ዛሬ ሳይንስ ብለን የምንጠራው ማንኛውም የዕውቀት ዘርፍ መገኛው የዓለም
ፍልስፍና፤ አስገኚዎቹና ጀማሪዎቹ መሀንዲሶች ደግሞ የዓለም ፈላስፎች
ናቸው፡፡ ለዚህም የአሪስጣጣሊስን ሁለገብ ስራዎች፣ የፍራንሲስ ቤከንን ኢንደክቲቪዝምና የፓይታጎረስ ቴረምን በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ከዚህም ባሻገር ከአባታቸው ከፍልስፍና በመገንጠል ራሳቸውን ችለው የተፈጥሮና
የማህበረሰብ ሳይንስ በሚል መጠሪያ ኑሮን የጀመሩት ልጆቹንና፤ ሂሳብ፣ አስትሮኖሚ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ህግ፣ ሶሲዎሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ፣
ፖለቲካል ሳይንስና ወዘተ በመባል የሚታወቁት የልጅ ልጆቹን በአመክንዮ ባህል ከስር ከስር ኮትኩቶ በማሳደግና መስመር ሲስቱ በመገሰጽ
የሚጠበቅበትን ድርሻ ያለማቋረጥ በመወጣት ላይ ይገኛል፤ ፍልስፍና፡፡
ይሁንና በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች ላይ ከአባቶቻቸውና ከአያቶቻቸው
ርቀው በስደት የሚኖሩና ስለቀደመ ታሪካቸውና አሴቶቻቸው እምብዛም የማያውቁ ሳይንሶችና የእነርሱ ሞግዚት ሳይንቲስቶቻቸው ከአባታቸው ፍልስፍና በዘመንና በባህርይ በመራራቃቸው አባታቸው እንደ ሞተና
እንደ ተረሳ በመቁጠር ከእርሱ መውረስ የሚገባቸውን ስልታዊ መጠራጠርን (Methodical skepticism) ፣ በጥልቀት የመጠየቅና
(critical inquiry) የማሄስ (critique) ባህልን ወደ ጎን በመተው ሳይንሳዊ ሃይማኖትን (Scientific dogmatism) ገንዘብ በማድረጋቸው
በማንነት ጥያቄ ውዥንብር ውስጥ ገብተው የተወለዱበትን ዓላማ ማሳካት አቅቷቸው ሲደነባበሩ መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የአባታቸውንና ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ ሳይንሶችና ሞግዚቶቻቸው
ሳይንቲስቶች ባሉባቸው ክፍላተ ዓለማት ውስጥ የሳይንስና ፍልስፍና ዘለዓለማዊ ቁርኝትና መግቦት እስከዛሬ ህያው ሆኖ እናገኛለን፡፡
ለዚህም ነው የጽሁፌን ርዕስ ፍልስፍና የሳይንስ አልፋና ኦሜጋ በማለት የሰየምኩት፡፡ አልፋና ዖሜጋ በግሪክ የመጀመሪያና የመጨረሻ
ማለት፡፡ ከሳይንሶች ሁሉ በፊት የነበረ በመሆኑና እነርሱም ከእርሱ በመገኘታቸው የመጀመሪያ ስለው የመጨረሻ ያልኩበት ምክንያትም ዛሬም ድረስ ፍልስፍና ለሳይንስ መሻሻል የላቀ አስተዎጽኦ በማበርከት
ላይ በመሆኑ ነው፡፡
በፍልስፍናና በሳይንስ መካከል እጅግ ጠንካራ ትስስር እናገኛለን፡፡ ከሳይንስ
ከተለየ ፍልስፍና ግምታዊ ዕውቀት (Speculative Knowledge) እንደሚሆን ሁሉ፤ ከፍልስፍና የተለየ ሳይንስም እንዲሁ አዳዲስ
ፈጠራዎች የማይገኙበትና በእምነት ላይ የተመሰረተ የዘልማድ ዕውቀት (Common sense Knowledge) መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
በማንኛውም የሳይንስ ዘርፍ ለከፍተኛው የትምህርት፣ የምርምርና የግኝት
ደረጃ የሚሰጠው ዲግሪ የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ (Doctor of Philosophy) ወይም በምህጻረ ቃል ፒ.ኤች.ዲ
(Ph.D) ተብሎ መሰየሙ ፍልስፍና የሳይንስ ኦሜጋ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ስለ ዕውቀት ምንነት፣ ስለእውነትና እውነተኛ እውቀት ምንነትና ስለ ሰው
ልጆች የእውቀት ምንጭ፣ ስለ ሳይንስ፣ ሳይንሳዊ ስነ-ዘዴና ሌሎች ሳይንሳዊ ያልሆኑ የእውቀት መንገዶች የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና
ንዑስ ዘርፍ ስነ-ዕውቀት (epistemology) ይባላል፡፡
ይህ የፍልስፍና ዘርፍ ባለንበት ዘመን “የሳይንስ ፍልስፍና” (Philosophy of Science) በሚል ሳይንሳዊ
እውቀት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ የሳይንስን ፍልስፍናዊ መሰረት ጠንቅቀው በሚያውቁ ምሁራን በሚመሩ በርካታ ዓለማችን ከፍተኛ የትምህርት
ተቋማት ውስጥ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት በተለይ ለሳይንስ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንደ አንድ ወሳኝ (Compulsory) ኮርስ
ይሰጣል፡፡
የሳይንስ ፍልስፍና ትምህርት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የድኅረ ምረቃ
ተማሪዎች፤ በተለይም ፒ.ኤች.ዲ ተመራማሪዎች ዋነኛ ግብ አዲስ እውቀትን ማግኘት (Innovation & Discovery) እንደመሆኑ
መጠን ለማንኛውም የሳይንስ ጥናት መስኮች የሚዘጋጁ ምሁራን ስለ እውቀት ምንነት፣ ምንጮችና መስፈርቶች ወዘተ ማወቃቸው የግድ አስፈላጊ
በመሆኑ ነው፡፡
የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በዘልማድ ከሚያውቁት ወይም በአንደኛ፣ በሁለተኛ
ደረጃና በቅድመ ምረቃ ትምህርት ሂደት ላይ ካወቁትና ካወቁበት መንገድ በተለየ ሁኔታ እንዲጠይቁ፣ አንዲመራመሩና በተሰማሩበት የምርምር
ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ነባር ንድፈ ሃሳቦችን በእምነት እንዲቀበሉ ሳይሆን በጥልቀት እንዲፈትሹና እንዲያሻሽሉ፣ ማህበራዊ ችግሮችን
እንዲለዩና እንዲፈቱ፣ አዳዲስ ንድፈ ሃሳቦችን (New Theory) እንዲያፈልቁ፣ እንዲሁም እንደ ሳይንስ አብዮተኛው ኮፐርኒከስ
(Copernicus Revolutions) አዲስ የአስተሳሰብ አድማስ (New Paradigm) ወይም ርዕዮተ ዓለም (World
View) እንዲያመጡ፤ በአጠቃላይ የነገዎቹን ሳንቲስቶችና ቴክኖሎጂስቶችን ለማፍራት “የሳይንስ ፍልስፍናን” ማስተማር የጥናትና ምርምርን
ሀ-ሁ እንደማስቆጠር ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን በሀገሪቱ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አብዮት
ለማምጣት ሰባ በመቶ ትኩረት ሰጥተው በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ መርሃግብሮች በትጋት እየሰሩ መሆናቸው በሚነገርላቸው የኢትዮጵያ
ዩኒቨርስቲዎች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ምንም ዓይነት “የሳይንስ ፍልስፍና” ትምህርት አለመካተቱ ነው፡፡ አንዳንድ ተቋማት ይባስ
ብለው ከአንዳንድ የቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንደ Introduction to Logic የመሳሰሉ ወሳኝ የፍልስፍና
ትምህርት ዓይነቶች እንደ አላስፈላጊ በመቁጠር ከቀድሞው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ለቅመው አስወግደዋቸዋል፡፡
ለሀገር ልማት ሳይንስ፤ ለሳይንስ እድገት ደግሞ የፍልስፍና ህልውና ይህን
ያህል አስፈላጊ ሆኖ ሳለ በሀገራችን ለፍልስፍናና ለፍልስፍና ኮርሶች ይህን ያህል ትኩረት መነፈጉ ለምን ይሆን? የፍልስፍናን በሰው
ልጆች ሁለንተናዊ ልማት (Genuine Development) ላይ ያለውን ሚና ከማንም በላይ የሚውቁትና የተጠቀሙበት ምዕራባውያንና
በምዕራባውያን ተጽዕኖ ስር የሚገኙት እንደ IMF እና World Bank ዓይነት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትስ ፍልስፍናን እንዴት
ለአፍሪካውያን ሳያስቡት ቀሩ?