Monday, March 4, 2013

አፍሪካውያን ፍልስፍና አላቸውን?


I wrote for Addis Admas Newspaper (Yekatit 2,2005E.C) 
ብዙዎች አጠቃላይ የፍልስፍናን አጀማመር ከአውሮፓውን ጋር በተለይ ደግሞ ከክ.ል.በፊት በ580 ዓ.ዓ ገደማ ከተነሱ ቀደምት ግሪኮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለመሆኑ በአንድ ድምጽ ይስማማሉ፡፡
አንዳንዶች ከዚህም አልፈው ፍልስፍና በተወሰኑ የዓለም ክፍሎች ለሚኖሩ፣በቆዳ ቀለም ተለይተው ለሚታወቁ የሰው ዝርያዎች ብቻ የተሰጠ ጸጋ መሆኑን በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ኢማኑኤል ካንት በጂኦግራፊካል ስነ-ሰብ (Geographical Anthropology) ጥናቱ የሰውን ዘር ከአካባቢ አንጻር በቆዳቸው ቀለም የአስተሳሰብ ችሎታን በደረጃ ከፋፍሎ ባስቀመጠበት አንቀጽ አፍሪካውያንንና አሜሪ-ኢንዲያንን የመጨረሻዎቹ ተርታ ላይ አሰልፏቸዋል፤ ጀርመናውያንን (አውሮፓውንን) የመጀመሪያ አድርጎ ማለት ነው፡፡
ሌቪ ብሩልና ሄግል የተባሉት አውሮፓውያን የስነ-ሰብ (Anthropology) ተመራማሪዎችም እንዲሁ በጹሁፎቻቸው አፍሪካውያንና አሜሪ-ኢንዲያን እንደ አውሮፓውያን በአመክንዮ ማሰብ ስለማይችሉ (savage, premature or primitive mentality) የራሳቸው ባህልና ታሪክ የላቸውም፤ ለፍልስፍናም ብቁ አይደሉም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ለመሆኑ ፍልስፍና ለአውሮፓውያን ብቻ የተሰጠና በአውሮፓውያን፣ በጀርመኖች ወይም በግሪኮች የተጀመረ ጥበብ ነው ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ጥያቄውን በጥሞና ማስተዋል ግድ ይላል፤ በተለይ በፍልስፍና መጀመርና በፍልስፍና ትምህርት መስፋፋት መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ፡፡ የፍልስፍና አጀማመርን ለመረዳት የፍልስፍናን ምንነት ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ፍልስፍና አንድ እውነት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አንድን መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ወይም በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ለመመለስ የሚደረግ ጥልቅ የአስተሳሰብ ሂደት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ በዘር፣ በጎሳ፣ በቆዳ ቀለም ወይም በአካባቢ ሳይለይ ለሰው ልጆች ሁሉ በተፈጥሮ የተሰጠ የሰብዓዊ ፍጡርነት መገለጫ ነው፡፡ እ.አ.አ በ335ዓ.ዓ የተነሳው የግሪኩ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ (Aristotle) ሰው በምክንያታዊነት ማሰብ የሚችል እንስሳ ነው “Man is a rational animal.” ማለቱ ፍልስፍና የሰውነት መገለጫ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
ፍልስፍና ከሰው ልጆች ወደዝች ዓለም መምጣት ጋር ተያይዞ የተጀመረ የሰውነት መለያና የሰዎች መደበኛ ተግባር እንጂ ከጊዜ በኋላ በአውሮፓ የተፈጠረ ታሪክ አይደለም፡፡
አንሰልም እንደተባለው የመካከለኛው ዘመን አውሮፓዊ ክርስቲያን ፈላስፋ ማሳመኛ (argument) አምላክ በባህርይው ምክንያታዊ ስለሆነና መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሰው በአምላክ አምሳል መፈጠሩን ስለሚናገር፤ በአምላክ አምሳል የተፈጠረው የሰው ዘር በሙሉ እንደ አምላኩ ምክንያታዊ ነው የሚለው ድምዳሜ ምክንያታዊ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው አምላክ ለመጀመሪያው ሰው አዳም ትዕዛዝ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮና አዳም “መልካምና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ በበበላህ ቀን  ሞትን ትሞታለህ” የተባለበትን እውነተኛ ምክንያት ምንነት የማወቅ  ውስጣዊ ጥያቄ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች ዘንድ የፍልስፍና ጥያቄ ተጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡ ይህንንም የሰው ልጅ ለፍልስፍና ያለውን ብርቱ ፍላጎት አዳምና ሄዋን ከአምላካቸው ትዕዛዝ ይልቅ በእባብ በቀረበላቸው አመክኖአዊ ማብራሪያ በመማረካቸውና፤ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያም ለመሻር በመብቃታቸው እንረዳለን፡፡
በአጠቃላይ የፍልስፍና አጀማመር ከሰው ልጅ ማሰብ መጀመር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፤ በዓለም ታሪክ ቀደምት ስልጣኔ የነበራቸው ህዝቦች በሙሉ በተለይ ሜሶፖታሚያ፣ ግብፅ፣ እንዲሁም ቻይናና ህንድን የመሳሰሉ የሩቅ ምስራቅ ህዝቦች ሁሉ የራሳቸው ፍልስፍና ስልጣኔ ታሪክ ያላቸው ስለሆኑ፤የፍልስፍና ጀማሪነትንም ሆነ ባለቤትነትን ለግሪኮች ብቻ መስጠት ስህተት ይሆናል፡፡ ይልቁንም ጥንታዊ ግሪኮች በምእራባውያን የፍልስፍና ታሪክ (History of Western Philosophy) ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ መያዛቸውን ማስረገጥ ይገባል፡፡
ፍልስፍና ወይም ምክንያታዊነት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ሃብት ነው ስንል ግን በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦችና ግለሰቦች በሙሉ ተመሳሳይ የፍልስፍና ባህል አላቸው ማለታችን ግን አይደለም፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠን የፍልስፍና ዝንባሌ በግለሰቦች ንቃተ-ህሊና፣ ልምምድና የፍልስፍና ትምህርት ወይም በማህበረሰቡ ባህልና የጋርዮሽ ፍልስፍና ተጽዕኖ ሊጎለብት ወይም ሊዳፈን ይችላል፡፡
ይህም ማለት አከራካሪው ነጥብ የፍልስፍና አጀማመርና ባለቤትነት ሳይሆን የፍልስፍና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጠው የክብር ቦታ ወይም ጥልቅ ምክንያታዊነት እንደ ባህል የመዳበሩና ያለመዳበሩ ጉዳይ ነው፡፡
አንዳንድ ህዝቦች ስለፍልስፍና ካላቸው የዕውቀት ማነስና የግንዜቤ መዛባት የተነሳ ለመስኩ ጭፍን ጥላቻን በማዳበር ፍልስፍናን ሲሸሹት፣ የፍልስፍና ዝንባሌ ያላቸውን ግለሰቦችን ሲያሳድዱ፣ የጻፏቸውንም መጻህፍት ሲቃጥሉ ኖረዋል፤ በዚህም ምክንያት በእንደነዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ ፍልስፍናና ስሁል መስተሐልይ (critical thinking) በበቂ ሁኔታ ሊዳብር አይችልም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ግለሰቦች ለፍልስፍና ወይም ለእውነት ካላቸው ፍቅር የተነሳ በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ፍልስፍና በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት ለታወቅና በግለሰቦች የህይወት ፍልስፍና  ውስት ትልቅ ስፍራ ለማግኘት ከመቻሉም ባሻገር እነዚሁ ጥቂት ግለሰቦች ፍልስፍናቸውን በቃል አስተምረው ህዝባቸውን ለማንቃትና በጻፏቸው መጻህፍት ደግሞ ለሌላው ህዝብ ለመትረፍ ችለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በጥቅሉ አውሮፓውያንን በነጠላ ደግሞ ጥንታውያን ግሪኮችን የሚበልጥ አይኖርም ለማለት እደፍራለሁ፡፡ እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትርን ረስል “The History of Western Philosophy” በሚለው መጽሃፉ ላይ በአውሮፓውያን የፍልስፍና ታሪክ የመጀመሪያው ፈላስፋ በመባል ከሚታወቀው ቴሊስ (Thales) ጀምሮ በየዘመናቱ በቃልና በጽሁፍ የተላለፈውን የፍልስፍና ዕድገት ይተርካል፡፡
በዓለም የሚገኙ ነገሮች የተገኙበትን ጥንተ ቁስ (Primordial matter) ምንነትና ካለመኖር ወደ መኖር መምጣትና ከመኖር ወደ አለመኖር የመመለስን የተፈጥሮ ምስጢር ላይ ለመድረስ ይነሳ የነበረውን የዲበአካላዊነት (metaphysical) ጥያቄ በምዕራብም ሆነ በምስራቅ ያሉ ህዝቦች በየዘመናቱ በየራሳቸው መንገድ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡
ለምሳሌ ምዕራባዊው ፈላስፋ ቴሊስ በ546 ዓ.ዓ ገደማ ዓለም የተገኘችበት ንጥተ ቁስ ውሃ መሆኑን ተናግሯል፤ተከታዩ አናግዚሜንስ ጥንተ ቁሱ ንፋስ ነው ሲል ሄራክሊተስ ደግሞ እሳት ነው ብሎ ነበር፣ ፓይታጎረስም በተለየ ሁኔታ የዓለም መገኘት ምስጢር ቁጥሮች ናቸው ብሎ ያምን ነበር፡፡
አፍሪካውያን ፍልስፍና አላቸው? የሚለው ጥያቄ አፍሪካውን እንደ ሰው ያስባሉ? መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ያነሳሉ ? የተነሳባቸውን ጥያቄ ለመመለስ በራሳቸው መንገድ ይፍጨረጨራሉ? ከሚሉት ጥያቄዎች ተለይቶ አይታይም፡፡ መልሱም አወንታዊ ነው፡፡ ምንም እንኳ የፍልስፍና መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰው ልጆች ሁሉ ዘንድ በጋራ የሚነሱ ቢሆኑም ጥያቄዎቹ የሚመለሱበት መንገድ ግን ከግለሰብ ግለሰብ፤ ከአህጉር አህጉር ሊለያይ ይችላል፡፡
እንደ ኬንያዊው ፈላስፋ ኦዴራ ኦሩካ እምነት አፍሪካውያን ከአውሮፓውን በተለየ ሁኔታ ፍልስፍናቸውን በአራት የተለያዩ መንገዶች ሊከናውኑ ይችላሉ፡፡
የመጀመሪያው ኢትኖፊሎሶፊ (ethno philosophy) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህም የአፍሪካውያን ፍልስፍና እንደ ቋንቋና ሃይማኖት በመሳሰሉ የማህበረሰቡ  ቱባ ባህላዊ እሴቶች ውስጥ በገቢር የሚገለጽ ነው የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የማህበረሰቡ ፍልስፍና አጭር መገለጫዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል አክሲማሮስ የተባለው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ብራና የሃይማኖት መጽሐፍ ዓለም ስለተገኘበት ጥንተ ቁስ ምንነት ሲያብራራ አምላክ በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሁድ አራቱን ባህርያተ ሥጋ በመባል የሚታወቁትን ጥንተ ቁሶች ማለትም ንፋስ፣ እሳት ውሃ እና መሬት (አፈርን) በአርምሞ መፍጠሩን ይተርካል፡፡ ይህም ምዕራባውያኑ ፈላስፎች እነ ቴሊስ፣ አናግዜሜንስና ሄራክሊተስ ሃሳብ ጋር እንዲሁም በኦሪት ዘፍጥረት “አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው” ከሚለው ኃይለ ቃል ጋር ተቀራራቢ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ፊሎሶፊክ ሳጋሲቲ (Philosophic Sagacity) ሁለተኛው የአፍሪካውያን ፍልስፍና መልክ ሲሆን ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ለየት ያለ የፍልስፍና ዝንባሌ ባላቸው የማህበረሰቡ ነባር አባላት የሚካሄድ የፍልስፍና ተግባር ነው፡፡ ይህ የሳጋሲቲ ፍልስፍና እነዚህ ግለሰቦች በማህበረሰባቸው ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ዙሪያ የሚያሳዩት ምልከታ፣ ወይም በሚያቀርቡት የሰላ ትችትና አማራጭ አስተሳሰብ የሚገለጽ ነው፡፡ በኢትዮያ ውስጥ በስፋት የሚታወቁት የአውራ አምባ ማህበረሰብ መሪ ዙምራ አስተሳሰብን ለዚህ ዓይነቱ ፍልስፍና ዓቢይ ምሳሌ ይሆናል፡፡
የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና         (Politico- ideological Philosophy) ሶስተኛው የአፍሪካውያን ፍልስፍና መገለጫ ሲሆን በተለይ በቅኝ ግዛት የነበሩ አፍሪካውያን ሀገራቸውን ከአውሮፓውያን ቀጥተኛና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣትና ህዝባቸውን በተሻለ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ የዕድገት መንገድ ለመምራት ቅኝ ገዢዎቻቸው ምዕራባውያን ፈላስፎችና መሪዎች ካቀረቡላቸው ርዕዮተ ዓለም የተለየና በአፍሪካውያን ነባር ማህበረሰባዊ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ይዘው በቀረቡ  ልዩ ልዩ የአፍሪካ መሪዎች የሚሰራ ፍልስፍና ነው፡፡ የታንዛንያው የቀድሞ ፕሬዚደንት ጁሊየስ ኔሬሬ የገጠር ሶሻሊዝም ፍልስፍና (Ujamaa)፣ የጋናው ክዋሜ ንክሩማ አፍሪካን አንድ የማድረግ ፍልስፍና (Pan-Africanism)፣ የደቡብ አፍሪካው ታቦ ምቤኪ የአፍሪካ ህዳሴ (African Renaissance) እንዲሁም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ የኢትዮጰያ ህዳሴ (Ethiopian Renaissance) ርዕዮተ ዓለም የዚህ ፍልስፍና ማሳያዎች ናቸው፡፡
አራተናውና የመጨረሻው የአፍሪካውን ፍልስፍና ዘውግ ሙያዊ ፍልስፍና      (professional Philosophy) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ዘውግ ፍልስፍናን በዩኒቨርስቲ  ውስጥ በማጥናት ልዩ ልዩ ደረጃ ያለው ዲግሪ ያገኙና በተለያየ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ወይም በአፍሪካ ወይም ከአፍሪካ ውጪ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፍልስፍናን በሚስተምሩ አፍሪካውያን የሚቀርቡ ፍልስፍና ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የነ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ቴዎድሮስ ኪሮስ፣ ጸናይ ሰረቀብርሃን ክዋሴ ዊሬዱና ኦዴራ ኦሩካ ከውጪ እንዲሁም የነዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ወርቅነህ ቀልቤሳ፣ በቀለ ጉተማ፣  ጠና ዳዎ ስራዎች ከሀገር ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንደ ካናዳዊው ኢትዮጵያዊ ክላውድ ሰምነር ማሳመኛ በአቀራረቡም ሆነ በይዘቱ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ከነበሩ ፈላስፎች ተርታ የሚሰለፈው የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ሌላው የአፍሪካውን ፍልስፍና ገጽታ ነው፡፡
›››››….‹‹‹‹‹

No comments:

Post a Comment