ የአምላክን ህልውና በቅዱሳት መጻህፍት ምስክርነት (Scriptural truth) ወይም በምስጢራዊ መገለጽ (revelation) ማረጋገጥ ስለመቻሉ ሲያስረግጥ፤ ሳይንሳዊው ምልከታ ደግሞ የአምላክ ህልውና ጥያቄ በሳይንሳዊ መንገድ ሊረጋገጥ የሚችል (verifiable) አይደለም ይላል፡፡
የፍልስፍናን አተያይ ስንመለከት በአንድ በኩል በርካታ ፈላስፎች (theists) የአምላክን ህልውና በፍልስፍና ማረጋገጥ ይቻላል የሚል እምነት ሲያራምዱ ሌሎች ደግሞ (Atheists) በተቃራኒው ስለአምላክ አለመኖር በፍልስፍና ማረጋገጫ መስጠት ይቻላል በሚል በሁለት ጎራ ተከፍለው ለዘመናት ተካራክረዋል፤ አስተምረዋል፤ ጽፈዋልም፡፡ ከዚህም ባሻገር የአምላክን ሆነ የሌሎች መንፈሳዊ አካላትን ህልውና ማረጋገጥ ወይም ስለመኖራቸውም ሆነ ስላለመኖራቸው እርግጠኛ መሆን በጭራሽ አይቻልም የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ጎኖስቲካዊ አመለካከት ያላቸው ፈላስፎች  (agnostics) ማዕከላዊ የሆነ አቋም ይዘው ሁለቱ ጽንፎች ሲያቀራርቡ ኖረዋል፡፡  
በዚህ ክፍል ላይ “የአምላክን ህልውና በፍልስፍና ማረጋገጥ ይቻላል!” የሚለውን የፍልስፍና መስመር ተከትለው የቅዱሳት መጻህፍትን ምስክርነት ሳይሹ በአመክንዮ (reasoned argument) ላይ ብቻ ተመስርተው ለአምላክ ህልውና ፍልስፍናዊ ማረጋገጫ የሰጡ ፈላስፎችን ስራ ለማየት እንሞክራለን፡፡
የፈጣሪን ህልውና ከሚቀበሉና የአምላክን ህልውና በአመክንዮ ማረጋገጥ ይቻላል ብረው ከተከራከሩ ፈላስፎች መሃል አንሰልም፣ አኳይናስ፣ ኦውግስቲን ከክርስትናው፤ እንዲሁም አቬሲናና አቬሮስ ደግሞ ከእስልምናው ዓለም በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
አምላክ (God) የሚለው ቃል በበርካታ ፈላስፎች ስራዎች ውስጥ የምናገኘው ቃል ቢሆንም ቃሉን የተለያየ ሃሳብን ለመግለጽ ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌ ቴሊስ ውሃን፣ ሬኔ ዴካርት አምላክን፣ እንዲሁም አንሰልም፣ አኳይናስና ኦውግስቲን ደግሞ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ለማመልከት ተጠቅመውበታል፡፡
አንሰልም ከ1033-1109 ዓ.ም የነበረ ጣልያናዊ የስነመለኮት ምሁርና ፈላስፋ ሲሆን Monologion እና Proslogion በተባሉ ስራዎቹ የእግዚአብሄርን ህልውና ማረጋገጫ ፍልስፍና (ontological argument) ያቀረበ ነው፡፡
የአንሰልም የማረጋገጫ ፍልስፍና መዋቅር (framework) በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ እምነት (reasoned faith) አንዲኖር የሚያስረግጥ ሲሆን ይህም እምነትን (faith) ከአመክንዮ (reason) የሚያስቀድመውን ነባር አስተሳሰብ የሚቃረን ነው፡፡
እንደ አንሰልም እምነት የክርስትና እምነት ዶግማ በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላክ ራሱ በላዕላይ አመክንዮ (supreme reason) የሚመራና በፈጠራቸው ፍጥረታት ላይ ይኸው ጥበቡ የሚገለጽ በመሆኑ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር የሰው ልጆች ሁሉ አመክንዮ ከአምላክ የተሰጣቸው ስለሆኑና የእምነት መነሻ ምክንያትን መገንዘብ ስለሚችሉ አስቀድመው ህልውናውን የሚያምኑ ክርስቲኖችም ሆነ በቅዱሳት መጻህፍት የማያምኑ ግለሰቦች ሁሉ የእግዚአብሔርን ህልውና በአመክንዮ ላይ ብቻ ተመስርተው ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡
አንሰልም ካቀረባቸው እርስ በርሳቸው የተያያዙ ሶስት ማረጋገጫዎች መካከል የመጀመሪያው ደረገው በዓለም ካሉ ጥሩ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አንድ ጥሩ ነገር    (Supreme Good) መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በመቀጠልም ይህንንም ማረጋገጫ ተንተርሶ ከሁሉም በላይ የሆነ ባህርይ ያለው (Supreme Nature) አካል መኖሩን ማረጋገጥ፤ በመጨረሻም በሁለተኛው ማረጋገጫ ላይ ተመርኩዞ በሁሉም ነገር ከሁሉም የበለጠ አካል (Most Excellent Being) ወይም አምላክ መኖሩን በማረጋገጥ ይደመድማል፡፡
የአንሰልም የመጀመሪው ማረጋገጫ የመልካሞች ሁሉ መልካም የሆነ ነገር  (Supreme Good) ስለመኖሩ ነው፡፡
በዓለማችን ላይ በርካታ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ የጥሩነታቸውን መጠን ስናወዳድር ግን ጣት ከጣት ይበልጣል እንደሚባለው አንዱ ጥሩ ነገር ከሌላው መብለጡ የግድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፈረስ ከሌላው፤ መልካም ፈረስ የሚባለው ከጥንካሬውና ከፍጥነቱ አንጻር ነው፡፡ ይሁንና ጠንካራና ፈጣን የሆነ ዘራፊ ግን መልካም ሰው ሊባል አይችልም፤ መጥፎ እንጂ፡፡ በመሆኑም አንጻራዊ የሆነ መልካምነት (Good) ያላቸው ነገሮች በራሱ (Intrisitically) መልካም ከሆነ ነገር አንጻር ያነሰ መልካምነት ያላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር መልካም እንጨት፣ መልካም ፈረስ፣ መልካም ሰው ሁሉም በመጠኑ መልካም የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ መልካም ናቸው ብለን በደመደምንበት መስፈርት አሰሳ ብናካሂድ ለእነርሱ አቻ የሆኑ ሌሎች መልካም ሰዎች፣ ፈረሶችና ሰዎችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ነገር ግን መልካም እንጨት ከመልካም ፈረስ ወይም ከመልካም ሰው ጋር አንድ ዓይነት የመልካምነት ባህርይ ስለሌላቸው የአንዱን መልካምነት ከሌላው ጋር ማወዳደር ትክክል አይሆንም፤ ሁሉም ከአቻዎቻቸው ጋር ይነጻጸራሉ እንጂ፡፡
በመሆኑም አንዱ መልካም ነገር ከሌላው መብለጡ ግድ ከሆነና ከላይ የተመለከትናቸው ነገሮች መልካምነት አንጻራዊ ነው ከተባለ ከመልካም ነገሮች ሁሉ የላቀ መልካም የሆነ፣ ለመልካምነቱ አቻ የሌለው መልካምነቱም ከራሱ የመነጨ (Intrisitic) አንድ አካል አለ ብሎ መደምደም አመክኗዊ ይሆናል፡፡ መልካም ነገሮች ሁሉ እንደሚወደዱ ሁሉ ይህ የመልካሞች ሁሉ መልካም (Supreme Good) የሆነ ታላቅ አካል ከመልካሞች ሁሉ የበለጠ ሊወደድ ይገባል ማለት ነው፡፡      
የአንሰልም ሁለተኛው ማረጋገጫ ከሁሉም በላይ የሆነ (ልዑል) ባህርይ ያለው አካል (Supreme Nature) ስለመኖሩ የሚያትት ነው፡፡   
በዓለማችን ላይ የሚገኙ የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ካለመኖር ወደመኖር ሲመጡ ወይ ከሆነ ነገር (out of something) ተገኝተዋል አልያም ከምንም (out of nothing) የተገኙ ናቸው፡፡
በሳይንሳዊው ሮጀርስ መርህ ደግሞ “Nothing comes from nothing” ከምንም የተገኘ ምንም ነገር የለም፡፡ ስለሆነም በዓለማችን ላይ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተገኙት ከሆነ ነገር (something) ነው ማለት ነው፡፡
ዓለማችን ከሆነ ነገር ተገኝታለች ብለን ካመንን የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ሁሉ የተገኙት ወይ ከአንድ ነገር ነው አልያም ከብዙ ነገሮች ነው ማለት ነው፡፡
ዓለማችን የተገኘችበት ብዛት ያላቸው ነገሮች ካሉ ለእነዚህ ነገሮች ሁሉ አንድ ብቸኛ አስገኚ አላቸው፤ አልያም እንዳንዱ ነገር በራሱ የተገኘ ነው፤ወይም ደግሞ አንዱ ከሌላው የተገኘ ነው፡፡
እያንዳንዱ ነገር በራሱ የተገኘ ነው እንዳንል ምንም ነገር ከምንም ሊገኝ አይችልም፡፡ አንዱ ከሌላው የተገኘ ነው ብንልም አስገኚውን ነገር ያስገነውን ሌላ አስገኚ ማግኘት ግድ ይለናል፡፡ ይህም ብዛት ያላቸውን ነገሮች ያስገኘ፤ በራሱ የተገኘ አንድ ኃይል አለ ወደሚለው ድምዳሜ ያስገባናል፡፡
ብዛት ያላቸው ነገሮች የተገኙበት አንድ አካል አለ ማለት የሚታዩና የማታዩና የማይታዩ ነገሮች በሙሉ የተገኙት በራሳቸው ሳይሆን ከእነርሱ ውጪ በሆነ አካል ነው ማለት ነው፡፡ ከራሱ ውጪ በሆነ አካል የተገኘ ነገር በሙሉ በራሱ ከተገኘ ነገር አንጻር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ወይም ያነሰ ነው፡፡ ስለዚህ በራሱ ከተገኘው አካል ውጪ ያሉ ነገሮች በሙሉ በባህርቸው በራሱ ከተገኘው አካል ያነሱ  ናቸው፡፡ ከዚህም በመነሳት በራሱ የተገኘው አካል ታላቅና (Great) ከሁሉም በላይ የሆነ (ልዑል) ባህርይ (Supreme Nature)  አለው ማለት ነው፡፡ ይህም   አንሰልም  ከሁሉም በላይ እጅግ በጣም መልካም የሆነ አካል (Excellent Being) ስለመኖሩ የሚያትተውን ሶስተኛ ማረጋገጫ ያስከትላል፡፡ 
እንደ ሰር ጀምስ ፍሬዘር ብያኔ አምላክ ማለት የመጀመሪያው ኃያል አስገኚ፣ ዓለምን የሚቆጣጠር፣ ከሰዎች እውቀትና ከተፈጥሮ ህግ በላይ የሆነ አካል ነው፡፡ እንደ አንሰልም እምነት አምላክ ማለት ከእርሱ በላይ ማንም ምንም ኃያልና መልካም ቀዳሚ የሌለ አካል ማለት ነው፡፡  የዚህ ዓይነት አካል (Being) ስለመኖሩ በእእምሮአችን ውስጥ ሊታሰብ ይችላል፤ በሁለተኛው ማረጋገጫ የተመለከተውን ከሁሉም በላይ የሆነ (ልዑል) ባህርይ ያለው አካል (Supreme Nature) በመኖሩ የተስማማ ሰው በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር (Logic) ስሌት መሰረት ይህ አምላክ አለ ብሎ መደምደሙ ተገቢ ይሆናል፡፡
ስለአምላክ ህልውና በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው የፈላስፎች ማረጋገጫ ከስነፍጥረት አንጻር የቀረበ ማሳመኛ (cosmological argument) ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን የነበረው የቶማስ አኲናስና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ሳሙኤል ክላርክም ስራዎች ለዚህ ፍልስና ማሳያዎች ናቸው፡፡
አኲናስም ሆነ አብዛኞቹ የዚህ ፍልስፍና አራማጆች የሚያቀርቡት ማሳመኛዎች የሚከተለውን የአመክንዮ መዋቅር የተከተለ ነው፡፡
ማንም ሰው ስነ-ፍጥረትን ወይም በጊዜና በቦታ ተወስኖ የሚታየውና የማይታየውን ዓለም ህልውና ይገነዘባል፡፡ ይህ ዓለም ደግሞ ራሱን በራሱ አስገኘ ማለት አይችልም፡፡ ይህ እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነ ዓለም ከምንም ተገኘ ማለት ደግሞ አይቻልም፡፡ ከሌላ ከሆነ ግዑዝ ነገር ተገኘ ካልን የመጨረሻውን አስገኚው ለማግኘት መጨረሻ ወደሌለው የአስገኚና የተገኚ ክትትሎሽ ውስጥ እንገባና ያለመልስ እንቀራለን፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም ከጊዜና ከቦታ ውጪ በሆነ ያልተገኘ ግን የሚያስገኝ አንድ የመጨረሻ አካል የተገኘ ነው፡፡
በዚህ ፍልስፍና በቀዳሚነት የሚታወቀው ጣልያናዊው ፈላስፋና የሥነ-መለኮት ምሁር ቅዱስ ቶማስ አኲናስ (1225-1274) “Summa Theologiae” በተባለ መጽሐፉ የፈጣሪን ህልውና በአምስት መንገድ ሊረጋገጥ እንደሚችል አስረድቷል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ማንም ሰው ለማየትና ለማረጋገጥ እንደሚችለው በዓለም ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ነገሮች ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ ማንኛውም ተንቀሳቃሽ ነገር የሚንቀሳቀሰው በሌላ አንቀሳቃሽ ነው፤ ምክንያቱም እንቅስቃሴ የሚፈጠረው አንድን የመንቀሳቀስ አቅም (potentiality) ያለውን ነገር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ (actuality) መለወጥ የሚችል ኃይል ሲኖር ብቻ ነው፡፡ አንድና ተመሳሳይ ነገር ደግሞ በራሱ አንቀሳቃሽም ተንቀሳቃሽም መሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ እንጨት የሚፋጅ ሞቃት የመሆን አቅም አለው ነገር ግን ወደሞቃትነት የሚለወጠው እሳትን ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ስለሆነም ማንኛውም የሚንቀሳቀስ ነገር የግድ በሌላ ሊንቀሳቀስ ይገባል ማለት ነው፡፡ አሁን የምናያቸው የሚንቀሳቀሱ ነገሮች በቅርብ የምናውቀው አንቀሳቃሽ ቢኖራቸውም ለዚያ አንቀሳቃሽ ሌላ አንቀሳቃሽ አለው፡፡ ይህም በመጨረሻው ወደ መጀመሪያው አንቀሳቃሽ እርሱ ግን በሌላ በማንም ወደማይንቀሳቀሰው አንቀሳቃሻ ያደርሰናል፤ እርሱን ሁሉም አምላክ ብለው ይረዱታል፡፡
ሁለተኛ በዚህ በሚታየው ዓለም የምክንያትና (cause) የውጤት (effect) ትስስር ስርዓት እናያለን፤ አንዱ ነገር ቀጥተኛ ምክንያት (efficient cause) ሆኖ ሌላኛውን ሲያንቀሳቅሰው ማለት ነው፡፡ ለአንድ ውጤት አንድ ወይም ከአንድ በላይ ምክንያቶችን በመሃል ላይ ልናገኝ እንችላለን፡፡ እነዚህን ማዕከላዊ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁንም አንዱ ምክንያት ሌላውን አስገኘ እያልን ብንቀጥል የትየለሌ (infinity) ውስጥ እንገባለን፤ ይህም መልስ አይሆንም፡፡ ስለዚህም አንድ የመጀመሪያ ቀጥተኛ ምክንያት (first efficient cause) መኖሩን መቀበል ግድ ይለናል፤ ይህም አምላክ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ነው፡፡
በሌላ በኩል በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን ስንመለከት እንዴት ሊሆን ቻለ (How possible) ብለን እንጠይቃለን፤ ነገሮቹ ሊኖሩ ወይም ላይኖሩ ይችሉ ነበርና፡፡ ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር በማምጣት ረገድ ምንም እንኳ በርካታ መካከለኛ ምክንያቶችን ብንመለከትም በመጀመሪያ የግድ አንድ በራሱ የተገኘ ኃይል (necessity) ሊኖር እንደሚገባ የታመነ ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የተፈጥሮን ሥርዓት ደረጃ (gradation) ስንመለከት አንዱ ነገር ከሌላው የበለጠ ወይም ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአንድ ዋና ምድብ (genus) ውስጥ የምናገኘው የመጨረሻው ነገር የምድቡ አስገኚ ነው፡፡ እሳት የሞቃት ነገሮች ምድብ የመጨረሻው ደረጃ እንደመሆኑ መጠን የሞቃት ነገሮች ሁሉ አስገኚ ነው፡፡ ስለዚህም ከጎዶሎነት ወደ ፍጹምነት ካለማወቅ ወደ ጠቢብነት ከፍ እያልን ስንመጣ የምናገኛቸው የመጨረሻ የፍጹማን ፍጹም የመልካሞች ሁሉ መልካም የጠቢባን ሁሉ ጠቢብ የምክንያቶች ሁሉ ምክንያት አምላክ ብለን የምንጠራው ነው፡፡
በመጨረሻም ከዓለም አስተዳደር (governance of the world) የቀረበውን ማሳመኛ ስንመለከት በሚሰራው ስራ ዙሪያ እውቀት ያነሰው ማንኛውም አካል የተሻለ እውቀትና ጥበብ ባለው ሌላ አካል ካልታገዘ ወይም ካልተመራ በቀር ውጥኑን ከግብ ለማድረስ እንደማይችል ሁሉ ይህቺን ዓለምና በውስጧ ያሉ ነገሮች የተፈጠሩበትን ዓላማ ግብ መምታት እንዲችሉ ዓለምን በዓላማና በጥበብ የሚመራ አንድ እጅግ አዋቂና ጠቢብ አካል (intelligent being) አለ ብሎ ማመን ተገቢ ይሆናል፡፡             
ስለአምላክ ህልውና በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው (Teleological Argument) በመባል የሚታወቀው ሲሆን ይህም አኲናስ በመጨረሻ ደረጃ ካስቀመጠው ማረጋገጫ ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ የዚህ ማሳመኛ ዋና የፍልስፍና መዋቅር ይህቺ ዓለም ያለ አንድ ዓላማ (purpose)፣ ግብና (goal) አስገኚ (designer) በዘፈቀደ የተገኘች አለመሆኗን ማረጋገጥ ነው፡፡
የዊሊያም ፓሊ (William Paley) 1743-1805 የእጅ ሰዓት ምሳሌ (watch analogy) ማሳመኛ በዚህ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የእጅ ሰዓት መሬት ላይ ወድቆ ቢገኝ መሬት ላይ ወድቆ እንደተገኘ ድንጋይ እንዲሁ ያለዓላማና ያለአስገኚ ተገኘ ብለን ማሰብ አይገባንም፤ ምክንያቱም የተገኘው ሰዓት አንድ በሰዓት ህንድስና ጥበብ በተካነ መንዲስ (designer) በጥንቃቄ በውስጡ ያሉት ልዩ ልዩ ጥርሶችና ተገጣጣሚ አካላት እርስ በርስ ተቀናጅተው በቀን አስራ ሁለት ሰዓት፣ በሰዓትና በደቂቃ ደግሞ ስልሳ ጊዜ እየተሽከረከረ ሳይዛነፍ በትክክል ጊዜን ለመለካት ዓላማ የተሰራ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ውስጥ የሚገኙ እጅግ ውስብስብና አስደናቂ በሆነ መንገድ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ነገሮች ለምሳሌ ረቂቅና ግዙፍ፣ እንስሳትና ዕጽዋት፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ አንጎልና ልብ፣ አጥንትና ጅማት፣ፕላኔቶችና ምህዋሮቻቸው የመሳሰሉት ነገሮችም እንዲሁ ያለዓላማና ያለአስገኚ  በዘፈቀደ ተገኙና የሚሰሩ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ይሆናል፡፡ ሰዓቱን የሰራውን መሃንዲስ ማንነት በትክክል አለማወቃችን ለሰዓቱ አስገኚ የለውም ለማለት እንደማያበቃን ሁሉ የአምላክን ማንነት በትክክል አለመረዳታችንም ለዝች ዓለም አስገኚና መጋቢ አምላክ የላትም፤ እንዲሁ የተገኘች ናት ለማለት በቂ ምክንያት አይሆንም ማለት ነው፡፡
እስከ አሁን ከተመለከትናቸው የፈጣሪ ህልውና ማሳመኛዎች በተለየ መልኩ የምናገኘውና የአንዳንድ ግኖስቲክ ፈላስፎች አቋም ከሆነው ፍልስፍና አንዱ የፓስካል ዌይጀር (Pascal’s Wager) ማሳመኛ በመባል ይታወቃል፡፡ እንደ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ፈረንሳዊው ፈላስፋና ሳይንቲስት ብሌይዝ ፓስካል እምነት አምላክ አለ ወይም የለም ብሎ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ፍልስፍናም ሆነ ሳይንስ ለርግጠኝነታችን ድጋፍ ማቅረብ አይችሉም፡፡ በአምላክ ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደ ውርርድ ቁማር (Wager) የተሻለ ያዋጣል ብለን የምናስበውን አቋም ደግፈን በተስፋ ከመጠባበቅ የተሻለ ምርጫ አይኖረንም፡፡ እርግጠኛ ባልሆንበት ሁኔታ አምላክ የለም የሚለውን አቋም ብንይዝና ግምታችን የተሳሳተ ቢሆን ከፍተኛ ዋጋ እንከፍላለን (infinite suffering) ግምታችን ትክክል ሆኖ ቢገኝ ግን የምናገኘው ዋጋ ግን በዘመን የተወሰነ ምድራዊ ደስታ (finite earthly happiness) ነው፤ ነገር ግን እርግጠኛ ባንሆንም እንኳ አምላክ አለ የሚለውን አቋም ብንደግፍ ግምታችን ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ የምናገኘው ሽልማት  እጅግ ከፍ (infinite salvation) ሲሆን የምናጣው እጅግ በጣም አነስተኛ ነገር ነው፡፡ በውርርድ ቁማር ውስጥ ከተሸነፍክ ያስያዝከውን ነገር በሙሉ ታጣለህ፤ ካሸነፍክ ግን ምንም የምታጣው ነገር አይኖርም፡፡ “If you win you win everything, if you lose you lose nothing.” ስለሆነም በአመክንዮ ለሚመራ ሰው በአምላክ ህልውና ካለማመን ይልቅ ማመን የተሻለ ነው፡፡      
›››››…..‹‹‹‹‹

አፍሪካውያን ፍልስፍና አላቸውን?


I wrote for Addis Admas Newspaper (Yekatit 2,2005E.C) 
ብዙዎች አጠቃላይ የፍልስፍናን አጀማመር ከአውሮፓውን ጋር በተለይ ደግሞ ከክ.ል.በፊት በ580 ዓ.ዓ ገደማ ከተነሱ ቀደምት ግሪኮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለመሆኑ በአንድ ድምጽ ይስማማሉ፡፡
አንዳንዶች ከዚህም አልፈው ፍልስፍና በተወሰኑ የዓለም ክፍሎች ለሚኖሩ፣በቆዳ ቀለም ተለይተው ለሚታወቁ የሰው ዝርያዎች ብቻ የተሰጠ ጸጋ መሆኑን በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ኢማኑኤል ካንት በጂኦግራፊካል ስነ-ሰብ (Geographical Anthropology) ጥናቱ የሰውን ዘር ከአካባቢ አንጻር በቆዳቸው ቀለም የአስተሳሰብ ችሎታን በደረጃ ከፋፍሎ ባስቀመጠበት አንቀጽ አፍሪካውያንንና አሜሪ-ኢንዲያንን የመጨረሻዎቹ ተርታ ላይ አሰልፏቸዋል፤ ጀርመናውያንን (አውሮፓውንን) የመጀመሪያ አድርጎ ማለት ነው፡፡
ሌቪ ብሩልና ሄግል የተባሉት አውሮፓውያን የስነ-ሰብ (Anthropology) ተመራማሪዎችም እንዲሁ በጹሁፎቻቸው አፍሪካውያንና አሜሪ-ኢንዲያን እንደ አውሮፓውያን በአመክንዮ ማሰብ ስለማይችሉ (savage, premature or primitive mentality) የራሳቸው ባህልና ታሪክ የላቸውም፤ ለፍልስፍናም ብቁ አይደሉም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ለመሆኑ ፍልስፍና ለአውሮፓውያን ብቻ የተሰጠና በአውሮፓውያን፣ በጀርመኖች ወይም በግሪኮች የተጀመረ ጥበብ ነው ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ጥያቄውን በጥሞና ማስተዋል ግድ ይላል፤ በተለይ በፍልስፍና መጀመርና በፍልስፍና ትምህርት መስፋፋት መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ፡፡ የፍልስፍና አጀማመርን ለመረዳት የፍልስፍናን ምንነት ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ፍልስፍና አንድ እውነት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አንድን መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ወይም በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ለመመለስ የሚደረግ ጥልቅ የአስተሳሰብ ሂደት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ በዘር፣ በጎሳ፣ በቆዳ ቀለም ወይም በአካባቢ ሳይለይ ለሰው ልጆች ሁሉ በተፈጥሮ የተሰጠ የሰብዓዊ ፍጡርነት መገለጫ ነው፡፡ እ.አ.አ በ335ዓ.ዓ የተነሳው የግሪኩ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ (Aristotle) ሰው በምክንያታዊነት ማሰብ የሚችል እንስሳ ነው “Man is a rational animal.” ማለቱ ፍልስፍና የሰውነት መገለጫ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
ፍልስፍና ከሰው ልጆች ወደዝች ዓለም መምጣት ጋር ተያይዞ የተጀመረ የሰውነት መለያና የሰዎች መደበኛ ተግባር እንጂ ከጊዜ በኋላ በአውሮፓ የተፈጠረ ታሪክ አይደለም፡፡
አንሰልም እንደተባለው የመካከለኛው ዘመን አውሮፓዊ ክርስቲያን ፈላስፋ ማሳመኛ (argument) አምላክ በባህርይው ምክንያታዊ ስለሆነና መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሰው በአምላክ አምሳል መፈጠሩን ስለሚናገር፤ በአምላክ አምሳል የተፈጠረው የሰው ዘር በሙሉ እንደ አምላኩ ምክንያታዊ ነው የሚለው ድምዳሜ ምክንያታዊ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው አምላክ ለመጀመሪያው ሰው አዳም ትዕዛዝ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮና አዳም “መልካምና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ በበበላህ ቀን  ሞትን ትሞታለህ” የተባለበትን እውነተኛ ምክንያት ምንነት የማወቅ  ውስጣዊ ጥያቄ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች ዘንድ የፍልስፍና ጥያቄ ተጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡ ይህንንም የሰው ልጅ ለፍልስፍና ያለውን ብርቱ ፍላጎት አዳምና ሄዋን ከአምላካቸው ትዕዛዝ ይልቅ በእባብ በቀረበላቸው አመክኖአዊ ማብራሪያ በመማረካቸውና፤ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያም ለመሻር በመብቃታቸው እንረዳለን፡፡
በአጠቃላይ የፍልስፍና አጀማመር ከሰው ልጅ ማሰብ መጀመር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፤ በዓለም ታሪክ ቀደምት ስልጣኔ የነበራቸው ህዝቦች በሙሉ በተለይ ሜሶፖታሚያ፣ ግብፅ፣ እንዲሁም ቻይናና ህንድን የመሳሰሉ የሩቅ ምስራቅ ህዝቦች ሁሉ የራሳቸው ፍልስፍና ስልጣኔ ታሪክ ያላቸው ስለሆኑ፤የፍልስፍና ጀማሪነትንም ሆነ ባለቤትነትን ለግሪኮች ብቻ መስጠት ስህተት ይሆናል፡፡ ይልቁንም ጥንታዊ ግሪኮች በምእራባውያን የፍልስፍና ታሪክ (History of Western Philosophy) ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ መያዛቸውን ማስረገጥ ይገባል፡፡
ፍልስፍና ወይም ምክንያታዊነት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ሃብት ነው ስንል ግን በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦችና ግለሰቦች በሙሉ ተመሳሳይ የፍልስፍና ባህል አላቸው ማለታችን ግን አይደለም፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠን የፍልስፍና ዝንባሌ በግለሰቦች ንቃተ-ህሊና፣ ልምምድና የፍልስፍና ትምህርት ወይም በማህበረሰቡ ባህልና የጋርዮሽ ፍልስፍና ተጽዕኖ ሊጎለብት ወይም ሊዳፈን ይችላል፡፡
ይህም ማለት አከራካሪው ነጥብ የፍልስፍና አጀማመርና ባለቤትነት ሳይሆን የፍልስፍና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጠው የክብር ቦታ ወይም ጥልቅ ምክንያታዊነት እንደ ባህል የመዳበሩና ያለመዳበሩ ጉዳይ ነው፡፡
አንዳንድ ህዝቦች ስለፍልስፍና ካላቸው የዕውቀት ማነስና የግንዜቤ መዛባት የተነሳ ለመስኩ ጭፍን ጥላቻን በማዳበር ፍልስፍናን ሲሸሹት፣ የፍልስፍና ዝንባሌ ያላቸውን ግለሰቦችን ሲያሳድዱ፣ የጻፏቸውንም መጻህፍት ሲቃጥሉ ኖረዋል፤ በዚህም ምክንያት በእንደነዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ ፍልስፍናና ስሁል መስተሐልይ (critical thinking) በበቂ ሁኔታ ሊዳብር አይችልም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ግለሰቦች ለፍልስፍና ወይም ለእውነት ካላቸው ፍቅር የተነሳ በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ፍልስፍና በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት ለታወቅና በግለሰቦች የህይወት ፍልስፍና  ውስት ትልቅ ስፍራ ለማግኘት ከመቻሉም ባሻገር እነዚሁ ጥቂት ግለሰቦች ፍልስፍናቸውን በቃል አስተምረው ህዝባቸውን ለማንቃትና በጻፏቸው መጻህፍት ደግሞ ለሌላው ህዝብ ለመትረፍ ችለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በጥቅሉ አውሮፓውያንን በነጠላ ደግሞ ጥንታውያን ግሪኮችን የሚበልጥ አይኖርም ለማለት እደፍራለሁ፡፡ እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትርን ረስል “The History of Western Philosophy” በሚለው መጽሃፉ ላይ በአውሮፓውያን የፍልስፍና ታሪክ የመጀመሪያው ፈላስፋ በመባል ከሚታወቀው ቴሊስ (Thales) ጀምሮ በየዘመናቱ በቃልና በጽሁፍ የተላለፈውን የፍልስፍና ዕድገት ይተርካል፡፡
በዓለም የሚገኙ ነገሮች የተገኙበትን ጥንተ ቁስ (Primordial matter) ምንነትና ካለመኖር ወደ መኖር መምጣትና ከመኖር ወደ አለመኖር የመመለስን የተፈጥሮ ምስጢር ላይ ለመድረስ ይነሳ የነበረውን የዲበአካላዊነት (metaphysical) ጥያቄ በምዕራብም ሆነ በምስራቅ ያሉ ህዝቦች በየዘመናቱ በየራሳቸው መንገድ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡
ለምሳሌ ምዕራባዊው ፈላስፋ ቴሊስ በ546 ዓ.ዓ ገደማ ዓለም የተገኘችበት ንጥተ ቁስ ውሃ መሆኑን ተናግሯል፤ተከታዩ አናግዚሜንስ ጥንተ ቁሱ ንፋስ ነው ሲል ሄራክሊተስ ደግሞ እሳት ነው ብሎ ነበር፣ ፓይታጎረስም በተለየ ሁኔታ የዓለም መገኘት ምስጢር ቁጥሮች ናቸው ብሎ ያምን ነበር፡፡
አፍሪካውያን ፍልስፍና አላቸው? የሚለው ጥያቄ አፍሪካውን እንደ ሰው ያስባሉ? መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ያነሳሉ ? የተነሳባቸውን ጥያቄ ለመመለስ በራሳቸው መንገድ ይፍጨረጨራሉ? ከሚሉት ጥያቄዎች ተለይቶ አይታይም፡፡ መልሱም አወንታዊ ነው፡፡ ምንም እንኳ የፍልስፍና መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰው ልጆች ሁሉ ዘንድ በጋራ የሚነሱ ቢሆኑም ጥያቄዎቹ የሚመለሱበት መንገድ ግን ከግለሰብ ግለሰብ፤ ከአህጉር አህጉር ሊለያይ ይችላል፡፡
እንደ ኬንያዊው ፈላስፋ ኦዴራ ኦሩካ እምነት አፍሪካውያን ከአውሮፓውን በተለየ ሁኔታ ፍልስፍናቸውን በአራት የተለያዩ መንገዶች ሊከናውኑ ይችላሉ፡፡
የመጀመሪያው ኢትኖፊሎሶፊ (ethno philosophy) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህም የአፍሪካውያን ፍልስፍና እንደ ቋንቋና ሃይማኖት በመሳሰሉ የማህበረሰቡ  ቱባ ባህላዊ እሴቶች ውስጥ በገቢር የሚገለጽ ነው የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የማህበረሰቡ ፍልስፍና አጭር መገለጫዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል አክሲማሮስ የተባለው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ብራና የሃይማኖት መጽሐፍ ዓለም ስለተገኘበት ጥንተ ቁስ ምንነት ሲያብራራ አምላክ በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሁድ አራቱን ባህርያተ ሥጋ በመባል የሚታወቁትን ጥንተ ቁሶች ማለትም ንፋስ፣ እሳት ውሃ እና መሬት (አፈርን) በአርምሞ መፍጠሩን ይተርካል፡፡ ይህም ምዕራባውያኑ ፈላስፎች እነ ቴሊስ፣ አናግዜሜንስና ሄራክሊተስ ሃሳብ ጋር እንዲሁም በኦሪት ዘፍጥረት “አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው” ከሚለው ኃይለ ቃል ጋር ተቀራራቢ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ፊሎሶፊክ ሳጋሲቲ (Philosophic Sagacity) ሁለተኛው የአፍሪካውያን ፍልስፍና መልክ ሲሆን ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ለየት ያለ የፍልስፍና ዝንባሌ ባላቸው የማህበረሰቡ ነባር አባላት የሚካሄድ የፍልስፍና ተግባር ነው፡፡ ይህ የሳጋሲቲ ፍልስፍና እነዚህ ግለሰቦች በማህበረሰባቸው ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ዙሪያ የሚያሳዩት ምልከታ፣ ወይም በሚያቀርቡት የሰላ ትችትና አማራጭ አስተሳሰብ የሚገለጽ ነው፡፡ በኢትዮያ ውስጥ በስፋት የሚታወቁት የአውራ አምባ ማህበረሰብ መሪ ዙምራ አስተሳሰብን ለዚህ ዓይነቱ ፍልስፍና ዓቢይ ምሳሌ ይሆናል፡፡
የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና         (Politico- ideological Philosophy) ሶስተኛው የአፍሪካውያን ፍልስፍና መገለጫ ሲሆን በተለይ በቅኝ ግዛት የነበሩ አፍሪካውያን ሀገራቸውን ከአውሮፓውያን ቀጥተኛና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣትና ህዝባቸውን በተሻለ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ የዕድገት መንገድ ለመምራት ቅኝ ገዢዎቻቸው ምዕራባውያን ፈላስፎችና መሪዎች ካቀረቡላቸው ርዕዮተ ዓለም የተለየና በአፍሪካውያን ነባር ማህበረሰባዊ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ይዘው በቀረቡ  ልዩ ልዩ የአፍሪካ መሪዎች የሚሰራ ፍልስፍና ነው፡፡ የታንዛንያው የቀድሞ ፕሬዚደንት ጁሊየስ ኔሬሬ የገጠር ሶሻሊዝም ፍልስፍና (Ujamaa)፣ የጋናው ክዋሜ ንክሩማ አፍሪካን አንድ የማድረግ ፍልስፍና (Pan-Africanism)፣ የደቡብ አፍሪካው ታቦ ምቤኪ የአፍሪካ ህዳሴ (African Renaissance) እንዲሁም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ የኢትዮጰያ ህዳሴ (Ethiopian Renaissance) ርዕዮተ ዓለም የዚህ ፍልስፍና ማሳያዎች ናቸው፡፡
አራተናውና የመጨረሻው የአፍሪካውን ፍልስፍና ዘውግ ሙያዊ ፍልስፍና      (professional Philosophy) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ዘውግ ፍልስፍናን በዩኒቨርስቲ  ውስጥ በማጥናት ልዩ ልዩ ደረጃ ያለው ዲግሪ ያገኙና በተለያየ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ወይም በአፍሪካ ወይም ከአፍሪካ ውጪ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፍልስፍናን በሚስተምሩ አፍሪካውያን የሚቀርቡ ፍልስፍና ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የነ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ቴዎድሮስ ኪሮስ፣ ጸናይ ሰረቀብርሃን ክዋሴ ዊሬዱና ኦዴራ ኦሩካ ከውጪ እንዲሁም የነዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ወርቅነህ ቀልቤሳ፣ በቀለ ጉተማ፣  ጠና ዳዎ ስራዎች ከሀገር ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንደ ካናዳዊው ኢትዮጵያዊ ክላውድ ሰምነር ማሳመኛ በአቀራረቡም ሆነ በይዘቱ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ከነበሩ ፈላስፎች ተርታ የሚሰለፈው የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ሌላው የአፍሪካውን ፍልስፍና ገጽታ ነው፡፡
›››››….‹‹‹‹‹